የእለት ዜና

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ተወልደ ገብረማርያም “በአየር እቃ ጭነት አገልግሎት አመራር” ዘርፍ ተሸለሙ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ ተወልደ ገብረማርያም “Flight Global” መስከረም 17 ቀን 2014 በለንደን ባዘጋጀው የአየር መንገዶች የቢዝነስ ስትራቴጂ ሽልማት ላይ “በአየር እቃ ጭነት አገልግሎት አመራር” ዘርፍ ተሸላሚ ሆነዋል።

ዋና ስራ አስፈፃሚው ወረርሽኙ በተከሰተበት ወቅት ላደረጉት የሚመሰገን የአየር እቃ ጭነት አገልግሎት አመራር ነው የኢትዮጵያ አየር መንገድን በመወከል የተሸለሙት።

ሽልማቱ በኮቪድ 19 ቀውስ ወቅት በዋና ሥራ አስፈፃሚው በኩል የተሰጡ የአየር መንገዱ ቀልጣፋ ስልቶችና የችግር አመራሮችን ዕውቅና ለመስጠት የተዘጋጀ ነው።

የንግድ ሥራ አፈፃፀም፣ የአውታረ መረብ ስትራቴጂና በችግሩ ጊዜ ያለው የፈጠራ አስተሳሰብ ለሽልማቱ ቁልፍ ከሆኑት መስፈርቶች መካከል ይገኙበታል።

ዋና ሥራ አስፈጻሚው “Flight Global እና የአየር መንገዶች የቢዝነስ ስትራቴጂ ሽልማት ዳኛ ፓነል የእኛን ልዩ የችግር አያያዝ ችሎታዎች፣ ቅልጥፍናን፣ የውሳኔ አሰጣጥን ፍጥነት፣ የፈጠራ ችሎታን እና የመቋቋም አቅማችንን አይተው ይህን ሽልማት በማግኘቴ በጣም ተደስቻለሁ።” ያሉ ሲሆን፤ በአጠቃላይ በዓለም ላይ የተከሰተው ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ግዙፍነት እና ውድመት ቢኖረውም በኢትዮጵያ አየር መንገድ በኩል ቀውሱን በተሳካ ሁኔታ ወደ ዕድል መቀየሩን ተናግረዋል።

በዚህ መሠረት እያደገ የመጣውን የጭነት ንግድ ተጠቅመን 25 የመንገደኛ አውሮፕላኖቻችንን ወደ የጭነት ማመላለሻዎች ቀይረናል ያሉት ተወልደ፤ ወሳኝ የህክምና አቅርቦቶችን እና ክትባቶችን በማቅረብ ለዓለም ማህበረሰብ መልካም ለማድረግ ጥረት አድርገናል ብለዋል።

አክለውም “ለሁሉም የኢትዮጵያ ማኔጅመንት ቡድን አባላት፣ ለዳይሬክተሮች ቦርድ እና ለ17 ሺህ ታታሪ ሠራተኞች በጣም አመሰግናለሁ። የአየር መንገዶች የቢዝነስ ስትራቴጂ ሽልማት እና ለFlight Global ለሽልማት ስለመረጡኝ ማመስገንም እፈልጋለሁ።” ብለዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዓለም ዙሪያ አስፈላጊ የህክምና አቅርቦቶችን በማመላለስ ውጤታማነቱ እንደ የአለም የምግብ ፕሮግራም ያሉ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እውቅና ሰጥተውታል።

አየር መንገዱ ከ50 ሚሊዮን በላይ የኮቪድ 10 ክትባቶችን ለተለያዩ አገሮች በማሰራጨትና የሰብአዊ አገልግሎት በመስጠት ረገድ ባደረገው ሚና አድናቆት አግኝቷል።
__________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!