የእለት ዜና

‹‹አገር ለቀው እንዲወጡ በታዘዙ የውጭ ዜጎች ላይ የተወሰደው እርምጃ ሕጋዊነትን ለማስፈን የተወሰነ፤ ለሌሎችም ትምህርት የሚሰጥ ነው›› -አምባሳደር ዲና ሙፍቲ

በዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ የሚሰሩና ከተሰማሩበት ዓላማ ውጪ የኢትዮጵያን ጥቅም በሚጎዳ ተግባር ላይ ተሰማርተው የተገኙ ሰባት የውጭ ዜጋ ሠራተኞች ላይ የተወሰደው እርምጃ ሕጋዊነትን ለማስፈን የተወሰነ፤ ለሌሎችም ትምህርት የሚሰጥ ነው ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ተናገሩ፡፡

በዓለም አቀፍ ድርጅቶች ውስጥ የሚሰሩ ሰባት ሠራተኞች በ72 ሰዓታት ውስጥ ከአገር እንዲወጡ የኢትዮጵያ መንግሥት ማዘዙን ተከትሎ ማብራሪያ የሰጡት አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፤ ግለሰቦቹ ከአገር እንዲወጡ የታዘዙት ከተሰጣቸው ኃላፊነት ውጪ ሲንቀሳቀሱና በሕገወጥ ተግባር ላይ ተሰማርተው በመገኘታቸው ነው፤ ይህ ደግሞ ሕጋዊነትን ለማስፈን የተወሰደ እርምጃ ሲሆን፤ ለሌሎችም ትምህርት የሚሰጥ ነው ብለዋል፡፡

እንደ አምባሳደር ዲና ገለጻ፤ ማንኛውም ዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ያልሆነ ተቋምም ሆነ ግለሰቦች ሲገቡ ፈቃድ አላቸው፡፡ የሚሰሩትም በፈቃድ ነው፡፡ የትኛውም ተቋምና ግለሰብ ከተሰጣቸው ፈቃድ ውጪ ሲንቀሳቀሱ ከተገኙ ተግባሩ ሕገወጥ ነው፡፡ ከአገር እንዲወጡ በታዘዙት ግለሰቦች የሆነውም ይሄው ነው፡፡

«አንዳንዱ ለሕክምና ሥራና ለጤና አገልግሎት ይመጣና፣ ጤናን በሚያዛቡና የኅብረተሰቡን ሰላም በሚያደፈርሱ ተግባራት ላይ ይሰማራል፡፡ ለውሃ ቁፋሮ ይመጣና አገር ሲቆፍር ይውላል፡፡ ይህ ዓይነት ተግባር ደግሞ በየትኛውም አገር አይፈቀድም፤» ያሉት አምባሳደር ዲና፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በሌላም አገር የአንድን አገር ሉዓላዊነት፣ የአንድን አገር ደህንነት፣ የአንድን አገር ሰላም የሚያደፈርሱ እንቅስቃሴዎች በሙሉ ክልክል መሆናቸውን አውስተዋል ሲል ኢፕድ ዘግቧል፡፡

መንግሥት ደግሞ እነዚህን ኃይሎች የማስቆም ኃላፊነት ያለበት እንደመሆኑ የኢትዮጵያ መንግሥት እርምጃም በዚህ መሠረት የተወሰደ ነው ሲሉም አስረድተዋል፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!