የእለት ዜና

በቆቦ ከተማ የአንድ እንጀራ ዋጋ 50 ብር እየተሸጠ ነው

በከተማዋ መነገድ የሚችለው የትግራይ ተወላጅ ብቻ ነው

በተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጀው ህወሓት በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ውስጥ የምትገኘውን ቆቦ ከተማን መቆጣጠሩን ተከትሎ የአንድ እንጀራ ዋጋ 50 ብር መግባቱን የአካባቢው ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።
ሰሞኑን ከአካባቢው ተፈናቅለው ወደ ደሴ ከተማ የመጡ የከተማዋ ነዋሪዎች እንደሚሉት ከሆነ፣ በሽብርተኝነት የተፈረጀው ህወሓት አካባቢውን ከተቆጣጠረበት ጊዜ ጀምሮ የነዋሪዎቹን “እህል በሙሉ በመዝረፉ” አሁን ላይ አንድ እንጀራ 50 ብር እንደሚሸጥ እና በቦታው ያሉ ሰዎች ርሃብ ላይ መሆናቸውን ነው የገለጹት።

“አስር ብር የነበረው እንጀራ 50 ብር ነው ስንገዛ የነበረው” ያሉት ኗሪዎቹ፣ ዋጋው የጨመረበት ምክንያትም እንጀራውን መግዛት የሚቻለው ከትግራይ ክልል መጥተው በቆቦ ከተማ ከሰፈሩት ነጋዴዎች ብቻ ስለሆነ ነው ብለዋል።
አዲስ ማለዳ ከነዋሪዎቹ የተረዳችው፣ የአካባቢው ነዋሪዎች ከመዘረፍ ያተረፉትን ብር በመጨረሳቸው እና በእያንዳንዱ ሸቀጥ ላይ ከልክ ያለፈ የዋጋ ጭማሪ በመከሰቱ የዕለት ምግባቸውን መግዛት አለመቻላቸውን ነው።

ሰሞኑን ከቆቦ ወደ ደሴ ከተማ የመጣው ማህደር ታደሰ የተባለው ወጣት የአንድ እንጀራ ዋጋ ሃምሳ ብር መሆኑን የተናገረ ሲሆን፣ “ሊያስገርመን የሚገባው እንጀራ ሃምሳ ብር መሆኑ ሳይሆን በዚህ ዋጋም መገኘት አለመቻሉ ነው” ሲል ያለውን አሳሳቢ ሁኔታ ገልጾታል።
መብራት ከጠፋ ኹለት ወር ሆኖታል የሚለው ማህደር፣ የትግራይ ተወላጆች በቆቦ ከተማ በጀመሩት የንግድ እንቅስቃሴ በእያንዳንዱ ዕቃ ላይ የዋጋ ጭማሪ ተደርጎ አስር ብር ሲገዛ የነበረው ሻማ 60 ብር፣ 120 ብር የነበረው አንድ ሊትር ዘይት 390 ብር፣ አራት ብር የነበረው ክብሪት 13 ብር፣ ኹለት ብር የነበረው ዳቦ 10ብር መሆኑን ነው የገለጸው።

አክሎም የእጅ ባትሪ 160ብር እንደሆነና አንዷ የባትሪ ድንጋይ 50 ብር በመሆኗ የአካባቢው ተወላጆች የመብራት ዕጥረት እንደገጠማቸው አብራርቷል። “ከሞት በተረፈው ሕዝብ ላይ ሆን ተብሎ የኢኮኖሚ ብዝበዛ እየተደረገበት ከመሆኑም በላይ፣ አብዛኛው ሰው ብር ስለሌለው መግዛት ስለማይችል ለርሃብና ለጨለማ ተጋልጧል” ብሏል።

ሌላኛው ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉት አየነ በላይ የተባሉት የነርስ ባለሙያ አንድ እንጀራ ከ50 ብር በላይ ሲሸጥ የቆየ ቢሆንም፣ አሁን ላይ የአቅርቦት ችግር መኖሩን አብራርተዋል። አያይዘውም የአንድ ኪሎ ዱቄት ዋጋ 70 ብር እንደሚሸጥ የገለጹ ሲሆን፣ “መነገድ የሚችለው የትግራይ ተወላጅ ብቻ ነው” በማለት አንድ ኩንታል ዱቄት 2ሺሕ ብር ሲሸጡ የነበሩት የአካባቢውን ተወላጆች “ለምን በቅናሽ ዋጋ ትሸጣላችሁ’’ ተብለው ከንግድ ሥራቸው እንደተባረሩ እና የትግራይ ተወላጆቹም አንድ ኩንታል ፉርኖ ዱቄት 7ሺሕ ብር እየሸጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የአካባቢው ነዋሪዎች በከተማው በነበሩት ኹለት የነዳጅ ወፍጮዎች አንድ ኪሎ ጥሬ 26 ብር እያስፈጩ የቆዩ መሆኑን የገለጹት አየነ በላይ፣ ወፍጮዎቹ ከአንድ ወር በፊት ተነቅለው ወደ መቀሌ በመወሰዳቸው ለሽያጭ የሚቀርበው ዱቄት ከመቀሌ የሚመጣ እና በቆቦ ከተማ ለሚገኙ የትግራይ ክልል ነጋዴዎች ብቻ በችርቻሮ የሚሸጥ መሆኑንም ነው የገለጹት።

አክለውም፣ በሽብርተኝነት የተፈረጀው የህወሓት ቡድን ራሳቸውን መልካም ለማስመሰል ለሕዝቡ አቅርቦት አለ ቢሉም፣ እውነታው ግን እያንዳንዱ ነገር ውድ መሆኑን ነው። ከዚህ በተጨማሪ እርግጠኛ ሆኘ የምናገረው ነገር ቢኖር ከጳጉሜ አራት ጀምሮ የንግድ እንቅስቃሴ በመዘጋቱና ምንም አይነት አቅርቦት ባለመኖሩ የአካባቢው ተወላጆች በርሃብ ላይ መሆናቸውን ነው” በማለት የዐይን እማኝነታቸውን መስክረዋል።

ከቆቦ ከተማ ተፈናቅለው በደሴ የሚገኙት ነዋሪዎች እንደገለጹት ከሆነ፣ ህወሓት በተቆጣጠረው አካባቢ የቀሩ ሰዎች “ከኹለት ወር ጀምሮ በርሃብ ከመቀጣታቸውም በተጨማሪ፣ በሽብርተኝነት የተፈረጀው ህወሓት ጳጉሜን አራት 2013 በሰነዘረው ጥቃት ከ600 በላይ ንጹኃን በግፍ ተገድለዋል’’ ብለዋል።

ግድያው አቅመ ደካማ አዛውንቶችን ያጠቃለለ ሲሆን፣ ሰኞ ገበያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በተሰነዘረው የፈንጂ ጥቃት ከተለያዩ ቦታዎች የመጡ የቀን ሠራተኞችና የከተማው ገበሬዎች መገደላቸውን በአካባቢው የነበሩ የዐይን እማኞች አብራርተዋል።
“ኹለት ወር ሙሉ ለፈለፍን፣ ግን ሰሚ የለም” የሚሉት ነሪዎቹ፣ ከሞት ተርፈው በርሃብ ላይ ላሉት ሰዎች ቢያንስ ቀይ መስቀል እንኳን ሊደርስላቸው ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 151 መስከረም 15 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!