የእለት ዜና

ጦርነቱ የሕገ-ወጥ ተግባር መሸፈኛ አይደረግ!

በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የተለያየ ስያሜ እየተሰጠው ሲካሔድ በቆየው ጦርነት እስካሁን ብዙዎች ሕይወታቸውን እንዳጡ ይገመታል። እስካሁን በቀጠለበት መንገድ ከተጓዘም ከእስከአሁኑ በላይ ጉዳት እንደሚያስከትል የብዙዎች ስጋት መሆን ከጀመረ ከራርሟል።
ይህ ለብዙዎች ዕልቂትና መፈናቀል እንዲሁም ለበርካታ ንብረት መውደም የዳረገውና ብዙ ወጪም እንዳስከተለ የሚነገርለት ጦርነት፣ በአንዳንዶች ተስፋ የተጣለበትን ያህል ለአንዳንዶች ደግሞ ኪሳራውና ጉዳቱ ብቻ ይታያቸዋል። ጦርነት አውዳሚ መሆኑ ቢታወቅም፣ ተከትሎት ለሚመጣ ሠላም አስፈላጊ ነው ብለው የሚያምኑ በርካታዎች ናቸው።

በመንግሥት ኃይሎችና በተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ተብሎ በተፈረጀው ህወሓት መካከል ሲካሄድ የቆየው ጦርነት ካስከተለው ቀጥተኛ ጉዳት በተጨማሪ፣ በተዘዋዋሪ ሕገ-ወጥ አሠራርን እንዳስፋፋ የሚናገሩ ማስረጃ የሚሉትን እያቀረቡ ይሟገታሉ። ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውርና ዋጋ በመጨመር አላግባብ ለመበልጸግ የሚሞክሩ ግለሰቦችንና ነጋዴዎችን የመሳሰሉትን መንግሥት ዘግየት ብሎም ቢሆን ዕርምጃ መውሰዱ የሚያስመሰግነው እንደሆነ ይነገራል።

በሌላ በኩል፣ የመንግሥትን ሥልጣን ይዘው፣ ወቅቱን ተጠቅመው ሥልጣናቸውን ለማደላደልና ዝናቸውን ለመገንባት የሚጠቀሙበት የመኖራቸውን ያህል፣ ሕገ-ወጥ ተግባራቸውን ለመሸፈን የሚሞክሩም ተገኝተዋል። “በዚህ ጦርነት ወቅት እንዴት መንግሥትን ሊያስወቅስ የሚችል ነገር ታደርጋላችሁ” በሚል ስህተታቸውን ለመሸፈን የሚሞክሩ በተደጋጋሚ በማጋጠማቸው፣ መንግሥት ውስጡ ሆነው ስሙ እንዲጠፋ የሚሠሩትን ሊቆጣጠር እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ማሳሰብ ትወዳለች።

“ወታደሩ ሕይወቱን እየሰጠ እናንተ መብታችን ይከበር ትላላችሁ!” እያሉ የሚገባቸውን ክፍያ የጠየቁ የመንግሥት ሠራተኞች እንዲሸማቀቁ የሚያደርጉ፣ የራሳቸውን ጥቅማጥቅም ግን አሳልፈው የማይሰጡ ኃላፊዎች መኖራቸው እየተደመጠ ነው። ለወራት ያልተከፈለ ደሞዛቸው ከኑሮ ውድነቱ አንፃር ታስቦ እንዲሰጣቸው የሚጠይቁ ሠራተኞች፣ ጦርነቱ ሰበብ እየተደረገ የወታደሩ መስዋዕትነት እየተመካኘ ማግኘት የሚገባቸውን ሊከለከሉ አይገባም።

የመንግሥት አሳቢ መስለው ሕዝብ እንዲማረር የሚያደርጉ አመራሮችን በተመለከተ ሕዝቡ እየጠቆመ አስፈላጊው ዕርምጃ እንዲወሰድባቸው ሊያደርግ ይገባል። በየመሥሪያ ቤቱ በአመራር ላይ የተቀመጡት ምሳሌ ሆነው ሌላው እንዲከተላቸው ማድረግ እንጂ፣ በአገር ዐቀፍ ደረጃ ሳይታወጅ በሥራቸው ያሉትን ብቻ ለይተው ለመዋጮም ሆነ ለግዳጅ እንዳይዳርጉ መመሪያ ሊሰጣቸው እንደሚገባ አዲስ ማለዳ አፅንኦት ሰጥታ ትናገራለች።

