የእለት ዜና

ለመንግሥት እጃቸውን የሰጡት የኦነግ ሸኔ አዛዥ የተለያዩ አካባቢዎችን እየጎበኙ ነው ተባለ

ለመንግሥት እጃቸውን የሰጡት የኦነግ ሸኔ የደቡብ ዞን አዛዥ የነበሩት ጃል ጎልቻ በሠላማዊ መንገድ እየተንቀሳቀሱና የተለያዩ አካባቢዎችን እየጎበኙ መሆናቸውን የኦሮሚያ ክልል የመንግሥት ባለሥልጣናት ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።
እጃቸውን የሰጡት የኦነግ ሸኔ አዛዥ በተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት ከተፈረጀው የህወሓት ቡድን ጋር ሲንቀሳቀሱ የቆዩ ቢሆንም፣ አሁን ላይ በሠላም አቀባበል ተደርጎላቸው ሕዝባቸውን ለመጥቀም እየሠሩ መሆናቸውን ነው የክልሉ ባለሥልጣናት የተናገሩት።

ጃል ጎልቻ ከኦነግ ሸኔ ቡድን ተነጥለው እጃቸውን ለመንግሥት እንደሰጡና ከዚህ ቀደም በሽብርተኝነት ከተፈረጀው የህወሓት ቡድን ጋር በነበራቸው ግንኙነት ምክንያት ምንም አይነት ችግር ሳያጋጥማቸው በነጻነት እየተንቀሳቀሱና በተለያዩ ቦታዎች ጉብኝት እያደረጉ መሆናቸውን የኦሮሚያ ክልል የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ጌታቸው ባልቻ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ኃላፊው አክለውም፣ በሽብርተኝነት ከተፈረጀው የህወሓት ቡድን ጋር የተቀላቀሉ የሸኔ ታጣቂ ኃይሎችን መንግሥት በይቅርታ እንደሚቀበላቸው ያስታወቁ ሲሆን፣ “ጃል ወደ አገሩ ተመልሷል፤ ወደ አገሩ ከተመለሰ ደግሞ የሚያስፈልገውን ሠላማዊ ትግል ማካሄድ ይችላል” ብለዋል።
አዲስ ማለዳ ከኃላፊው የተረዳችው፣ ጃል ጎልቻ ምንም እንኳን ጥቃት ከሚያደርሰው የህወሓት ቡድን ጋር አብረው ሲሠሩ የነበረ ቢሆንም፣ በሠላም እንቀሳቀሳለሁ ብለው ለመንግሥት እጃቸውን የሰጡ ሰው በመሆናቸው ምንም አይነት ጥያቄ ሊነሳባቸው እንደማይገባ እና “ሠላማዊ ትግሉን” መቀጠል የሚችሉ መሆኑን ነው።

በዚህ ወቅት ጃል እጃቸውን ለመስጠት የወሰኑት የኦነግ ሸኔ በፌደራል መንግሥት በሽብርተኝነት ከተፈረጀው ህወሓት ጋር “የጀመረውን ስምምነት ባለመቀበልና ከዚህ በኋላ የኦሮሞ ሕዝብ ትግል በጫካ ሊሆን አይገባም” የሚለውን ውሳኔ በመወሰን መሆኑን ነው ጌታቸው የገለጹት።
በፌደራል መንግሥት በሽብርተኝነት የተፈረጀው ቡድን በመጀመሪያ “አገር ለማተራመስ ሲሞክር እንዲያግዙት ካዘጋጃቸው በአገሪቱ ከሚገኙ ጽንፈኞች መካከል የኦነግ ሸኔ ቡድን ዋነኛው ነበር” በማለት የገለጹት የኮሚኒኬሽን ኃላፊው፣ የጃል ጎልቻ ከቡድኑ የመገንጠል ውሳኔ የህወሓትን የጥቃት ኃይል ያዳክመዋል በማለት ነው ሐሳባቸውን ያስቀመጡት።

ጌታቸው አያይዘውም፣ የኦነግ ሸኔ አዛዥ ከቡድኑ መግለል በኢትዮጵያ ላይ ለሚታየው ጦርነት መዳከም አስተዋጽኦ ቢኖረውም፣ በአገሪቱ ላይ በውጭ አገራት እየደረሰ ያለውን ተጽዕኖ ሊቀንሰው አይችልም ሲሉ ነው አስተያየታቸውን ያስቀመጡት።
ኃላፊው አክለውም በሽብርተኝት የተፈረጀው ህወሓት በሰሜኑ ክፍል ላይ ጥቃት ሲፈጽም የኦነግ ሸኔ ቡድን ሰፊ ድርሻ ይዞ መቆቱን አንስተው፣ ቡድኑ ከዚህ በኋላ ወደ ሠላማዊ ትግል መመለስ እንደሚችልም ነው የተናገሩት።

የጃል እጅ መስጠት በመንግሥት በኩል “ትግሉ ከጫካ ወደ አዳራሽ ይግባ” የተባለውን ጥያቄ በትክክል የሚመልስ፣ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል እየተካሄደ ላለው የሉዓላዊነት ዘመቻ ትኩረት ሰጥተን ለመረባረብ እንድንችል የሚረዳ ነው ሲሉ ኃላፊው ጨምረው ተናግረዋል።
የኦነግ ሸኔ የደቡብ ዞን አዛዥ ጃል ጎልቻ በዚህ ወቅት ከቡድኑ የመገለላቸው ምክንያት “በአገሪቱ ውስጥ እየተካሄደ ያለው ጦርነት አስፈላጊ አለመሆኑን በማመን ነው” ሲሉ የመሰከሩት ጌታቸው፣ ግለሰቡ የወሰዱትን ውሳኔም አበረታተዋል።

በሕግ የተከለከሉ ተግባራትን የፈጸመ ማንኛውም ሰው ከተጠያቂነት ሊያመልጥ የሚችለው በምህረት ሕጉ መሰረት መሆኑን ለአዲስ ማለዳ የገለጹት አንድ የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ባልደረባ፣ በጃል ጎልቻ ጉዳዩ ላይ ለመነጋገር ሰፊ ጊዜ እንደሚያስፈልግ ገልጸው ቀጠሮ ቢሰጡንም፣ በቃላቸው መሰረት ጋዜጣዋ ለኅትመት እስከተላከችበት ጊዜ ድረስ ምላሽ ሊሰጡን አልቻሉም።


ቅጽ 3 ቁጥር 151 መስከረም 15 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com