የእለት ዜና

የመስቀል በዓል እና የቱሪስት ፍሰት

የመስቀል በዓል በኢትዮጵያ በጣም አስደሳች ከሆኑት አውደ ዓመቶች አንዱ ነው። በዓሉ በርካታ ችቦዎች በአንድ ላይ ተደምረው የሚበሩበት በዓል ነው። የመስቀል በዓል የተለያዩ የባህር ማዶ ጎብኚዎች መጥተው የሚጎበኙት ከበርካታ የአገሪቱ የማይዳሰሱ ቅርሶች አንዱ ነው።
ኢትዮጵያ ከሌላው ዓለም የተለየ የቀን መቁጠሪያ ያላት አገር ስትሆን፣ መስቀል አሮጌው ዓመት አልፎ አዲስ ዓመት በገባ በ17ኛው ቀን የሚከበር ኃይማኖታዊ በዓል ነው።
የመስቀል በዓል ከአደባባይ ኃይማኖታዊ በዓላት ውስጥ የሚካተት ሲሆን፣ ከበዓሉን ስያሜውን ባገኘው የመስቀል አደባባይ ላይ በርካታ መንፈሳዊ ክንውኖች ይካሄዳሉ።
የቱሪዝም ኢትዮጵያ መረጃ የሚጠቁመው፣ በአሁኑ ጊዜ ወቅታዊ የሆነው የኮቪድ 19 ወረርሽኝና የጦርነቱ ሁኔታ የቱሪስት ፍሰቱ እንዲቀንስ ማድረጉን ነው።
ባሳለፍነው በጀት ዓመት ከቱሪዝም ዘርፍ ምንም አይነት የውጭ ምንዛሬ እንዳልተገኘ የቱሪዝም ኢትዮጵያ መረጃ ያሳያል።

የቱሪዝም ኢትዮጵያ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ፍጹም ካሳሁን ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ የቱሪዝም ገቢ ከተለያዩ አገራት ከሚመጡ ጎብኚዎች የሚገኝ በመሆኑ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ እና የአገሪቱ አለመረጋጋት ከዘርፉ ገቢ እንዳናገኝ ተጽዕኖ አሳድሯል።
ከቱሪዝም ዘርፍ በ2030 እንደ መንግሥት የታቅደው የ10 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ሲሆን፣ አመታዊ የጎብኚዎች ቁጥርን ደግሞ 7.2 ሚሊዮን ማድረስ ነው።
በዚህም የታሰበውን ያህል ትንሽ የሚባል ቁጥር እንኳን ጎብኚ ባለመኖሩ ይህን ያህል ገቢ አለ ለማለት አይቻልም ሲሉ ፍጹም ጠቁመዋል።

ጎብኚ ከሌለ የቱሪዝም ገቢ ሊኖር እንደማይችል ይታወቃል። አንድ ቱሪስት ሲገባ ለ11 ሰው የሥራ ዕድል ይፈጥራል ተብሎ ይታሰባል። እንደዚህ አይነት ዓለም ዐቀፍ ችግሮች ሲከሰቱ የአገር ውስጥ ቱሪስቶችን ማበረታት ያስፈልጋል የሚሉት ፍጹም፣ ለዚህ ማበረታቻ ይሆን ዘንድ የሚጎበኙ ቦታዎች ባሉበት አካባቢ ያሉትን ሆቴሎች የማስከፈት እና የመቆጣጠር ሥራ ያስፈልጋል።

አጠቃላይ እንደ አገርም ሆነ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ በቱሪዝም ዘርፉ ላይ በጣም ከፍተኛ ጉዳት ያስከተለው ኮቪድ 19 ወረርሽኝ መሆኑን ፍጹም አንስተዋል። በዚህም ባሳለፍነው 2013 ላይ እዚ ግባ የሚባል የቱሪስት ቁጥር ማግኘት አልተቻለም። በጣም አነስተኛ ቁጥር ያለው ቱሪስት ነው የመጣው ሲሉ ገልጸዋል።

