የእለት ዜና

እሌኒ ገብረመድህን (ዶ/ር) የተባበሩት መንግሥታት ልማት ፕሮግራም በአፍሪካ የሥራ ፈጠራ ዋና ኃላፊ በመሆን ተሾሙ

እሌኒ ገብረመድህን (ዶ/ር) የተባበሩት መንግስታት ልማት ፕሮግራም በአፍሪካ ቀጠና የሥራ ፈጠራ ዋና ኃላፊ በመሆን ተሹመዋል።
የተባበሩት መንግስታት ልማት ፕሮግራም እንዳስታወቀው ከሆነ እሌኒ ገብረመድህን “ቲምቡክቱ” (timbuktoo) የተባለውን በአፍሪካ የግል፣ የመንግስትና የወጣቶችን ጅምር የፈጠራ ሥራዎች በገንዘብ አቅርቦት የሚደግፍ አዲስ ፕሮግራምን ለማስጀመር ግምባር ቀደም ሚና ይጫወታሉ።
“የአፍሪካን የወደፊት ተስፋ ለማሳደግ ዲጂታላይዜሽንን ማሳደግ እና ወጣቶችን ማበረታታት፤ በተባበሩት መንግስታት ልማት ፕሮግራም ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ተግባራት መካከል አንዱ እና ዋንኛው ነው።
ለዚህ አዲስ ተነሳሽነት ደግሞ የእሌኒ አመራር ትልቅ ተጽዕኖ ከማሳደሩም በላይ፤ የአፍሪካ ወጣቶችን ግዙፍ የፈጠራ እና የሥራ ፈጠራ ችሎታን ለማጎልበት እና ለማሻሻል የምናደርገውንምጥረት በእጅጉ ይደግፋል።”ሲሉ የተባበሩት መንግስታት ረዳት ዋና ጸሐፊ እና በተባበሩት መንግስታት ልማት ፕሮግራም የአፍሪካ ቀጠና ዳይሬክተር አሁንና ኢዚያኮንዋ ተናግረዋል።
በተባበሩት መንግስታት ልማት ፕሮግራም በአፍሪካ ልማት ተጽዕኖ ፈጣሪ ቡድን አባል የሆኑት እሌኒ የፈጠራ መፍትሄዎችን በመንደፍና ተግባራዊ በማድረግ ከ25 ዓመታት በላይ ልምድ ያላቸው ኢትዮጵያዊት ናቸው።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እሌኒ በአፍሪካ ልማት፣ በግብርና ገበያ፣ በሥራ ፈጠራ እና በወጣቶች የፈጠራ ችሎታ ላይ ከፍተኛ እውቅና፣ የተከበረ ድምጽና የአስተሳሰብ መሪነት ያላቸው ሴት ናቸው ሲልም እውቅናን ሰጥቷቸዋል።
እሌኒ ከአዲሱ ሀላፊነታቸው በፊት በግል እና የመንግስት ድርጅቶች ላይ በከፍተኛ የሥራ ሀላፊነቶች ያገለገሉ ሲሆን፣ በተለይም በኢትዮጵያ የወጣቶች መሪ ንግድ አፍላቂ፣ በብሉ ሞን፣ እንዲሁም በአፍሪካ ቀዳሚ የምርት ልውውጥ ገንቢ በሆነው በእሌኒ ኤል.ኤል.ሲ ውስጥ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሆነው ሰርተዋል።
እሌኒም በሦስት ዓመታት ውስጥ በዓመት 1.2 ቢሊዮን ዶላር የንግድ ዋጋ በማስመዝገብ ከፍተኛ ዕውቅና የተሰጠው የኢትዮጵያ ምርት ገበያ መሥራች እና የመጀመሪያ ሥራ አስፈፃሚም ነበሩ።
በተጨማሪም በዓለም ባንክ፣ በተባበሩት መንግስታት የንግድ እና ልማት ኮንፍረንስ እና በዓለም አቀፍ የምግብ ፖሊሲ ምርምር ኢንስቲትዩት ውስጥ ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎችን በመያዝ፤ በበርካታ የዓለም አቀፍ ኮርፖሬት እና ለትርፍ ያልተቋቋሙ ድርጅቶች ውስጥ በቦርድ አባል በመሆን አገልግለዋል።
ከስታንፎርድ ዩኒቨርስቲ በኢኮኖሚክስ ፒ.ኤች.ዲ ያገኙት እሌኒ በተለያዩ ጊዜያት ከፍተኛ ሽልማቶችንና እውቅናዎችንም ያገኙ ሲሆን፤ እ.ኤ.አ በ2020 ከምርጥ 50 ፈጣን እድገት ያስመዘገቡ ግለሰቦች ውስጥ እንዲሁም በ2016 እ.ኤ.አ ከምርጥ 5 አለም አቀፍ ተፅእኖ ፈጣሪ ሴቶች ውስጥ አንዷ በመሆን ተመርጠዋል።
እንዲሁም በሚያዚያ ወር እ.ኤ.አ 2013 በ”ኒውስዊክ” ከ125 አለም አቀፍ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሴቶች መካከል ስማቸው የተጠቀሰው እሌኒ፤ በ2012 በአፍሪካ ውስጥ ከ100 እጅግ ተደማጭ አፍሪካውያን መካከል የተሰየሙና፤ በተመሳሳይ ዓመት በአፍሪካ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ለውጥ “ያራ” ሽልማት እና የአፍሪካ የባንክ አዶ ሽልማትን ሌሎችንም አለም ዓቀፍ እውቅናና ሽልማቶችንም አግኝተዋል።
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n
Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com