የእለት ዜና

የኮንስትራክሽን ባለሙያዎች በአሸዋ ዕጥረት ምክንያት ሥራ ለማቆም መገደዳቸውን ተናገሩ

በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የኮንስትራክሽን ባለሙያዎች በአሸዋ አቅርቦት ዕጥረት ምክንያት ሥራ ማቆማቸውን ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።
አሸዋ ሲጭኑ የነበሩ ሹፌሮች ወንዝ ሒደው እንዳይጭኑ በመከልከላቸው የአሸዋ አቅርቦት ዕጥረት እንዳጋጠማቸው እና ከአንድ ሳምንት በላይ ለሚሆን ጊዜ ሥራ ማቆማቸውን ነው የኮንስትራክሽን ባለሙያዎች ለአዲስ ማለዳ የጠቆሙት።
የግንባታን ሥራ ለማከናወን አሸዋና ሲሚንቶ ዋነኛውን ድርሻ የሚይዙ ግብዓቶች ናቸው የሚሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፣ የአሸዋ አቅርቦቱ ዕጥረት ካልተፈታ የጀመሯቸውን ግንባታዎች እንኳን መጨረስ እንደማይችሉ አመላክተዋል።

በአሸዋ አቅርቦቱ ዕጥረት ምክንያት የኮንስትራክሽን ባለሙያዎቹ ለዘጠኝ ተከታታይ ቀናት ሥራቸውን መሥራት ባለመቻላቸው የግንባታ ዕቅዳቸው እንደተጓተተባቸውና የጊዜ ብክነት እንዳገጠማቸው ነው አዲስ ማለዳ ከምንጮቿ መረዳት የቻለችው።
የኮንስትራክሽን ባለሙያዎቹ የአሸዋ አቅርቦት ዕጥረት መከሰቱ የብሎኬት ዕጥረትንም እንዳስከተለባቸው የገለጹ ሲሆን፣ የግንባታ መሠረቱ ተሠርቶ ካለቀ በኋላ በቅድሚያ የሚያስፈልገው ከግርፍ ሥራው ይልቅ የብሎኬት ድርደራ በመሆኑ፣ የብሎኬት ዕጥረቱ ሥራ እንዲያቆሙ እንዳስገደዳቸው ነው የገለጹት።

ቅሬታ አቅራቢዎቹ፣ ምንም እንኳን ኹሉም የኮንስትራክሽን ባለሙያዎች ሙሉ ለሙሉ ሥራ እንዳላቆሙና አንዳንዶች ቀድሞ በነበራቸውን የአሸዋና የብሎኬት አቅርቦት በሥራ ላይ እንዳሉ የገለጹ ቢሆንም፣ ነገር ግን አሁን ላይ በእጃቸው ያለው አቅርቦት እያለቀ በመሆኑ በቅርቡ ችግሩ ካልተፈታ ሥራቸውን መቀጠል እንደማይችሉ ነው የገለጹት።

የኮንስትራክሽን ዕቃ በማቅረብ ሥራ የተሠማሩት የአዲስ ማለዳ ምንጮች፣ “አሸዋ በማጣታችን ብዙ ነገር ነው ያጣነው። የቀን ሠራተኞች ኹሉ ሥራ አቁመዋል፤ ካልሰሩ መብላት እንደማይችሉ ይታወቃል። ሥራው ቁሟል፤ የአሸዋው ሲገርመን ጠጠርም ተዘግቷል” ሲሉ ነው የገለጹት።
ቅሬታ አቅራቢዎቹ በዚህ ችግር ምክንያት እየተጎዱ ያሉት የኮንስትራክሽን ባለሙያዎቹ ብቻ ሳይሆኑ በዘርፉ የተሠማሩና የቀን ሥራ በመሥራት ኑሯቸውን የሚመሩ ግለሰቦችም ጭምር መሆናቸወን ገልጸው፣ የተፈጠረውን የአሸዋ ዕጥረት ለመቅረፍ ርብርብ ሊደረግ ይገባል ብለዋል።
የአቅርት ችግሩ የገጠመን ሹፌሮች አሸዋ እንዳይጭኑ ስለተከለከሉ ነው የሚሉት የኮንስትራክሽን ባለሙያዎቹ፣ “ሹፌሮችን ጫኑልን ስንላቸው፣ የማዕድን ማዉጣት ሥራ እየተከናወነ በመሆኑ ለመጫን ተከልክለናል’’ እንዳሏቸውም ነው የጠቆሙት።

ቅሬታ አቅራቢዎቹ አያይዘዉም፣ የግንባታ ሥራ ለግንባታ ባለሙያዎቹ፣ በስሩ ለሚሳተፉ የቀን ሠራተኞች፣ ግንባታውን ለሚያስገነቡ ግለሰቦች፣ እንዲሁም ለአገሪቱ ዕድገት የሚጫወተውን ሚና የሚመለከተው አካል ግምት ውስጥ በማስገባት፣ የጭነት አገልግሎቱ እንዳይከናወን መንስኤ ነው የተባለውን የማዕድን ማውጣት ሥራን በማያስተጓጉል መልኩ አሸዋ የምናገኝበትን እና የተቋረጠው ሥራችንን የምንቀጥልበት መፍትሔ ሊሰጠን ይገባል በማለት አሳስበዋል።

አዲስ ማለዳ የኮንስትራክሽን ባለሙያዎች ገጠመን ያሉት ችግር ለማረጋገጥ አሸዋ በመጫን ለኮንስትራክስን ባለሙያዎች ከሚያስረክቡ ሾፌሮች ጋር ቆይታ ያደረገች ሲሆን፣ ሾፌሮቹም ችግሩ እንዳለ ገልጸው፣ አሸዋ ለመጫን ያልቻሉበት ምክንያት የማዕድን ሚኒስቴር የማዕድን ግብዓትን ከመጨመር አኳያ ለ2014 ያለመውን ዕቅድ ለማሳካት ማዕድን በማዉጣት ተግባር የተሠማሩ ሠራተኞች በየወንዙ ሥራ ላይ በመሆናቸው ነው ብለዋል።

አሸዋ ስንጭንባቸው በነበሩት በሁሉም ቦታዎች እንዳንጭን ተከልክለን ነበር የሚሉት ሾፌሮቹ፣ የማዕድን ማስጫኛ ወረቀት ያልያዘ ሾፌር መጫን እንደማይችልም ተናግረዋል።
ሾፌሮቹ አሸዋ ሲያመጡ የነበረው ከመተሃራ፣ መቂ፣ አዋሽና ከሌሎችም ቦታዎች እንደነበር የገለጹ ሲሆን፣ አሁን ላይ ሁሉም ቦታዎች እንደተዘጉ ነው የጠቆሙት።

አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ላይ አስተያት ለመቀበል ወደ የማዕድን፣ነዳጅና ተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር በተደጋጋሚ ስልክ ብትደዉልም የሚመለከታቸው አካላት ምላሽ ለመስጠት ፍቃደኛ ስላልሆኑ ሐሳባቸውን ማካተት አልቻለችም።


ቅጽ 3 ቁጥር 151 መስከረም 15 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com