የእለት ዜና

ፒያሳ ለሚገኙ የአትክልትና ፍራፍሬ ነጋዴዎች የንግድ ፈቃድ ዕድሳትም ሆነ ምዝገባ ተከለከለ

በአራዳ ክፍለ ከተማ ልዩ ስሙ ፒያሳ አትክልት ተራ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ለሚገኙ የአትክልትና ፍራፍሬ ነጋዴዎች የንግድ ፈቃድ ዕድሳትም ሆነ አዲስ ምዝገባ መከልከሉን የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ምክትል ኃላፊ አከበረኝ ወጋገን ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ በአካባቢው የሚገኙ ነጋዴዎች የንግድ ፈቃዳቸውን ማሳደስም ሆነ አዲስ ማውጣት እንደማይችሉ ተናግረዋል።
ምክንያቱን በውል ያልተረዱ በአትክልትና ፍራፍሬ ንግድ የተሰማሩ ነጋዴዎች ቅሬታቸውን ያቀረቡ ሲሆን፣ አዲስ ማለዳም ጥያቄያቸውን በመያዝ ቢሮውን ጠይቃለች።

የአትክልትና ፍራፍሬ ነጋዴዎች ንግድ ፈቃድ ዕድሳትና ምዝገባ የተቋረጠው በአካባቢው የሚገኙ አብዛኞቹ ነጋዴዎች ወደ ላፍቶ መሄዳቸውን ተከትሎ ከአካባቢው ያልተነሱት መከልከል ስላለበት ነው ሲሉ አከበረኝ ገልጸዋል።
ኃላፊው፣ የአትክልትና ፍራፍሬ የገበያ ማዕከል ከዚህ በፊት በኮሮና ምክንያት ከፒያሳ አትክልት ተራ ወደ ጃንሜዳ መሄዱን እና ቀጥሎ ደግሞ ዘመናዊነቱን፣ ጽዳቱንና ደህንነቱን የጠበቀ የገበያ ማዕከል በመገንባት ወደ ላፍቶ የማዘዋወር ሥራ መሠራቱን አስታውሰዋል።

የከተማዋን የገጽታ ዕድገት ያገናዘበ ነው በተባለለት የገበያ ማዕከል ውስጥ ከሚገኙት ነጋዴዎች ውስጥ 90 በመቶ የሚሆኑት ሕጋዊ የንግድ ሥርዓት የሚከተሉ መሆኑንም አከበረኝ ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።
ቀድሞ በነበሩበት ቦታ 10 በመቶ የሚሆኑት እንኳን ሕጋዊ ሆነው የማይሠሩ ነጋዴዎች የነበሩ መሆናቸውን የገለጹት አከበረኝ፣ በላፍቶ የገበያ ማዕከል የሚገኙት ምንም አይነት ክልከላ አልተደረገባቸውም ብለዋል።

መንግሥት ከፍተኛ ወጪ አውጥቶ የከተማውን ንጽህና እና ጸጥታ ለመጠበቅ፣ እንዲሁም ሕብረተሰቡ ንጹህ ምርት እንዲያገኝ ለማድረግ በሠራው የገበያ ማዕከል መነገድ የነጋዴዎች ግዴታ በመሆኑ ነው በተጠቀሰው አካባቢ ክልከላ የተደረገው ሲሉ ገልጸዋል።
በተያያዘ ዜና፣ በንግድ ቢሮው ሲሰሩ ከነበሩት በርካታ ሥራዎች መካከል ለነዳጅ ማደያዎች ቦታ በመስጠት የሥራ ዕድል ፈጠራ ለማከናወን ያቀደው ሥራ እስከአሁን ወደ ተግባር አለመግባቱን አከበረኝ ጠቁመዋል።

ከዚህ በተጨማሪ፣ ተቋሙ ባደረገው የቁጥጥር ሥራ በከተማዋ የኢኮኖሚ አሻጥር ሲፈጽሙ የነበሩ 1ሺሕ 886 የንግድ ድርጅቶች ላይ የማሸግ እና ከንግድ ሕግ ውጪ ሲሠሩ በተገኙ 657 ድርጅቶች ላይ ደግሞ የንግድ ፈቃዳቸውን የመሠረዝ ዕርምጃ መወሰዱን አከበረኝ ጠቅሰዋል።
የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ 369 መጋዘኖችን የመፈተሽ ሥራ መሠራቱን እና በ20 መጋዘኖች ከፍተኛ የምርት ክምችት በመገኘቱ መጋዘኖቹ መታሸጋቸው የተገለጸ ሲሆን፣ የተከማቹት ምርቶች ደግሞ ለተጠቃሚ እንዲደርሱ ተደርጓል ብለዋል ።

ከዚህ በተጨማሪም ከፍተኛ ወንጀል የፈጸሙ 64 ነጋዴዎች በወንጀል እንዲከሰሡ በማድረግ የተወሰኑት ላይ የእስር ትዕዛዝ እንዲወጣ ተደርጓል ሲሉ አከበረኝ ተናግረዋል።

ተቋሙ የበዓል ወቅት በ31,278 የንግድ ተቋማት ላይ ባደረገው የቁጥጥር ሥራ፣ በ1,967 ንግድ ድርጅቶች ላይ ሕጋዊና አስተዳደራዊ ዕርምጃዎች መወሰዱን የገለጸ ሲሆን፣ ከነዚህም ውስጥ 317 የንግድ ድርጅቶች ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በማድረጋቸው ዕርምጃው የተወሰደባቸው ሲሆን፣ ከ40 በላይ ድርጅቶች ደግሞ በሕገ-ወጥ መልኩ ምርት አከማችተው በመገኘታቸው መሆኑ ታውቋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 151 መስከረም 15 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com