የእለት ዜና

ስርዓት ያጣው አሰፋፈር፤ ሌላው ተግዳሮት

የሰው ልጅ ከቀደመው ጊዜው ጀምሮ በአንድ ላይ በጋርዮሻዊ ስርዓተ ማኅበር መኖር ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በአሰፋፍ የሚመቸውን ስፍራ ይዞ በአኗኗር እና በአገዛዝ ደግሞ በጎለበተው እየተመራ በዲሞክራሲያዊ አካሄድ መመራት እስኪደርስ ድረስ የአለም እና የሰው ልጅ ዕድገት አዝግሟል፡፡

በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት አኗኗር እና የአሰፋፈር ሁኔታ ዘፈቀዳዊ መሆኑን እና ይህንንም ደግሞ በተደጋጋሚ በተካሄዱ ጠናቶች መመልከት ይቻላል፡፡ ይህንንም ተከትሎ ዜጎች በርካታ መብቶቻቸው ሲጣሱ እና ከአሰፋፈራቸው የተነሳ የሚደርስባቸው መገለል ወይም ለመብቶቻቸው ተጠቃሚ አለመሆን ዋነኛው ምክንያት በመሆን ይነሳል፡፡ በእነዚህ ጥናት መሰረት የሰዎች አሰፋፈር ደግሞ በሌላ በኩል ሕገ ወጥነትን ከማስፋፋት ባሻገር መንግሥት እንደዜጎች በመቁጥር በሕገ ወጥ መንገድ በሰፈሩበት ስፍራ ላይ ተገቢውን መሰረተ ልማቶች ለማሟላት እንደማይጠበቅበትም ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች ይናገራሉ፡፡

የአሰፋፈር ሕጋዊነትን በተመለከተ አጥኚዎች እንደሚሉት የአገረ መንግስት አስተዳደር እና አቋም ይለካበታል፤ ማብራሪያም የሚሰጥበት አንደኛው ጉዳይ ቢኖር ይህ የአሰፋፈር ሕጋዊነት ወይም ደግሞ አገርን እና የተፈጥሮ ኃብትን በማይጎዳ መሆኑ ነው፡፡ በቅርቡ ፒ ኤች ኢ ኢትዮጵያ የተባለ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጥምረት  ከአይ አር አይ ከተባለ ምግባረ ሰናይ እና ድርጅት ጋር በመተባበር አንድ ዝግጅት ባዘጋጀበት ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየውን ኢ መደበኛ የሆነ አሰፋፈርን በተመለከተ ጥናት ቀርቦ ነበር፡፡

በከተሞች ሚታየው የኢ መደበኛ የሰዎች አሰፋፈር በኢትዮጵያ፤ ከሰብዓዊ መብቶች እና ከአከባቢያዊ መብቶች አንጻር በሚል የቀረበው ጥናት ኢትዮጵያ ከተሞችን በመመርኮዝ ነበር ጥናቱን ያካሔደው፡፡ በዚህም መዲናችን አዲስ አበባ፣ ዋቻሞ ወይም ሆሳዕና ፣ ሐዋሳ እና ደብረ ብረሐን ከተሞች የጥናቱ አካል ነበሩ፡፡

በዚህ ጥናት መሰረት ከዚህ ቀደም በከተሞች ዙሪያ ይታዩ ወይም የእርሻ ስራ ይከወንባቸው የነበሩ አካባቢዎች በኢ መደበኛ ሰዎች ሰፋፈር ምክንያት የእርሻ ቦታዎች ወደ መኖሪያ ስፍራዎች እየተቀየሩ የመምጣት አካሔድ መኖሩን ይጠቁማል፡፡ አዲስ ማለዳ በተለያዩ አካባቢዎች ተዘዋውራ ለመታዘብም እንደቻለችው ከዚህ ቀደም ከተነሱት ሕጋዊ ካልሆኑት የመሬት ቅርምቶች ባለፈ ኢ መደበኛ የሆኑ አሰፋፈሮች አሁንም ደረስ በተለይም ደግሞ በመዲናችን አዲስ አበባ ዙሪያ በስፋት የሚታይ አዲሱ ስጋት ነው፡፡

መሬት አንደኛው እና ትልቅ የተፈጥሮ ኃብት ከመሆኑ ጋር ተዳምሮ በአግባብ አለመጠቀም እና በተጊው መንገድ ለልማት እና ለዕድገት መሰረትነት አለማዋል ውጤቱ አሁን ኢትዮጵያ ያለችበት የኑሮ ደረጃ አመላካች እንደሆነም ይነገራል፡፡ ይህን በሚመለለከት አዲስ ማለዳ ያነጋረቻቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዢ የሆኑት ፍቃዱ ደግፌ፤ የተፈጥሮ ሀብት መኖር በራሱ ማስተማመኛ አይደለም ሲሉ ሀሳባቸውን ይሰነዝራሉ፡፡ የተፈጥሮ ሀብት በአግባቡ በመጠቀም ማልማት እንጂ የተፈጥሮ ሀብቱ ብቻውን መኖር ዋስትና ሊሆን አይችልም ሲሉ ሀሳባቸውን ያስረግጣሉ፡፡

