የእለት ዜና

‹‹የአገር ዐቀፍ የካርታ መረጃ ለኹሉም ተቋማት ግዴታ ነው››

ቴዎድሮስ ካሳሁን በኢትዮጵያ ጂኦስፓሻል ኢንፎርሜሽን ኢንሰቲትዩት የካርታ ሥራ ዲፓርትመንት ዳይሬክተር

ቴዎድሮስ ካሳሁን ይባላሉ። በቀድሞው የካርታ ሥራዎች ድርጅት፣ በአሁኑ የኢትዮጵያ ጂኦስፓሻል ኢንፎርሜሽን ኢንሰቲትዩት ውስጥ የካርታ ሥራ ዲፓርትመንት ዳይሬክተር ናቸው። ከስድስት ዓመት በፊት ተቋሙን የተቀላቀሉት ቴዎድሮስ፣ ከዛ በፊት ለሦስት ዓመት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የሲቪክስ መምህር ነበሩ። በመቀጠልም የትምህርት ቤቱ ምክትል ርዕሰ መምህር በመሆን አገልግለዋል።
በጂኦስፓሻል መሥሪያ ቤት ለመጀመሪያ ጊዜ ሲቀጠሩ በዲፕሎማ ደረጃ ዲግሪ ይዘው የነበረ ቢሆንም፣ ቀስ በቀስ ዕድገት በማግኘት የፎቶግራሜትሪክ ቴክኒሺያን፣ ከዛም የካርቶግራፊ ባለሙያ ሆነው አገልግለዋል። ላለፉት አራት ዓመታት በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ከሠሩ በኋላ ከባለፈው ዓመት ጀምሮ የካርታ ሥራዎች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ። ተቋሙ በቀጣይ ሊያከናውናቸው ካሰባቸው ተግባራት መካከል በቴክኖሎጂ የተደገፈ የካርታ አገልግሎት አንዱ መሆኑን ተከትሎ የአዲስ ማለዳዋ ሰላማዊት መንገሻ የካርታና ካርታ ነክ ተያያዥ ጥያቄዎችን በማንሳት ከቴዎድሮስ ካሳሁን ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርጋለች።

የጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት የተባለው ተቋም ማነው?
ኅብረተሰቡ የካርታ ሥራዎች የሚለውን የቀድሞ ሥሙን በደንብ ያውቀዋል። የአሁኑን የኢትዮጵያ ጂኦስፓሻል ኢንፎርሜሽን ኢንስቲትዩት የሚለውን ሥያሜውን የሚያውቀው በጣም ጥቂት ሰው ነው። ተቋሙ የካርታ መረጃዎችን የሚሰጥ ሲሆን ለውሳኔ ሰጪዎች ወሳኝ የሆነ ተቋም ነው። እዚህ አገር ላይ ማንኛውም ልማት ከታሰበ የካርታ ሥራ መረጃዎች ማግኘት ያስፈልጋል። ለመንገድ ግንባታ፣ ለተቋራጭ ሥራዎች፣ ለእርሻና ለይዞታ ሥራ የሚያግዝ መረጃ የሚሰጥ ነው።

የካርታ ሥራ ድርጅት በወረቀትም ሆነ በሶፍት ኮፒ የተሟሉ መረጃዎችን በማካተት ለሚፈልገው አካል የሚሰጥ ነው። እንደነ ጎግል ማፕ (Google Map) እና ጎግል ኧርዝ (Google Earth) ያሉ አካባቢዎችን የሚጠቁመን ባይኖር ምን እንሆን ነበር የሚሉ ሰዎች አሉ። ምላሹ በግምት መሄድ ወይ ደግሞ ሰው መጠየቅ ነው። እንደነዚህ ያሉ መረጃዎችን በማሰባሰብ ለሕዝቡ ኑሮን የማቅለል ሥራ የሚሠራ ድርጅት ነው።

እንደ አገር በዐስር ዓመት ዕቀድ ውስጥ የተካተተው የካርታ ሥራ ምንድነው?
ተቋማችን በሚቀጥሉት ዐሥር ዓመታት ሊሠራ ካሰባቸው ሥራዎች መካከል ሦስት ዋና ዋና ነገሮች አሉ። እነዛም የከፍተኛ ካርታ መስፈርት፣ ታማኝ እና ባለቤትነት ያለው የካርታ አገልግሎት መስጠት ናቸው።
የከፍተኛ ካርታ መስፈርት ማለት በአገራችን ያሉ ካርታዎች አንድ ለኹለት ሚሊዮንኛ እና አንድ ለ20 ሺሕኛ ናቸው። ይህ ቁጥር በጨመረ ጊዜ ዝቅተኛ የሆነ መስፈርት ይኖረዋል። ቁጥሩ ሲቀንስ ደግሞ ከፍተኛ መስፈርት ይባላል።
አዲስ የታሰበው ትልቅ ምስል አንድ ለ10 ሺሕኛ ነው። ይህ ደግሞ የነበረውን በግማሽ የሚቀንስ ነው። ለምሳሌ፣ ስልክ ላይ ፎቶውን ስናይ ጠቅላላ ከተማውን እናያለን፤ እየቀረበ ሲመጣ በጥልቀት የምንፈልገውን እናያለን። ከላይ ኢትዮጵያን ዐይተን፣ ከኢትዮጵያ አዲስ አበባን ከዛም የምንፈልገውን ሰፈርና አካባቢ ለማየት የሚያስችል ማለት ነው።

