የእለት ዜና

የትርፍ ድርሻ ለባለአክሲዮኖች ያልከፈለው ሐበሻ ሲሚንቶ ቅሬታ ቀረበበት

የሲሚንቶ ፋብሪካው አመራር ኹለት እና ሦስት ዓመት ታግሰው ከጠበቁን የትርፍ ድርሻቸውን መክፈል እንጀምራለን ሲል አስታውቋል

ሐበሻ ሲሚንቶ አክሲዮን ማኅበር ከተመሰረተ ከ10 ዓመት በላይ ቢያስቆጥርም ፋብሪካው ሥራ ከጀመረበት ጊዜ አነስቶ እስከ አሁን ምንም አይነት የትርፍ ድርሻ ከፍሎን አያውቅም ሲሉ ባለአክሲዮኖች ለአዲስ ማለዳ ቅሬታቸውን አቀረቡ።

ባለአክሲዮኖቹ በመደበኛ ዓመታዊ የባለአክሲዮኖች ስብሰባዎች ላይ በተደጋጋሚ የትርፍ ድርሻ ክፍያችን ይከፈለን ስንል ብንጠይቅም፣ የቦርዱ አመራሮች ያሉትን ችግሮች ሁሉ አስተካክለን መክፈል እንጀምራለን ሲሉን ቆይተዋል ብለዋል። ቢሆንም ግን ሰኔ 9/2013 በተካሄደው ዓመታዊ ስብሰባ ላይ ፣ ፋብሪካው ከአቅም በላይ በሆነ ኪሳራ ላይ ስለሚገኝ የባለአክሲዮኖችን የትርፍ ድርሻ ክፍያን መክፈል አይችልም ሲል ቦርዱ እንዳስታወቃቸው ገልጸዋል።

እንደ ባለአክሲዮኖቹ ገለጻ ከሆነ፣ ተቋሙ የተጠበቀውን ትርፍ ማግኘት ባይችልም፣ ባላቸው ድርሻ ተጠቅመው መበደርና አክሲዮናቸውን መሸጥ የሚችሉበት አሠራር እንዲፈጠርላቸው ጠይቀዋል። ቅሬታ አቅራቢዎቹ ቦርዱ የፋብሪካውን አጠቃላይ የሀብት ግምገማ ሪፖርት እንዲያሳውቃቸው ቢጠይቁም፣ ለመስከረም 2014 እንደቀጠሯቸውና እስከ አሁን ምንም አይነት ምላሽ እንዳልተሰጣቸው ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።

“ከ16 ሺሕ በላይ በሆኑ ኢትዮጵያዊያን የተመሰረተው ፋብሪካ፣ በአስተዳደር ችግር ምክንያት ወደ መክሰም እያመራ ስለሚገኝ የሚመለከተው አካል መፍትሔ ሊሰጠን ይገባል” ሲሉም ቅሬታቸውን አሰምተዋል።

አዲስ ማለዳም ቅሬታውን በመያዝ የሐበሻ ሲሚንቶ ዋና ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ጋሰን ብሮማና አናግራለች። ሥራ አስኪያጁ እንደገለጹት፣ ወደ ፋብሪካው በኃላፊነት በገቡበት ወቅት ፋብሪካው በከፍተኛ ኪሳራ ላይ እንደነበር ገልጸዋል።

“በመደበኛ ዓመታዊ የባለ አክሲዮኖች ስብሰባ ላይ ዕድል ቢሰጠኝና መናገር ብችል፣ ባለ አክሲዮቹ ትንሽ እንዲረጋጉና አክሲዮናቸውን ለመሸጥ እንዳይቸኩሉ እንግራቸው ነበር። ምክንያቱም ከጥቂት ዓመት በኋላ ነገሮች ይስተካከላሉ፤ ያኔ የተሻለ ነገር ይኖራል” ሲሉ አስረድተዋል።

አክለውም፣ የአክሲዮን ማኅበሩ ያጋጠመውን የምርት አነስተኛነት እና አጠቃላይ ኪሳራ ለመቅረፍም ፒ.ፒ.ሲ እና አይ.ዲ.ሲ ለተሰኙ የደቡብ አፍሪካ የሲሚንቶ አምራች ድርጅቶች የፋብሪካው 60 በመቶ የሚሆን ድርሻ መሸጡን በመግለጽ፣ እነርሱ ከፍተኛ የድርሻ ተካፋይ እንደመሆናቸው ከእነሱ እና ከአጠቃላይ የቦርድ አባላቱ ጋር ተነጋግረን የይሁንታ ፍቃድ ስላላገኘን ነው ሪፖርት ከማድረግ የዘገየነው ብለዋል።

በፋብሪካው ላይ የነበሩ በርካታ ዕዳዎችና ከአውሮፓ ለሚመጡ የማሽነሪ ጥገና ባለሙያዎች ከፍተኛ ወጪ መውጣቱን ያብራሩት ጋሰን፣ ፋብሪካው ከ12 ሚሊዮን ዶላር በላይ ዕዳ እንደነበረበት እና ይህን ዕዳ ለመክፈል በርካታ አዳዲስ ኢንቨስትመንቶች መከናወናቸውን ተናግረዋል።

