የእለት ዜና

የመስቀል እና የኢሬቻ በዓላትን ለማክበር ወደ አዲስ አበባ የሚመጡ እንግዶች በሆቴሎች ጥሩ አቀባበልና መስተንግዶ ይጠብቃቸዋል ተባለ

የመስቀል እና የኢሬቻ በዓላትን ለማክበር ወደ አዲስ አበባ የሚመጡ እንግዶች በሆቴሎች ጥሩ አቀባበልና መስተንግዶ እንደሚደረግላቸው የአዲስ አበባ ከተማ ሆቴል ባለንብረቶች ማሕበር አስታወቀ።

ለኢሬቻ በዓል ከውጭና ከአገር ውስጥ ጥሪ የተደረገላቸው ከ400-500 እንግዶች አዲስ አበባ ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የማሕበሩ ሥራ አስኪያጅ አመሃ በቀለ፤ ሆቴሎች በዓላቱን ለማክበር የሚመጡ የውጭና የአገር ውስጥ እንግዶችን ለመቀበል አስፈላጊውን ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን ተናግረዋል።

የአገር ውስጥና የውጭ እንግዶች በተለያዩ ቦታዎች በመዘዋወር በዓሉን ሲያከብሩ የተሻለ መስተንግዶና ጥሩ አቀባበል ይጠብቃቸዋል ብለዋል።

ሆቴሎች ለሀገር ውስጥ ገበያም ትኩረት በመስጠት የዘርፉን አገልግሎት ለማሳደግ መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በአዲስ አበባ የሚገኙ ትላልቅ ሆቴሎች ለውጭ እና ለአገር ውስጥ እንግዶች እኩል ትኩረት እንዲሰጡም ጠይቀዋል።

በአሁኑ ወቅት በዘርፉ የሚፈለገውን እድገት ለማምጣትና የተለያዩ አማራጮችን ለማየት አገልግሎቱን ማስፋት ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ጠቁመዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

ኢትዮጵያዊያን ከቦታ ቦታ ተዘዋውረው አገራቸውን የሚጎበኙበትና በዓላትን የሚታደሙበት ልምድ እንዲያካብቱ ለማድረግ የሆቴሎች መስተንግዶ ወሳኝ መሆኑንም አመሃ ገልጸዋል።

የሆቴል ባለንብረቶች ከባህልና ቱሪዝም፣ ከአስጎብኝዎችና ከተሽከርካሪ አከራይ ድርጅቶች ጋር በመሆን እንግዶች በሆቴሎች የሚኖራቸውን የቆይታ ጊዜ ምቹ ለማድረግ በቅንጅት እየሰሩ ነው ሲሉም ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል።

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com