የመስቀል በዓል ኃይማኖታዊ መሠረቱ ምንድን ነው?
የመስቀል በዓል ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀል ከተቀበረበት ተቆፍሮ ከመገኘትና መስቀሉ ግብጽ ቆይቶ ከዚያም ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ ግሽን አምባ ከመቀመጡ ጋር ቀጥተኛ ቁርኝት ቢኖረውም፣ በኢትዮጵያ የተለያዩ ብሔረሰቦች በየራሳቸው ባህልና አኗኗር ያከብሩታል። መስቀል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተ ክርስትያን ዓመታዊ ኃይማኖታዊ በዓል ነው። እየሱስ ክርስቶስ በሮማውያኑ የተሰቀለበት እውነተኛው መስቀል በንግስት እሌኒ አማካይነት እንደተገኘ ይታመናል። ኃይማኖታዊ ተረኮች በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት ሮማዊቷ ንግስት እሌኒ መስቀሉን የት እንደሚገኝ በሕልሟ በራዕይ እንደተገለጠላት ታሪክ ይነግረናል።

ንግስት እሌኒ የኢየሩሳሌምን ሰዎች እንጨት እንዲሰበስቡ ካዘዘች በኋላ ኹሉንም እንጨቶች አንድ ላይ በመለኮስ እንዲነድ አደረገች። ከነደደው እንጨት የተነሳው ጭስም መስቀሉ የተቀበረበትን ቦታ ለማመልከት እንደረዳቸው የተለያዩ ቃላዊ ተረኮች ይገልጻሉ። የመስቀል ክብረ በዓል በኢትዮጵያ ኃይማኖታዊ በዓል ተደርጎ ይወሰዳል። ምክንያቱም በዋናነት እየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት ሙሉ መስቀል (አንዱ ቁራጭ ግማደ መስቀሉ ነው ሲባል የነበረ ቢሆንም፣ በቅርብ ጊዜ በግሸን ከተገኘ የጥንት መዛግብት ላይ ተመሳክሮ ሙሉው መሆኑ ይፋ ተደርጓል) ወደ ኢትዮጵያ እንደመጣ እና በአምባ ግሸን ተራሮች ውስጥ እንደተቀመጠ ስለሚታመን ነው።

ይህ ኃይማኖታዊ በዓል በተለይ በደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት በሚኖሩ ልዩ ልዩ ብሔረሰቦች የሚጀመረው ቀደም ብሎ ሲሆን፣ ለበዓሉ አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን አስቀድመው ይዘጋጃሉ።

የመስቀል በዓል አከባበር በአዲስ አበባ?
የመስቀል በዓል በመስቀል አደባባይ በሺሕዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በቀለማት ያሸበረቁ አልባሳትን ለብሰው፣ የተለያዩ መንፈሳዊ መዝሙሮችን እየዘመሩ፣ ችቦዎችን ሰብስበው በጋራ በማብራት ከዋዜማው ጀምሮ በድምቀት ይከበራል።
የውጭ አገር ዲፕሎማቶችና ቱሪስቶች የሚታደሙበት ይህ መንፈሳዊ በዓል፣ የፌደራል ፖሊስ ባንድ ትርዒትና በዘመናዊ መሣሪያ የታገዘ ሙዚቃ ያቀርባል።

