የእለት ዜና

በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ዞን ግድያ እና መፈናቀል መኖሩን ኢሰመኮ አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን /ኢሰመኮ/ በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ዞን ግድያ እና መፈናቀል መኖሩን ከነዋሪዎች መረጃ የደረሰው መሆኑን አስታውቋል።

ኮሚሽኑ በምሥራቅ ወለጋ ዞን፣ ኪራሙ ወረዳ የሚገኙ ሲቪል ሰዎች ለደኅንነታቸው አስጊ ሁኔታ ላይ የሚገኙ መሆናቸው የሚያሳስብ መሆኑን ነው ብሏል።

በዚሁ ወረዳ፣ ቦቃ ቀበሌ መስከረም 7 እና 8 ቀን 2014 ዓ.ም በደረሱ ሦስት ተያያዥ ጥቃቶች በአጠቃላይ 18 ሲቪል ሰዎች መገደላቸውን፣ እንዲሁም መስከረም 8 ቀን 2014 ዓ.ም በውልማይ ቀበሌ በተፈጸመ ሌላ ጥቃት 11 ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ለኮሚሽኑ አሳውቀዋል።

በኪራሙ ወረዳ ባለው አሳሳቢ የፀጥታ ሁኔታ ምክንያት ከተለያዩ የወረዳው አካባቢዎች ተፈናቅለው በኖሌ ቀበሌ፣ በሀሮ እና ኪራሙ ከተሞች ተጠልለው የሚገኙ ከ40 ሺህ በላይ የሚሆኑ ነዋሪዎች ለወራት አስቸኳይ ሰብአዊ ዕርዳታ እና ሌሎች ድጋፎችን ባለማግኘታቸው አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ነዋሪዎች ለኮሚሽኑ ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት ኪራሙ ወረዳን ከቡሬ እና ነቀምቴ ከተሞች ጋር የሚያገናኙ ዋና ዋና መንገዶች ለተሸከርካሪ እንቅስቃሴ ተዘግተው እንደሚገኙ ኮሚሽኑ አረጋግጡን ገልጿል።

የፌዴራል እና የክልሉ መንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በኪራሙ ወረዳ ላለው የፀጥታ ስጋት ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት እና በነዋሪዎች ላይ በተደጋጋሚ ጥቃት የሚያደርሱ ኃይሎችን ከሕግ ፊት ለማቅረብ ተጨባጭ እርምጃዎችን እንዲወስዱ ኮሚሽኑ አሳስቧል።

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com