የእለት ዜና

ኢዜማ በሰሜን ጎንደር ጭና ለተጎዱ ወገኖች ከ450 ሺህ ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ አደረገ

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በህወሓት ሃይል በሰሜን ጎንደር ጭና ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉና ቤተሰቦቻቸውን ላጡ ወገኖች ከ450 ሺህ ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ አደረገ።

ድጋፉን ለማድረስ በጭና የተገኙት የኢዜማ ብሔራዊ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ኑሪ ሙደሲር «የሕዝባችን ችግር የእኛም ችግር ነው ብለን ነው እዚህ የተገኘነው» ብለዋል።
«ወቅቱ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ፣ በብሔር ምክንያት ተለያይተን የምንቆምበት ሳይሆን ሀገራችን የመጣባትን ጠላት ተከላክለን ኢትዮጵያን ለሚቀጥለው ትውልድ የምናስረክብበት ነው” ሲሉ ገልጸዋል።
የኢዜማ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ቡድን ዋና ጸሐፊ ማስተዋል አስራደ «የፖለቲካ ልዩነት ቢኖረንም በቀጣይ በጋራ ልንቆም ይገባናል” ብለዋል።
“ደም ልገሳ፣ አልባሳትንና ንጽሕና መጠበቂያ እና መልሶ ማቋቋም ላይ የዜግነት ግዴን በተግባር እንወጣለን፣ ሀገራችን ችግር ውስጥ በምትሆንበት ጊዜ አብሮ የመቆም ባህሉም ልምዱም ስላለን የተደቀነብንን ፈተና እስክንወጣው ድረስ በእያንዳንዱ ነገር አብረን ሳንለያይ በጋራ እንቆማለን” ሲሉ ገልጸዋል።
በድጋፍ ርክክቡ ላይ የተገኙት የሰሜን ጎንደር ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ የተለያዩ ማኅበራት፣ የተደራጁ ወጣቶች፣ የመንግሥት ሠራተኞች የሚያደርጉት መሰል ድጋፍ በአንድ ጊዜ ብቻ ሊቆም እንደማይገባ ገልጸዋል።
መልሶ የማቋቋም ሥራን ለመስራት በክልል ደረጃ የተዋቀረው ኮሚቴ ተፈናቅለው ያሉትን ወደነበሩበት የመመለስ እና ተያያዥ ድጋፎችን የማድረግ ሥራ በቅርቡ እንደሚጀምር ገልጸው፤ በማቋቋም ሥራው ላይ ኢዜማ ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለበት ጠቁመዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
ፓርቲው ከጎንደር በተጨማሪ በደሴ እና በአፋር ክልል ጭፍራ ለሚገኙ ወገኖች ከመስከረም 12 ቀን 2014 ጀምሮ በሦስት ልዑክ በመንቀሳቀስ ተፈናቃዮች ያሉበት ድረስ በመገኘት ያሰባሰበውን ድጋፍ አስረክቧል።
Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com