በበላይ ባለሥልጣናት ለመወደድና ለመሾም ሲሉ ሠራተኞቻቸውን የሚያስጨንቁ ኃላፊዎች ከዚህ ተግባራቸው የማቆጠቡ ከሆነ ጦርነቱን በአጭሩ ለመቋጨት የሚደረገውን ርብርብ በመጉዳት ትብብሩ እንዲቀንስና የመንግሥት ደጋፊ እንዲመናመን ሊያደርግ ስለሚችል ሊታሰብብት ይገባል። በአንፃሩ “ኹሉ ነገር ወደ ጦር ግንባር” እያሉ በመንግሥት ላይ ሕዝቡ እንዲነሳና እንዲፋለም ለማድረግና ዕድሜያቸውን ለማራዘም የሚጥሩ አካላት የደርግ ሥርዓትን ይተቹበት ከነበረ ተግባር ካልተቆጠቡ መጨረሻቸው ከማንም ያልሆነ መድረሻ ያጣ ስብስብ መሆን ስለሆነ ጦርነቱን መጠቀሚያ ከማድረግ ሊቆጠቡ ይገባል።

አንድ አመራር እንዲያገለግል ኃላፊነት የተሰጠውን ሕዝብ በረባ ባረባው ከማጎሳቆልና ከማስፈራራት ሊታቀብ ይገባል። በማን አለብኝነት የሁሉም ትኩረት ወደ ጦርነቱ ነው በሚል ዕሳቤ ሕገወጥ ተግባርን ለመሸፋፈን መሞከር በሕግ ከማስቀጣቱም በላይ፣ በአደጋ ጊዜ የተፈፀመ ወንጀል እንደመሆኑ ቅጣቱ ሊከብድ ይገባል።

እየታመነ የከዳ አመኔታውን ማጉደሉ ይበልጥ እንደሚቀጣው፣ በእንዲህ አይነት አሳሳቢ ወቅት የግል ፍላጎታቸውን ለማራመድ፣ ተገቢ ያልሆነ ሥራቸውን ለመሸፋፈን፣ የመንግሥትን ድክመት ለመደበቅ በሚል የሚያስፈራሩ፣ እንዲሁም ለሚዲያዎች መረጃን ከመስጠት የሚቆጠቡ አካላት አካሄዳቸው ተዛብቶ በዚሁ መንገድ ከመቀጠሉ በፊት፣ መንግስት ሊያመጣ የሚችለውን ችግር ተረድቶ አካሄዳቸውን እንዲያስተካክሉ ማድረግ እንዳለበት የአዲስ ማለዳ እምነት ነው።

ጦርነት በባህሪው ምስጢር መጠበቅን ግድ የሚል መሆኑ ሳይዘነጋ፣ ሁሉን ነገር በመዝጋት ግን ውጤታማ መሆን አይቻልም። ወታደሩም ሆነ የሚመለከተው አካል ቀጥታ ተሳታፊ ሆኖ ሊገደድ የሚችልበት አሠራር ቢኖርም፣ ሚዲያን የመሳሰሉ ገለልተኛ ተቋማት ሥራቸው ሳይስተጓጎል ማከናወን እንዲችሉ መደረግ አለበት።

“ጦርነት ላይ ነን” እየተባለ ጦርነቱ ሊያስገኛቸው የታለመላቸውን መብቶችን ማሳጣት ዓላማውን ጥያቄ ውስጥ ስለሚከት ሊታሰብበት ይገባል። አገር ችግር ላይ በሆነችበት በዚህ ወቅት የሕዝብን ትኩረት ወደአልተፈለገ አቅጣጫ ሊወስዱ የሚችሉ የባለሥልጣናት ተግባራትን መከታተል እንደሚገባ ለማንም ግልፅ ነው። ስሜን እንዳያጠፉ ወይም እንዳይከዱ በሚል እያባበሉ ማስቀመጡ ድንገት ሊፈጠር በሚችል አጋጣሚ ሁሉን ማጣት ሊያስከትል ስለሚችል ለሕዝብ ቆሜያለሁ የሚል አካል ጉዳዩን በጥንቃቄ ሊያጤነው ይገባል።