መስከረም 16 አመሻሹ ላይ ችቦዎቹ ከመለኮሳቸው በፊት ለደመራ የሚሆን ችቦ አብዛኛው የበዓሉ ታዳሚ ወደ መስቀል አደባባይ ይዞ ይመጣል። ከተለያየ አካባቢ የመጡ የኃይማኖት መሪዎች ከበሮ በመምታት፣ ያጌጡ መስቀሎችንና መቋሚያዎችን በማወዛወዝ እያሸበሸቡ ከሕዝቡ ጋር ተሰብስበው ለችቦ ማብሪያ የሚሆኑ የተጌጡ አልባሳትን በማድረግ የማስዋብ እና ጧፍ የማብራት ሥነ-ስርዓት ከዝማሬ ጋር ይደረጋል። የተለኮሰው የችቦ ክምር ነድዶ ካበቃ በኋላ ተሳታፊዎቹ ክሰሉን ወይም አመዱን በግንባራቸው ላይ የመስቀል ቅርጽ በማድረግ ይቀቡታል። የደመራው እሳት ፍም እና የተቃጠለው ችቦ የወደቀበት አቅጣጫም የራሱ የሆነ ኃይማኖታዊ ትርጉም ይሰጠዋል።

ይህ ኃይማኖታዊ በዓል በዓለም ዐቀፍ የቅርስ መዝገብነት በዩኔስኮ የተመዘገበ ሲሆን፣ ይህንን በዓሉን ለመታደም በርካታ ጎብኚዎች ከተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ይመጣሉ።
በኦርቶዶክስ ክርስትያኖች ዘንድ የመስቀል በዓል ከደመራ ከመስከረም 16 ዋዜማ ጀምሮ አስከ ዋናው በዓል መስከረም 17 ድረስ የሚከበር ነው።

የቱሪስቶች ጉዞ ወደ ኢትዮጵያ
በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ በሚከበረው የመስቀል ደመራ በዓል ላይ ቱሪስቶች የክብረ-በዓሉ ዋና ተሳታፊ ናቸው። ቱሪስቶቹ ከልዩ ልዩ ቤተክርስትያኖች የተውጣጡት የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች እና በካህናት የተዋቀሩ የመዘምራን ቡድኖች ኃይማኖታዊ መዝሙሮችን ሲያቀርቡ እና አደባባይ ላይ የተተከለውን ግዙፍ ችቦ ሲለኮስ ያለውን ድባብ ለመመልከት የሚመጡ ናቸው።

በኢትዮጵያ ውስጥ እጅግ ደማቅ ከሆኑት የአደባባይ በዓላት አንዱ የሆነው መስቀል ለብዙ ሺሕ ዓመታት ሲከበር ቆይቷል። በዓሉ ቱሪስቶችን ከመሳቡም በላይ በኢትዮጵያ ያለውን የቱሪዝም ዕምቅ አቅም ለማሳወቅና አገርን ለዓለም ለማስተዋወቅ አንዱ መንገድ ነው።
እንደ መስቀል ያሉ ኃይማኖታዊ ክብረ-በዓላት ኢትዮጵያውያን በጋራ ሆነው የሚያከብሯቸው ስለሆነ እርስበርስ ለመተሳሰር እና የየራሳቸውን ባህልና ትውፊት ለማስተዋወቅ ያገለግላል።
የበዓሉ ዕለትም ሆነ በዋዜማው የሚከናወኑ ባህላዊ ክዋኔዎች እና የደመራ ሥነ-ስርዓት ወጣቶችና ሕጻናት በዘመን የተፈተነና የዳበረ ዕውቀት የሚያገኙበት ነው።

2013 ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እጅግ አስከፊ ዓመት ነበር። ከተለያዩ የዓለም አገራት ጋር ያሉ ውዝግቦችና ዓለም ዐቀፍ ውጥረት፣ የታዋቂው ዘፋኝ እና አክቲቪስት ሀጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ የነበረው ከፍተኛ ፖለቲካዊ አለመረጋጋት፣ከ ህወሓት አመራሮች ጋር የፌደራል መንግሥቱ ያለፈበት የፖለቲካ ፍትጊያ፣ የ COVID-19 መምጣት እና ተዛማጅ የመንግሥት ገደቦች የቱሪስት ፍሰቱን ቀንሰው የአገሪቱን ኢኮኖሚ ተፈታትነዋል።

