የእለት ዜና

ኢትዮ ስኳር በ3 ቢሊዮን ብር የፋብሪካ ግንባታ መጀመሩን አስታወቀ

ኢትዮ ስኳር ማኑፋክቸሪግ ኢንዱስትሪ አክስዮን ማኅበር በደቡብ ኦሞ ዞን ሐመር ወረዳ ልዩ ሥሙ ቆርጫ ቀበሌ፣ በሦስት ቢሊዮን ብር የስኳር ፋብሪካ እየገነባ መሆኑን አስታውቋል።
የፋብሪካ ግንባታው ተጠናቆ በሙሉ አቅሙ ወደ ስኳር ምርት ለመግባት ሦስት ቢሊዮን ብር ይፈጃል ሲሉ የኢትዮ ስኳር ፕሮጀክት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ቢተው ዓለሙ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። ዋና ሥራ አስፈጻሚው አክለውም፣ አሁን ላይ በቅድመ ሁኔታ ለሸንኮራ አገዳ መትከያ የሚሆነውን ማሳ በማጽዳትና በማስተካከል የእርሻ ሥራው ተጀምሯል ብለዋል። የስኳር ምርት ሥራ ሰፊ ከመሆኑ አንጻር ወደ ምርት ለመግባት ሦስት ዓመት እንደሚፈጅም ጨምረው ተናግረዋል።

ፋብሪካው በ10 ሺሕ ሄክታር መሬት ላይ እንደሚገነባ የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ አያይዘውም የሚገነባበት ቦታ ለስኳር ምርት ምቹ መሆኑን፣ የአፈር ሁኔታውን፣ የአየር ንብረቱን እንዲሁም ውኃ ገብነቱን በማጥናት ማረጋገጥ ተችሏል ብለዋል።
እንዲሁም ቦታው አስቀድሞ በልማት ባንክ ሥር እንደነበር እና ኢትዮ ስኳር በጨረታ አሸንፎ ከልማት ባንከ እንደገዛው ጠቁመው፣ ለእርሻ ሥራ አስፈላጊ የሆኑ እንደ ትራክተር እና ዶዘር የመሳሰሉ ከ100 በላይ ሜካናይዘድ የእርሻ መሣሪያዎች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።

የአክስዮን ማኅበሩ ከተመሠረተ ከሦስት ዓመት በላይ ያስቆጠረ ቢሆንም አሁንም አክሲዮን በመሸጥ ላይ ይገኛል። መንግሥትም የአክሲዮን ድርሻ መግዛት ቢፈልግ እስከ 21 በመቶ ለመስጠት ቦርዱ የወሰነ ሲሆን፣ በዚህም መሠረት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለተማሪዎች በሚያደርገው የምገባ መርሃ ግብር ለተለያዩ አገልግሎቶች ስኳር መፈለጉ ስለማይቀር አክሲዮን እንዲገዛ ግብዣ እንደቀረበለትም ነው የፕሮጀክቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ቢተው የተናገሩት።

ኢትዮ ስኳር ግንባታውን አጠናቅቆ ምርት ሲጀምር፣ ከስምንት እስከ ዐስር ኩንታል ከሚደርሰው የኢትዮጵያ ዓመታዊ የስኳር አቅርቦት ፍላጎት ውስጥ 10 በመቶ የሚሸፍን ይሆናል ብለዋል። ይህም የፋብሪካው የማምረት አቅም በዓመት አንድ ሚሊዮን ኩንታል እንደሚሆን ያሳያል።
ፋብሪካው በዋናነት ሊያጋጥመው የሚችለውን የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት ችግር ለመፍታት እንደ መፍትሄ፣ በስኳር ሥራ ላይ ሰባ ዓመት የሥራ ልምድ ካለው ታዋቂ የቤልጅየም ኩባንያ ጋር ለመሥራት እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል።

አክስዮን ማኅበሩ ትኩረቱ ከሆነው የስኳር ምርት በተጓዳኝ የተለያዩ ሥራዎችን እንደሚያከናውን ያስታወቀ ሲሆን፣ ለአብነትም ሽቶዎችን ማምረት፣ ወረቀት እና የእንስሳት መኖ፣ ለሕክምና የሚውል አልኮል፣ ከረሜላ እና ቼኮሌት እንዲሁም ኢታኖልና ሞላሰስ ብሎም የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ይገኙበታል።

በተጨማሪም የማኑፋክቸሪንግ እና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ (IT) ኮሌጅ እንደሚከፈት፣ የስኳር ቱሪዝምና የባህል ትዕይንት መዝናኛዎችን የሚያካትት ሎጅ እንደሚኖሩት ተገልጿል። ይህም ፋብሪካውን በኢትዮጵያ ካሉ ሌሎች የስኳር ፋብሪካዎች የተሻለ እና ትርፋማ ከማድረግም በላይ ስኳርን በዝቅተኛ ዋጋ ለገበያ ለማቅረብ እንደሚረዳ ከወዲሁ ታምኖበታል።

‹‹እንደዚህ ዓይነት ፕሮጀክት ሲጀመር የመጀመሪያው ድርጊት ከማኅበረሰቡ ጋር መተዋወቅ እና መግባባት በመሆኑ፣ ኢትዮ ስኳር ፋብሪካም በአካባቢው ማኅበረሰብ የትውውቅ ባህል መሠረት ትውውቅና ምርቃት አድርጎ እንቅስቃሴውን ጀምሯል›› ያሉት የፕሮጀክቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ፣ እንዲሁም የአካባቢው ማኅበረሰብ አርብቶ አደር በመሆኑ የውኃ እና የከብት መኖ አቅርቦት እገዛ እንዲያደርግላቸው ፋብሪካውን የጠየቁ መሆኑን አክለው ተናግረዋል።

ጥያቄያቸውን ተከትሎ ለማሳዎች ቅርብ የሆኑ ኩሬዎች በሚዘጋጁበት ጊዜ አርብቶ አደሮችም ከብቶቻቸውን ማጠጣት እንዲችሉ ሆኖ እንደሚዘጋጅና ለአካባቢው ማኅበረሰብ ከሥራ ዕድል ፈጠራ በተጨማሪ ፋብሪካው በብዙ መልኩ እንዲጠቅም ለማድረግ እንደታለመ ነው ዋና ሥራ አስፈጻሚው ቢተው ዓለሙ ለአዲስ ማለዳ የገለጹት።


ቅጽ 3 ቁጥር 152 መስከረም 22 2014
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

Comments: 2

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!