የእለት ዜና

በኢትዮጵያ ‹እንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍነት› – ይብቃ!

በኢትዮጵያ ሰሜኑ ክፍል ከወራት በፊት ትንሽ መስሎ የጀመረ የቃላት ጉሸማ አሁን ከወራት በኋላ የከፋ ጦርነት ላይ ደርሷል። ይህም የብዙዎችን ሕይወት ነጥቋል፣ እልፎችን አፈናቅሏል፣ ከዛ የሚልቁትን ለረሀብና እንግልት ዳርጓል። እንዲሁም ደግሞ ኹለት ጽንፎችን አሳይቷል። በአንድ በኩል በሃይማኖት አጥር እንኳ የማይመለስ የሰዎች ጭካኔን ሲሆን በሌላ በኩል ሰብአዊነት በምንም መስፈርት እንደማይመዘን ያመላከተ የበጎ አድራጎት ሥራ ነው። ያም ይህም ሆኖ፣ ዛሬ ላይ ደርሰናል።

አገራችን ትፈርስ ይሆን? እንደ ሶርያ የማንሆንበት ምን የተለየ ነገር አለን? ከዚህ ወደከፋ ደረጃ ብንደርስስ? አሁንስ ተስፋችን ማን ነው? ብዙዎች በሐሳብና በልባቸው የሚያመላልሱት ሐሳብና ጥያቄ ነው። አንዳንዶች በፍጹም ተስፋ መቁረጥ የሚሆነውን በመታዘብ ላይ ይገኛሉ። በዚህ የተነሳ ወጣቶች ወደ ሱሰኝነት ይገባሉ፤ ራስ ወዳዶች የሕዝቡን ስቃይ የሚጨምር ስግብግብነታቸውን ያጧጡፋሉ፣ ዘራፊዎች ከጨለማው እኩል በብርሃን የመዝረፍ ‹ወኔ› ያገኛሉ። ይህ አሁን በአገራችን በየአቅጣጫው የምናየው እውነት ሆኗል።

አጥኚዎች ታሪክን እንዲሁም ወቅታዊ የዓለምን መልክ መነሻ አድርገው ባቀረቡት ሐሳብ፤ አገራት እንዲበታተኑና እንዲፈርሱ የሚያደርጋቸው ምክንያት ግጭትና ጦርነት ብቻ አይደለም። ምንም እንኳ ወደ ግጭት የመምራት እድላቸው ሰፊ ቢሆንም በፖለቲካ ብቻ ሳይሆን በምጣኔ ሀብት ችግሮችና በማኅበራዊ ስርዓት መፋለስ የተነሳ የተበተኑ፣ ዜጎቻቸውም ከጦርነት ባልተናነሰ ረሀብና ችግር ውስጥ የሚገኙ አገራት አሉ።

አዎን! አገር በጦርነት ብቻ አይፈርስም። አገርን ወታደር በመሆን ብቻም ማዳንና መጠበቅ አይቻልም። በአንድ አገር ጦርነት የለም ማለት ሰላምና እድገት አለ ማለት እንዳልሆነ ሁሉ፣ ጦርነት አለ ማለት አገር ፈጽሞ ይፈርሳል ማለትም አይደለም። በጦርነት ላይ ከሚሳተፉ ወታደሮች በተጓዳኝ ዜጎች በየመስካቸው ባሉበት የሚሠሩትና የሚወስዱት ድርሻ ግን አንዲት አገር በጦርነት አልፋ እንድታሸንፍ አልያም በጦርነት መካከል ቀርታ እንድትሸነፍ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል አዲስ ማለዳ በጽኑ ታምናለች።

ባሏ ዘመቻ የሄደ ሚስት፣ ‹አባታችሁ ተመልሶ አይመጣምና ምን ዋጋ አለው!› ብላ ቤቷን አፍርሳ ልጆቿን አትበትንም። ይልቁንም ባሏ እንደሚመለስ ተስፋ በማድረግ ልጆቻቸውን እየተንከባከበች፣ ቤታቸውንም እየጠበቀች ትቆያለች። እንደዛ ካልሆነ የባሏ ጦር ሜዳ መዝመት ዋጋ የለውም። ስለማን ብሎስ ነው የሚደክመው? መስዋዕትነት የሚከፍለውስ ስለማን ሆነና? ምንም የሚያጣው ነገር የሌለው ሰው ሰነፍ ነው፤ ብዙ ሊያጣ የሚችለው ነገር ያለው ግን ጸንቶ ይበረታል።

ኢትዮጵያ አሁን ላይ ሰላሟ እንዲመለስ በምትወስደው አማራጭ ሁሉ፣ ሁሉም እያንዳንዱ ዜጋዋ የየራሱ ድርሻ አለው። እንደተባለው አንዳንዱ ወታደር ሆኖ የሚያገለግል፣ አንዳንዱ ደግሞ በአካባቢው ላሉ የቀን ሠራተኞች ዳቦና ሻይ በማቅረብ የሚሠራ ሊሆን ይችላል።
ነገሩን እንደ አገር አስፍተን ስናየው ጠጠር በጋን ይደገፋል እንዲሉ በአገር ሥራ ላይ የሚበላለጥ ወይም ትንሽ ትልቅ የሚባል ድርሻ የለም። ንግድ፣ ቱሪዝም፣ ባህል፣ ጥበብ፣ ምርምርና ጥናት፣ ትምህርት ወዘተ በየዘርፉ የሚያገለግሉ ሠራተኞች አሉ። የእነዚህ ሰዎች ሥራ አገርን ለማስቀጠል ከወታደር የሚጎዳኝ ድርሻ አለው። በሚገባ ኃላፊነታቸውን ካልተወጡ ግን፣ በነባራዊው እውነት ለኢትዮጵያ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንደሚሆኑባት ጥርጥር የለውም።