በጦር ቀጠና እንኳን የጦር ሕግን የመሳሰሉ ተፋላሚ ወገኖች ሊከተሏቸው የሚገቡ ድንጋጌዎች አሉ። ከጦርነት ርቀው ባሉ አካባቢዎች በተለይም በከተሞች የአስቸኳይ ጊዜ ታውጆ የሕዝብ መብት ሊገደብ ቢችልም፣ ያለ ሕግ ግን በዘፈቀደ የሚሠራ ነገር መኖር እንደሌለበት አዲስ ማለዳ ማሳሰብ ትወዳለች።

አንድ ኃላፊ ሥራውን ሲሠራ የሚመራበት መመሪያ እንዳለው ቢታወቅም፣ ያንን በሚጥስ መልኩ ወቅትን ምክንያት በማድረግ ሕዝብን ማጉላላት እንደሌለበት ሊያውቅ ይገባል። በተለይ መረጃ ከመስጠት አኳያ ሊጠበቁ የሚገባቸውን ምስጢሮችና ይፋ መሆን የሚችሉ ጉዳዮች በሕግ ተለይተውለት አስቀድሞ ኹሉም ሊያውቃቸው ያስፈልጋል።

በአንድ ጉዳይ ላይ እንደተፈለገ የሚወሰን ከሆነ ጦርነቱን መጠቀሚያ በማድረግ ወደአላስፈላጊ ተግባር መግባት ብቻ ሳይሆን፣ ጦርነቱ ሲጠናቀቅም ልምድ ሊሆን ስለሚችል መልካም አስተዳደር የሚባለውን ጽንሰ-ሐሳብ ሊፃረር ስለሚችል ይታሰብበት።
በሌላ በኩል፣ በባህላችን የነበረ በጦርነት ወቅት ሊኖር የሚችል ጊዜያዊ የፍርድ ሒደትም ጥቅሙ ታይቶ በየአካባቢው የሚቋቋምበት ሁኔታ ቢታሰብብት መልካም ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን አንድ ተዋጊ የማረከውን መሳሪያ ሊገበያይ የሚችልበት አጋጣሚ እንደጥንቱ ከውጊያ በኋላ ሊኖር ስለሚችል ሒደቱ እንደ ሕገ-ወጥ መታየቱ ቢያቆም ተገቢ ይሆናል። መንግሥት የሰጣቸውን ራሳቸው የሚሸጡ ከተገኙ መቀጣታቸው ተገቢ ቢሆንም፣ ከያዘው የግሉ ሌላ ተጨማሪ የማረከ ለሌላ ሸጦ የሌለው ገዢ አስተዋፅኦ እንዲያደርግ ካልተደረገ ችግር ሊፈጥር እንደሚችል ሊታሰብበት ይገባል። የወገን ጦር የሚማርከው መሣሪያ የመንግሥት የነበረ፣ ነገር ግን ተቃራኒ ወገን ማርኮትም ሆነ ወስዶት ተመልሶ የተማረከ ሊሆን ስለሚችል ሲሻሻጡ የተገኙን እያፈሱ ማሰሩ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል።

በአጠቃላይ፣ ወቅቱ የጦርነት ነው ተብሎ “የአባትህ ቤት ሲዘረፍ አብረህ ዝረፍ” የሚለው ብሂል ተግባራዊ መደረጉ ሊቆም ይገባል። ኹሉም ተዘርፎ ባዶ ከምንቀር፣ አብረን ዘርፈን ትንሽ እናስቀር የሚል መልዕክት ያለውን አባባል ትተን፣ እንዳይዘረፍ መሞከር ነው። ይህ ካልተቻለም ለጊዜው በመደበቅ ክፉ ጊዜው እንዲያልፍ ማድረግ እንጂ፣ ወቅቱን ተጠቅሞ ለመጠቀም መሞከሩ አተርፍ ባይ አጉዳይ እንደሚያደርግ አዲስ ማለዳ ማስገንዘብ ትፈልጋለች።


ቅጽ 3 ቁጥር 151 መስከረም 15 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!