የእለት ዜና

ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ ውስኪ ማምረት ጀመረ

ብሔራዊ አልኮልና አረቄፋብሪካ፣ ብሔራዊ ብላክ ዲር ውስኪ (National Black Deer Whisky) የተሰኘ አዲስ ምርት ከነሐሴ ወር 2013 ጀምሮ ማምረት መጀመሩን ለአዲስ ማለዳ አሳውቋል።
ብሔራዊ ብላክ ዲር ውስኪ ሌሎች ዓለም ዐቀፍ ታዋቂ የውስኪ ምርቶች የሚያሟሉትን መስፈርት ያሟላ በመሆኑ የአልኮል መጠኑ በተመሳሳይ 40 በመቶ መሆኑ ተገልጿል።

ምርቱ በአንድ ሊትር ጠርሙስ የሚመረት ሲሆን፣ ማምረት ከተጀመረ እስካሁን 50ሺሕ ገደማ ጠርሙስ ማምረት መቻሉንየገበያ ጥናትና ማስፋፊያ ቡድን መሪ የሆኑት አስራት ታዬ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
የምርቱ የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ታክስን ጨምሮ 650 ብር ሲሆን፣ በጅምላ ለሚገዙና ለወኪል አከፋፋዮች ከአስራ አምስት ብር ጀምሮ ቅናሽ እንደሚደረግ አስራት ጨምረው ገልጠዋል።
ምርቱንለማምረት አስፈላጊ ከሆኑ ጥሬ ዕቃዎች ውስጥ አብዛሃኛውቹ ከአገር ውስጥ የሚገኙ ሲሆን፣ ጥቂቶቹ ከውጭ አገር የሚመጡ ናቸው ተብሏል።

ምርቱን ለማምረት የተፈለገበት ዋናው ዓላማ በውጭ ምንዛሬ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ውስኪዎችን በሚመጥን ጥራት እና ተመጣጣኝ ዋጋ ለገበያ የሚቅረብ ውስኪአምርቶ የአገር ውስጥ ፍላጎትንለማርካት ነው። ከዚህ በተጨማሪም ለውጭ አገራት በተለይምለጎረቤት አገራት ምርቱን ለማቅረብ ጥረት እየተደረገ ነው ተብሏል።

ደቡብ ሱዳን ነባር ምርቶችን በስፋት እንደምትወስድ የገለጹት አስራት ታዬ፣ አሁንም የምርቱን ናሙና ወስዳለች ብለዋል። በተጨማሪምአሁን ላይ በሚመረተው የምርት መጠን የአገር ውስጥ ፍላጎትን ማሟላት የተቻለ በመሆኑ ወደእስራኤል፣ ጀርመንና አሜሪካ ምርቱን ለመላክ ሐሳብ መኖሩን የቡድን መሪው ተናግረዋል።

እስካሁን ባለው ሒደት ብዙ ደንበኞች ብሔራዊ ብላክ ዲር ውስኪ በጥራቱ ውጭ አገር ተመርተው ወደ ኢትዮጵያ ከሚገቡ ውስኪዎች ጋር ተመሳሳይ መሆኑን እየተናገሩ እንደሆኑ አስራት ተናግረዋል።አክለውም በምርት ማሸጊያው ልዩነትና ሳቢነት፣ እንዲሁም በመሸጫ ዋጋው ተመጣጣኝነት ላይ በርካታ አስተያየቶችመገኘታቸውንአንስተዋል።

ከኹለት ዓመት በላይ በፈጀ ጥናትና ምርምር፣ እንዲሁም ተገቢ የማምረት ዝግጅት በአገር ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ በከፍተኛ ጥራት መመረት የጀመረው ውስኪ፣ዘመናዊ የአስተሻሸግ ደረጃ መስፈርትን አሟልቶ የቀረበ እናሥራውም ሙሉ በሙሉ በአገር ውስጥ የሰው ኃይል የተከናወነ በመሆኑ ተፈላጊነቱ እየጨመረ መምጣቱ ተገልጧል። የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ውስኪ የሚመረተው አዲስ የማምረቻ ፋብሪካ ተገንብቶ ሳይሆን በነበረው የማምረቻ ፋብሪካ ነውም ተብሏል።

ፋብሪካው አዲስ ምርት ማምረት መጀመሩ በአሁኑ ወቅት ለተወሰኑ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ፈጥሯል ያሉት አስራት ታዬ፣ የምርት መጠናችን ሲጨምርና የገበያ ትስስሩ እያደገ ሲሄድ አሁን ካለው በላይ ለበርካታ ዜጎች የተሻለ የሥራ ዕድል ይፈጥራል ብለዋል።
ብሔራዊ ብላክ ዲር ውስኪ አዲስ እንደመሆኑ መጠን የውጭ አገራትን ምርት ሲጠቀሙ የነበሩ ደንበኞችን ከምርቱ ጋር ለማስተዋወቅ እና ለማላመድ ከፍተኛ ጥረት የሚጠይቅ ሲሆን፣ በአስተሻሸግም ተወዳደሪ ሆኖ መገኘት ተግዳሮት ሊሆን እንደሚችል አስራት ታዬ ለአዲስ ማለዳ አብራርተዋል።

ብሔራዊ አልኮልና አረቂ ፋብሪካ ኢትዮጵያ ውስጥ ለበርካታ ዓመታት የተለያዩ የአልኮል መጠጦችን በማመረት ይታወቃል።


ቅጽ 3 ቁጥር 151 መስከረም 15 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com