ለኢትዮጵያ አሁን ላይ ጆሮ ደግፍ ከሆኑባት መካከል ‹ነጋዴዎች› ቀዳሚ ናቸው። ገንዘብ ብዙ ቢሰበስቡ ለብቻቸው ይኖሩ ይመስል፣ ከእጥፍ በላይ ለማትረፍ የሚዳክሩት ጥቂት አይደሉም። በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ዋጋን ለመጨመር የሚደረግ ‹ጥረት› አልያም ዋጋ ለመጨመር አጋጣሚ ለመፍጠር የሚታየው ‹ድካም› እጅግ አሳዛኝ ነው።

አንዳንዴ ከጠላት አገር ዘርፋችሁ አምጡ የተባሉ ይመስላሉ። ይህን በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ባሉ ታክሲ ተራዎች በሰዎች ችግር ለመነገድ በሚደረገው ጥረት በሚገባ ማየት ይቻላል። በተለይ ማምሻው ላይ ሰዎች ተቸግረው አማራጭ በማጣት ለተባሉት ሁሉ የሚታዘዙበትን ሰዓት ቁጭ ብለው የሚጠባበቁ አሽከርካሪዎችን ታዝበናለ።

ግጭት ባለባቸው አካባቢ የተፈናቀሉ ዜጎች ላይ የቤት ኪራይን ጨምሮ የሸቀጥ ዋጋ ተቆልሎባቸው፣ እንደ ቱሪስት በወጪ የተቀበሏቸው ስግብግብ ‹ሰዎች› እንዳሉ በቅርብ ታዝበናል።
ይህ በአደባባይ የሚታይ ስለሆነ እንጂ በየቢሮው አጥራቸው ሆነው ሕዝብን የሚያስመርሩና የሚያሳዝኑ፣ አጋጣሚዎችን ለራሳቸው ጥቅም ለማዋል የሚዋደቁ ሰዎች አሉ። እነዚህ ሰዎች በተገልጋይ ዜጎች ላይ ተስፋ መቁረጥን፣ በስርዓትም ላይ ድክመትን ያባብሳሉ። በዛም መሠረት ነጋዴው በግብር አስከፋይ ተቋም፣ አሽከርካሪው በትራፊክ፣ ባለቢሮው በተሿሚ አለቃው ወዘተ ሁሉም በየደረጃው ‹የእጁን› ያገኛል። አዙሪቱ በዚህ መልክ ይቀጥላል።

እንደ ኢትዮጵያዊ የምንመካባቸው ሰብአዊነትና ርኅራሄ አለው የምንለው ማንነታችን በአንድ የሰፈር የታክሲ ተራ ፉርሽ ሆኖ እንመለከታለን። ይህ አገርን ከጦርነት በላይ የሚጎዳ የትውልድ መፍረስ መቅድሙ እንደሆነ አዲስ ማለዳ ታምናለች።
ኢትዮጵያ አሁን እንቅርት በሆኑባት የውስጥ ችግርና የውጪ ተጽእኖዎች ላይ የጆሮ ደግፍ የሆነ ሕመምና ሸክም አንሁንባት። ሲሆን በያለንበት አሉባልታና ወሬን እያናፈሱ ከመጨነቅና ከማስጨነቅ፣ ምንም ረብ በሌለው ነገር ጊዜን ከማባከን ሥራችንን በሚገባ እየሠራን የተረፈውን እንጠብቅ።

ሁሌም መንግሥት ላይ ብቻ ጣት መቀሰር ሳይሆን እንደ ሕዝብ፣ እንደ ማኅበረሰብ እንከኖቻችንን እየተመለከትን እንታረም። ይህ ጊዜ ሲያልፍ ምን እየሠራችሁ ነበር ሲባል ከመንጠቅ፣ ከመዝረፍና የየራሳችንን ቋት ከመሙላት የተሻለ ቁምነገር ለአገራችን ሠርተን የተገኘን ለመሆን እንጣር።

አገርን የሚያፈርሰው ጦር የታጠቀ ጠላት ብቻ አይደለም። በዝንጋኤ፣ በቸልታ፣ በግዴለሽነት፣ በተስፋ መቁረጥ፣ በራስ ወዳድነት…በብዙ እንደ ሕዝብና ማኅበረሰብ በሚስተዋሉ ችግሮች ምክንያትም ነው። ከጥቂቶች ሐሰት ይልቅ የብዙዎች እውነት ለማሸነፍ ጊዜ የሚወስድባት፣ ብዙዎቹ ሥራቸውን ዘንግተው ከጥቂቶቹ ጋር ፍልሚያ ስለሚገጥሙ ነው።

ኢትዮጵያ አሁን ላይ አቅንታ ወደ እድገቷ የምታይበት አንገቷ ላይ እንቅርት የተባለ ብዙ ማነቆና ችግር አርፎባታል። በሰሜኑ ያለው ጦርነት፣ ውጪ አገራት ተጽእኖና የሕዳሴ ግድብ፣ የጎረቤት አገራት ነጋ ጠባ የሚፈጥሩት አዲስ አጀንዳ፣ የኑሮ ውድነትና በዛ ላይ እንደ ሰው የማይታገሉት የኮቪድ 19 ወረርሽኝ። በዚህ ሁሉ ችግሯ ላይ ተደርቦ ዜጎችን በማማረርና ኑሮን በማክበድ እንደ ጆሮ ደግፍ መሆን ይብቃ ስትል አዲስ ማለዳ አጽንዖት ትሰጣለች።


ቅጽ 3 ቁጥር 152 መስከረም 22 2014
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com