ዋና ሥራ አስኪያጁ አክለውም፣ ፋብሪካው ውስጥ የሚገኙ ማሽኖች አሁንም ድረስ ጥገና የሚያስፈልጋቸው በመኖራቸው፣ ለባለአክሲዎኖቹ የድርጅቱን ውስጣዊ ችግር ለማስረዳት ዕቅድ መያዙን ጠቅሰዋል። አክለውም “ተስፋ እንዲቆርጡ አንፈልግም፤ ለተፈጠረው ነገር ሁሉ ይቅርታ እንጠይቃለን። ባለአክሲዮኖች ታግሰው ቢጠብቁ ቢበዛ በኹለት እና ሦስት ዓመታት ውስጥ ጥሩ የሚባል ትርፍ እናገኛለን። የትርፍ ድርሻ ክፍያቸውንም መክፈል እንጀምራለን” ብለዋል።

በአሁኑ ሰዓት ፋብሪካው የማምረት አቅሙ 35 በመቶ ሲሆን፣ አጠቃላይ ጥገናዎች ሲጠናቀቁ ከ60 በመቶ በላይ ለማምረት ታቅዷል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከአንድ ዓመት በፊት ለሲሚንቶ ፋብሪካዎች መለዋወጫና አጠቃላይ ጥገና እንዲውል 85 ሚሊዮን ዶላር መፍቀዱ የሚታወስ ሲሆን፣ ለሐበሻ ሲሚንቶ 8 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዶላር መፈቀዱን ጋሰን ጠቅሰዋል። ይህንን ድጋፍ የመለዋወጫ ግዢ እና አጠቃላይ ብድሮች ለመክፈል ተጠቅመንበታል ብለዋል።

አክለውም ፋብሪካው ከአራት ቢሊዮን ብር በላይ በኪሳራ ላይ እንደነበር አንስተው፣ ይህን ኪሳራ ለማስተካከል ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝና ተጨማሪ ድጋፎች እንደሚያስፈልጉትም አስረድተዋል።
ባለአክሲዮኖች አክሲዮን ገዝተው ከአስር ዓመት በላይ ያለ ምንም የትርፍ ክፍያ መቆየታቸው ሚዛናዊ አይደለም የሚሉት ሥራ አስኪያጁ፣ “ይሄ ነገር የተከናወነው እኔ በአመራር ቦታ ላይ ሳልኖር ነው›› ብለዋል።

“የሲሚንቶ ቴክኖሎጂ ላይ ማንኛቸውም ትላልቅ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች በዓመት አንዴ ጥገና ማድረግ አለባቸው። እንደ መርህም ‘ጥገና ከሌለ ምርታማነት አይኖርም’ የሚል ሐሳብ ተቀምጧል” የሚሉት ደግሞ በንግድ እና ኢንደስትሪ ሚኒስቴር፣ የኬሚካል እና ኮንስትራክሽን ግብአቶች ኢንዱስትሪ ልማት ኢኒስቲትዩት፣ የሲሚንቶና ተዛማጅ ኢንዱስትሪ ምርምር ቴክኖሎጂ ልማት ዳይሬክተር የሆኑት ስመኝ ደጉ ናቸው።

ዳሬክተሩ እንደሚሉት ከሆነ ሐበሻ ሲሚንቶ አ.ማ. በመንግሥት በታወቀና በዕቅድ ላይ በተመሠረተ መልኩ ለአንድ ወር አጠቃላይ ጥገና ለማድረግ ሥራ አቁሞ እንደነበር ገልጸው፣ በአሁኑ ሰዓት ግን የፋብሪካው አብዛኛው ጥገና ተጠናቆ ከአንድ ሳምንት በፊት ወደ ምርት መግባቱን አስረድተዋል።

የባለአክስዮኖቹን ቅሬታ በተመለከተ፤ የአክሲዮን ክፍያ ይከፈል አይከፈል መረጃው እንደሌላቸው የጠቆሙት ስመኝ፣ በአሁን ሰዓት ግን ፋብሪካው የማምረት አቅሙ ከ50 በመቶ በታች ስለሆነ ዝቅተኛ አፈጻጸም እንዳለው ጠቁመዋል።

አክለውም ሐበሻ ሲሚንቶ የተለያዩ ችግሮች የነበሩበት ሲሆን፣ እነሱን ለመቅረፍ እየሠራ እንደሚገኝ አመራሮቹ ለኢንስትቲዩቱ ማስታወቃቸውን ገልጸዋል። ስለዚህ የማምረት አቅሙ በጣም ዝቅተኛ ስለሆነ ከባለ አክሲዎኖች ጋር አለመስማማት ውስጥ ይገባል ተብሎ የሚገመት ጉዳይ ነውም ሲሉ ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።

ይህ ዜና ከተጠናቀረና ወደ ኅትመት ከገባ በኋላ፣ ባለአክሲዮኖቹ ከሐበሻ ሲሚንቶ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ለመነጋገር ቀጠሮ መያዛቸውን ብሎም ነገሮች የሚስተካከሉበትን መንገድ በጋራ ለመወያየት ዕድል ማግኘታቸውን አዲስ ማለዳ ለማወቅ ችላለች።


ቅጽ 3 ቁጥር 151 መስከረም 15 2014

Comments: 1

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

  1. Are minegrilin tefa mikiniatachew demo ayalkim yemikiniat dirdir yakerbalu endewum.enezi behig meteyek new yalebachew daru min hig ale

error: Content is protected !!