ልክ እንደሌላው ዓለም ሁሉ፣ ብሔራዊ እና ዓለም ዐቀፍ የጉዞ ገደቦች የኢትዮጵያን የቱሪዝም ዘርፍ አዳክመዋል። የሆቴሎች፣ የጉብኝት ኦፕሬተሮች፣ አየር መንገዶች እና ሌሎች ተዛማጅ ንግዶች ውስጥ 88 በመቶው ያህል በመዘጋቱ ችግሮቹ የበለጠ ዘርፉ ላይ ጎልተው ታይተዋል።
በአዲስ አበባ ኮቪድ -19 ተከስቶ በነበረ ወቅት ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑት ሆቴሎች በከፊል ተዘግተው ነበር። ከዚህም ገበያው ለማገገም የተወሰነ ጊዜ ወስዶበት ነበር።
በዓለም ደረጃ ሲታይ የቱሪዝም ሴክተር እንቅስቃሴ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለና ለአገራት ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚዊ ፖለቲካዊ ዕድገት አዎንታዊ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ጥናቶች ያመለክታሉ።

መንግሥታትም ይህንን እውነታ በመረዳት በየአገሮቻቸው ያለው የሴክተሩን እንቅስቃሴ ከማጎልበት ባሻገር ከሌሎች አገሮች ጋር በቱሪዝም ዘርፍ ያላቸውን ትስስርና አጋርነት በማጠናከር ላይ ይገኛሉ። ከዘርፉ የሚያገኙትንና ሊያገኙ የሚችሉትንና ጠቀሜታ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ በማጥናት፣ ተጨባጭ መረጃ በማደራጀትና የጠራ ስትራቴጂና ዕቅድ በማዘጋጀት ወደ ተግባር የገቡና በሒደቱም ተጨባጭ ውጤት በማስመዝገብ ከሴክተሩ የሚገኘውን ጥቅም በማሳደግ ላይ እንደሚገኙ አገራት ይናገራሉ።

የዓለም ዐቀፍ የቱሪዝም ሁኔታን በተመለከተ፣ በአሁኑ ወቅት በፍጥነት እያደጉ የሚገኙ ዘርፎች አንዱ ሲሆን፣ የዓለም ዐቀፉ የቱሪዝም ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው የቱሪስቶች ቁጥር በፈረንጆቹ አቆጣጠር 1950 ከነበረበት የ25 ሚሊዮን ቱሪስት ፍሰት፣ በ1980 ወደ 278 ሚሊዮን፣ እንዲሁም በ2013 ወደ 1087 ደርሷል። የድርጅቱ ትንበያ እንደሚያሳየው ከሆነ ከ2010 እስከ 2030 በየዓመቱ በአማካይ የቱሪስት ፍሰቱ 3.3 በመቶ እንደሚያድግና በ2030 ወደ 1.8 ቢሊዮን ይደርሳል ተበሎ የሚጠበቅ መሆኑን ነው።
ይህ ዕድገት በአህጉራት ደረጃ ሲታይ የአውሮፓ አገራት ከፍተኛ የቱሪስት ፍሰት ድርሻን ቢወስዱም፣ የእስያና ፓስፊክ አገራት የ6.2 በመቶ አማካይ እድገት አስመዝግበዋል።

ወደ አገራችን የሚመጡ ቱሪስቶች ቁጥርም በባለፉት አመታት ከፍተኛ ቁጥር ሲያስመዘግብ ቆይቷል። በፈረንጆቹ 2016 ወደ ኢትዮጵያ የገበት የውጭ አገራት ቱሪስቶች ቁጥር 918 ሺሕ ሲሆን፣ ከዘርፉ የተገኘው ገቢም 3.4 ቢሊዮን ዶላር እንደነበር በማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ የተጠና ጥናት ያሳያል።


ቅጽ 3 ቁጥር 151 መስከረም 15 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com