የእለት ዜና

በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልላዊ የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም ተጠየቀ

በኢትዮጵያ ሰኔ 14/ 2013 ምርጫ ሲካሄድ፣ በጸጥታ ችግር ምክንያት መጀመሪያ ወደ ጳጉሜ 1 ቀን 2013 ከዚያም ወደ መስከረም 20 ቀን 2014 ተራዝሞ የነበረውን የቤኒሻንጉል ክልል ምርጫ አሁንም መካሄድ እንደማይቻል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማሳወቁን ተከትሎ፣ የቦሮ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ መግለጫ ሰጥቷል።

ፓርቲው መስከረም 12 ቀን 2014 ባወጣው መግለጫ፣ ከመስከረም 25 ቀን 2014 በኋላ የክልሉ ገዥ ፓርቲ በሕዝብ ሳይመረጥ ክልሉን ማስተዳደር አይችልም ብሏል።
በድጋሜ የሕገ-መንግሥት ማሻሻያ ማድረግ እና የሥልጣንን ጊዜ ማራዘም አይቻልም ያለው የቦሮ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የመፍትሄ አማራጮች ያላቸውን አቅርቧል።

በዚህም ክልላዊ የሽግግር መንግሥት መመስረትን እንደ ቀዳሚ አማራጭ አስቀምጧል። በክልሉ ሕገ-መንግስት አንቀጽ 55(3) መሰረት የክልሉ ምክር ቤት የሥራ ዘመን የተገባደደ በመሆኑ፣ ምርጫ ተደርጎ አዲስ ክልላዊ መንግሥት እስኪቋቋም ድረስ የክልሉ ገዥ ፓርቲ እና በክልሉ የሚንቀሳቅሱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች በጋራ ክልላዊ የሽግግር መንግሥት እንዲመሰርቱ ጥሪ አቀርቧል።

ይሁን እንጂ፣ የቤንሻጉል ክልል ብልጽግና ፓርቲ ከቦሮ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ የቀርበውን ጥያቄ ውድቅ የሚያደርግ መግለጫ ማውጣቱን የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት መብራቱ አለሙ (ዶ/ር) ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ገዥው የክልሉ መንግሥት፣ “እናንተ ያቀረባችሁት አማራጭ ተቀባይነት የለውም እኛ በጉልበት እንቀጥላለን” የሚል መግለጫ አውጥቷል፤ ይህም ኢ-ህገ መንግሥታዊ ስለሆነ ፓርቲያችን አጥብቆ ሲያወግዘው ነበር ብለዋል። የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ያወጣውን መግለጫ ተከትሎ የእኛም ፓርቲ ምላሽ የሚሆን መግለጫ በድጋሜ አውጥቷል ሲሉ ገልጸዋል።

በዚህም የቦሮ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲን በተመለከተ የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ፣ ከጡት አባቱ የወረሰውን የፖለቲካ ሴራ በመጠቀም የክልላችንን ሕዝብ ወደ ግጭትና ብጥበጥ ለመምራት የተዘጋጀ ነው ሲል በመግለጫው አትቷል።
የቦሮ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ መስከረም 13 ቀን 2014 ድጋሜ ባወጣው መግለጫ፣ በክልሉ እስካሁን በዘለቀው ሞትና መፈናቀል የገዥው ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች እጃቸው አለበት በሚል የፓርቲው አባላት እስር ላይ እንደሚገኙ ገልጾ፣ ፓርቲው ከወላጅ አባቱ ከህወሓት-ኢሕአዴግ የወረሰው በሰበብ ሥልጣን ላይ የመሠንበት ፍላጎት፣ ፍረጃና የማጠልሸት ፖለቲካ ነው ሲል ገልጿል።

የቦሮ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ በመግለጫው አክሎም፣ ገዥው ፓርቲ የጸጥታ ችግሩን ተገን በማድረግ የመንግሥት እና የሕዝብ ንብረት ዘረፋ ውስጥ የገቡ በተለይም በማዕድን ሀብት የዘረፋ፣ የሕዝብ ስኳርና ዘይት የሠረቁ፣ ሕገ ወጥ ሲሚንቶ ንግድ ውስጥ የተዘፈቁ ሌቦች ከሥልጣን ቢነሱ የሚከተላቸውን ስለሚያውቁ ፈርተው ነው ይላል።

የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም የቦሮ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ብቻ ሳይሆን የቤኒሻንጉል ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ ተወያይተው የተስማሙበት መሆኑንም ነው መብራቱ አለሙ (ዶ/ር) ለአዲስ ማለዳ የጠቆሙት።
በክልሉ ለሚፈጠረው ማንኛውም ችግር ተጠያቂ የምናደርገው የክልሉን የብልጽግና ፓርቲ ነው ያሉት መብራቱ፣ ተጨማሪ የሥልጣን ጊዜ ብንሰጠው ችግሩን ይበልጥ እንዲባባስ መፍቀድ ነው ብለዋል።

በመጨረሻም፣ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት፣ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት እና ለኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አቤቱታ አቅርበው ምላሽ እየተጠባበቁ መሆኑን ገልጸው፣ ይህም ሆኖ ምላሸ ካላገኘን ሕገ-መንግሥቱ ለይስሙላ እንደተቀመጠ ቆጥረን ጥያቄችንን ጠቅላይ ፍርድ ቤት ድረስ በማቅረብ ፍርድ ቤቱ የሚሰጠውን ወሳኔ እንቀበላለን ብለዋል።

በ2007 የተመረጠው የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ምክር ቤት የሥልጣን ጊዜው በ2012 ያበቃ የነበረ ቢሆንም፣ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ምርጫ ማካሄድ ባለመቻሉ ሥልጣኑ እስከ መስከረም 24 ቀን 2014 ለአንድ ዓመት መራዘሙ ይታወቃል።


ቅጽ 3 ቁጥር 151 መስከረም 15 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!