በጥናቱ መሰረት በኢትዮጵያ ካለው የሰዎች ወይም የሕዝብ አሰፋፈር ውስጥ 30 በመቶ የሚሆነው አሰፋፈር ኢ መደበኛ እና ሕግን ያልተከተለ መሆኑን ያመላክታል፡፡ አየለ ሀገና (ዶ/ር) ጥናቱን ሲያቀርቡ እንደሚናገሩት በርካታ አርሶ አደሮች በኢ መደበኛ አሰፋፈር ምክንያት ከቀያቸው እና ከእርሻ ስፍራቸው ተፈናቅለው ለከፋ ችግር መዳረጋቸውን ያወሳሉ፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ በኢ መደበኛ መንገድ ሰፍረው በከተሞች ውስጥ ላሉ የመሰረተ ልማት አገልግሎቶች ተደራሽ አለመሆናቸው ደግሞ በሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ዘንድ እንዲሁም በተባበሩት መንግስታት የመኖሪያ እና ነዋሪዎች ድርጅት (ዩ ኤን ሐቢታት) አመካኝነት ሲጠቀስ እና መንግስትም በዚህ በኩል ሲወቀስ ይሰማል፡፡ ይህን በሚመለከት አዲስ ማለዳ ወደ መሰረታዊ የመሰረተ ልማት አቅራቢዎች ተቋማት በማቅናት ጥያቄውን ለማንሳትም ችላ ነበር፡፡ ከአዲስ አበባ መብራት አገልግሎት፣ የውሃ እና ፍሳሽ እንዲሁም አዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን የተመለሰው ምላሽ አንድ እና ተመሳሳይ ነው፡፡ ይህም ዜጎች በኢ መደበኛ መልኩ በሰፈሩበት አካባቢ እነዚህን መሰረተ ልማት ለማዳረስ በፍጹ የማይቻል እና አንደኛ የከከተማው ማስተር ፕላን አንጻር የሚጣረስ ሲሆን ሌላው ደግሞ አገልግሎቶችን ለማዳረስ በሚደረግበት እንቅስቃሴ ውስጥ ሌሎች በፕላን በተሰሩ መሰረተ ልማቶች ላይ፣ መኖሪያ ቤቶች ላይ እንዲሁም ሕንጻዎች ላይ ጉዳት ማድረሳችን የማይቀር ነው ስለዚህ ሊሆን አይችልም ሲሉ ይናገራሉ፡፡

ከዚህ ቀደም ምርት እና ምርታማነትን በሚመለከት ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ‹‹አንድም መሬት ጾም ማደር የለበትም›› ብለው ባስጀመሩት የከተማ ግብርናን ጨምሮ ሌሎች እንቅስቃሴዎች ላይ መሬቶች በገፍ ወደ እርሻ ስፍራነት መቀየራቸው ይታወሳል፡፡ ይሁን እንጂ ይህን ጹሑፍ ለማሰናዳት በተንቀሳቀስንባቸው አካባቢዎች ላይ የእርሻ ስፍራዎች ላይ አነስተኛ ቤቶች ተሰርተውባቸው ለማየት ተችሏል፡፡ በአካባቢያዊ አንቂዎች አንጻር ይህን አይነት ኢ መደበኛም ብቻ ሳይሆን ከልክ ያለፈ ከተሞች መለጠጥ ለአርሶ አደሮች ሕልውና አደጋ ነው ሲባል መቆየቱም ይታወቃል አሁንም ይህን ጉዳይ ሲያስተጋቡት ይገኛል፡፡

ለኢ መደበኛ አሰፋፈር እንደምክንያ የሚጠቀሱት ደግሞ ከፍተኛ የሆነ የመኖሪያ ቤት ወጪ በግንባር ቀደምትን ይጠቀሳል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ደካማ ምናልባትም ደግሞ የተሸነፈ የከተሞች አስተዳደር መገለጫ ተደርጎም እንደሚወሰድ ጥናቶች ያረጋግጣሉ፡፡ በመዲናችን አዲስ አበባ ደግሞ ይህ ጉዳይ ከገጠር ወደ ከተማ ከመፍለስ ጋር በጥብቅ የሚያያዝ ነው፡፡

በጥናታዊ ጽሑፉ ላይ በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ የመሬት አስተዳደር እና አያያዝ ጉዳይ በጠንካራ አቋም ላይ ነው ለመባል ማያስደርፍ እንደሆነም በግልጽ ተቀምጧል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የመጀመሪያውን መሬት አስተዳደር በተመለከተ 32 አንቀጾች ያሉት እና በዳግማዊ ሚኒልክ ጊዜ የተጀመረው የከተሜነት ሕግ የመሬት ባለቤትነትን ሕግ ያካተተ እና የመሬት ባለቤትነትን የሚያረጋግጥ እንደሆነ ይነገራል ሲሉ አየለ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት ለኢመደበኛው አሰፋፈር ከጀርባ በመሆን ድጋፍ እየሆነ ያለው የጠነከረው የሙስና መረብ መሆኑንም አየለ የናገራሉ፡፡

ከላይ የተጠቀሱት ችግሮችን ለመፍታት ታዲያ መንግስት መውሰድ የሚኖርበትን እርምጃዎችንም በጥናቱ ላይ ተቀመጠ ሲሆን ይህም ደግሞ ለአፈጻጸም ምቹ እና ጠንካራ ሆነ መሬት ፖሊሲ ወጥቶ ወይም በማርቀቅ ወደ ተግባር መግባት እንደሚኖርበት ተጠቁሟል፡፡ በተመሳሳይም በሕጋዊ መንገድ ያልተያዙ መሬቶችን እንዲሁ ወደ ሕጋዊነት በማምጣት ከልክ ያለፉ የመሬት ቅርምቶችን በተመለከተ ጠንካራ ቅጣት መጣልም ሌላኛው መፍትሔ ተደርጎ ተወስዷል፡፡


ቅጽ 3 ቁጥር 151 መስከረም 15 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com