የእለት ዜና

ተሰጥኦና ክህሎት ያላቸውን ሰዎች ከድርጅቶች ጋር የሚያገናኝ መተግበሪያ ይፋ ሆነ

ተሰጥኦና ክህሎት ብሎም የመፍጠር አቅም ያላቸው ባለሙያዎችን እና ግለሰቦችን እርስበርስ ወይም ተፈላጊና ፈላጊን የሚያገናኝ ‹ልዩ ታለንት› የሚባል መተግበሪያ ይፋ ተደረገ።
በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ማለትም በፊልም፣ በሥነ ግጥም፣ በሥነ ጽሑፍ፣ በሥነ ስዕል፣ በሙዚቃ፣ በቴከኖሎጂና በመሳስሉት ልዩ ልዩ ተሰጥኦና ክህሎት ያላቸውን ሰዎች በአንድ ላይ በማሰባስብ መያዝ የሚያስችል መድረክ የሚፈጥር መተግበሪያ መሥራት መቻላቸውን ሲሳይ መኳንንት የተባሉ የፈጠራ ባለሙያው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ከኹለት ዓመት በፊት ሐሳቡ እንደነበራቸው የገለጹት ባለሙያው፣ ውጥናቸውን በድረ-ገጽ (ዌብሳይት) ወይም በአጭር የጽሑፍ መልዕክት ለመሥራት ቢያስቡም፣ በዚህ መንገድ አዋጭ ስላልሆነ ወደ መተግበሪያ ቀይሬዋለሁ ብለዋል።

ተጠቃሚዎች መተግበሪያውን ከፕሌይ ስቶር በማውረድ ስልካቸውና ኮምፒዩተራቸው ላይ በመጫን መጠቀም ይችላሉ። በዚህም ስልክ ቁጥራቸውን፣ ኢሜላቸውን እንዲሁም የሚፈለጉትን የሙያ ዘርፍ በመሙላት ከተለያዩ ባለሙያዎችና ድርጅቶች ጋር በቀላሉ መገናኘት ይችላሉ ሲሉ ነው የገለጹት።

በኢትዮጰያ እስካሁን ተሰጥኦና ክህሎት ያላቸው ብዙ ሰዎች ችሎታቸውን ለማሳየትና ራሳቸውን ለመሸጥ ሲቸገሩ መኖራቸውን ጠቁመው፣ ከዚህ በኋላ ግን ልዩ ታለንት መተግበሪያ ላይ ራሳቸውን የሚገለጽ መረጃ በመሙላት ያለምንም ክፍያ ከሚፈልጉት አካል ጋር መገናኘትና ችሎታቸውን ማሳየት ይችላሉ ብለዋል። ዋና ዓላማዬ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ሰዎች ተጎጂ ሲሆኑ ስላየሁ ይህን ለማስተካከል ስል ነው የሠራሁት የሚሉት ሲሳይ መኳንንት፣ ገቢ የሚገኘው የተለያዩ ድርጀቶች በልዩ ታለንት ራሳቸውን ለማስተዋወቅ በሚከፍሉት የማስታወቂያ ክፍያ እንጂ ከግለሰቦች አይደለም ብለዋል።

ይህን ለመሥራት ምንም ዓይነት ኮምፒዩተር ነክ ትምህርት አልተማርኩም፤ ግንዛቤ ለሌለው ሰው እንዲህ ዓይነት አዲስ አግልግሎት የሚሰጥ መተግበሪያ መሥራት የማይሆን ነገር ቢመስልም፣ በድፍረት እና እችላለሁ በሚል ስሜት ሠርቸዋለሁ ይላሉ። አያይዘውም መተግበሪያውን በሌላ ባለሙያ ለማሠራት አስበው 60 ሺሕ ብር የተጠየቁ በመሆኑ በራሳቸው ለመሥራት እንደወሰኑ ገልጸዋል። በዚህም ሥራው በጣም ወስብስብና አሰለቺ በመሆኑ ከሰባት ወራት ድካም በኋላ ጳጉሜ 1/2013 ጨርሰው ለተጠቃሚዎች ይፋ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
አሁን ላይ የመረጃ ማዕከል (ሰርቨር) የሌላቸው በመሆኑ ዋጋውም እስከ 200 ሺሕ ብር የሚጠይቅ ስለሆነ፣ ለጊዜው የግለሰቦችን መረጃ መተግበሪያው ወስጥ የሚሞሉት ሰዎችን በአካል በመጠየቅ ነው።

የመረጃ ማዕከሉ ሲኖራቸው ግን ሰዎች ስለራሳቸው መረጃ መተግበሪያው ውስጥ ማስቀመጥ ይችላሉ። በዚህም አሁን ላይ ተደራሽነታቸው አዲስ አበባ ላይ ብቻ መሆኑን ገልጸዋል። ወደፊት ሰርቨር ሲያስገጥሙ ተጠቃሚዎች ከየትኛው የኢትዮጵያ ጫፍ ብሎም በዓለም ዙሪያ በዚህ ዘርፍ ያሉ ግለሰቦችና ባለሙያዎች እርስበርስ መገናኘት እንደሚችሉ ነው የገለጹት።

የመረጃ ማዕከልን በተመለከተ የጎግልን ሰርቨር ለመጠቀም ጎግል የተጠቃሚ ቁጥር ገደብ ያስቀመጠ በመሆኑ፣ የተጠቃሚዎች ቁጥር ከገደብ በሚያልፍበት ጊዜ ሌላ አሰልች የሆነ ፎርም እንድንሞላ ስለሚጠይቀን ከቻልን የራሳችንን እንገዛልን ወይም ካገኘን እንከራያለን ሲሉም ይገልፃሉ።
እገዛ በሚያስፈልጋቸው ዙሪያ ከሚመለከታቸው የመንግሥት ኣካላት ፊት ቀርበው ቢጠይቁም በጎ ምላሽ እንዳላገኙ ገልጸው። በየጊዜው የሚሠሩ ቴክኖሎጂዎች የሰዎችን ሕይዎት ለማቅለል ካላቸው ፋይዳ አንፃር፣ እንዲሁም የፈጠራ ባለሙያዎችን ለማበረታታት መንግሥት እገዛ ለሚያስፈልጋቸው ተገቢውን እገዛ መስጠት አለበት ብለዋል።

በመጨረሻም፣ አሁን ላይ በገንዘብ፣ በማቴሪያል እንዲሁም በአይሲቲ ብቁ የሠው ኃይል ስለሌለ እና የሚጠይቀውም ክፍያ ውድ በመሆኑ ቋሚ የሆነ የሥራ ማዕከል ከፍተን በተደራጀ መልኩ ሥራ ባንጀምርም ወደፊት ግን ይህን ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት እናደርጋለን ብለዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 151 መስከረም 15 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com