አሁን በተቋማችን ደረጃ ያለው መረጃ ከፍ ብሎ ያለ ሲሆን፣ በኢትዮጵያና ጠቅላላ ከተሞች ደረጃ ያለውን ዕይታ ማየት የሚያስችል ነው። ለመሥራት የታቀደው ደግሞ አዲስ፣ በዳታ የሚሠራ ካርታ በከተማ የነበረውን ወደ ሰፈር እና አካባቢ የሚያዳርስ ነው። ዝቅተኛ ሽፋናችን 50 ሺሕ ስኬል መቶ በመቶ የተሳካ አፈጻጸም ተቋሙ ያስመዘገበ ሲሆን፣ በ10 ሺሕ ስኬል 2.5 በመቶ የሆነ አፈጻጸም ያለው ነው።

ይህ ደግሞ የኢትዮጵያን የቆዳ ስፋት 2.5 በመቶ ብቻ ነው የሸፈነው። አሁን በምንሄድበት አዝማሚያ የሚቀጥል ከሆነ አጠቃላይ ኢትዮጵያን ካርታ ሠርቶ ለመሸፈን 200 ዓመት ሊፈጅ ይችላል። ይህ ደግሞ ተቋሙ ምንም ዓይነት ሥራዎችን ቢሠራም ትርፉ ልፋት ብቻ ነው የሚሆነው። ስለዚህ ይህንን 200 ዓመት ሊፈጅ የሚችለውን የካርታ ሥራ በ10 ዓመት ፈጽሞ ቢያንስ አገሪቱ በምትፈልገው ደረጃ ያህል ከስር ከስር ለማቅረብ ያለመ ነው። ካልሆነ ደግሞ ከፍተኛ ልማት በሚከናወንባቸው በተመረጡ ቦታዎች ብቻ መረጃ በመሰብሰብ በኹለት ዓመት ውስጥ ወደ ተግባር ለመግባት ታቅዷል።

ይህ ሲሆን ከፍተኛ መስፈርት ካርታ የሚያሟሉ ሦስት መሠረታዊ ጉዳዮች አሉ። አንደኛው ካርታ ማምረት ነው። ካርታ ማምረት ማለት በወረቀት እና በሶፍት ኮፒ የአገሪቷን ገጽታ ሠርቶ ማሳየት ነው። ይህን ለማከናወን ካርታ ሥራዎች ድርጅት አንዱ ተቋም ነው።

‹ጎግል ማፕ› እያለ የካርታ ሥራ ድርጅት ለምን አስፈለገ?
ተቋሙ ያስፈለገበት ዋና ምክንያት ተዓማኒነት ነው። ማንኛውም ሰው የሚጠቀመው ጎግል ማፕ ለሁሉም ሰው ክፍት የሆነ ነው። የጎግል አካውንት ያለው ሰው በሙሉ መረጃውን በመቀየር እንደፈለገ የሰፈሮችን ሥም መጻፍ ይችላል። ለምሳሌ ለልማት የተቋቋመን ድርጅት የስደተኞች ካምፕ ነው በማለት ሥያሜ መስጠት ይችላሉ። መረጃውን ማቅረብ እንዳለ ሆኖ በተሳሳተ መንገድ ሰዎች ላይ መጉላላት ይፈጥራሉ።

ስለዚህ እንዲህ ዓይነት ችግር እንዳይፈጠር ታማኝ የሆነ ተቋም በመንግሥት ተቋቁሟል። መንግሥት በአዋጅ ኃላፊነት ሰጥቶ ያቋቋመው ድርጅት የካርታ ሥራ በመሆኑ በአገሪቱ የተመረተ ማንኛውም መረጃ የሚቆጣጠርና ፍቃድ የሚሰጥ ነው። ይህ ማለት ኅብረተሰቡ መረጃዎች ከታማኝ ምንጭ እንዲያገኝ በማድረግ ከመሥራቱም በላይ በሌሎች አካላት የተሠሩትን የማረጋገጥ ተግባር አለው።

ጎግል ማፕ በውጭ አካላት የተሠራ መረጃ ስለሆነ እንደ አገር መረጃውን ለማግኘት መክፈል ወይም መስረቅ አለብን። ስለዚህ መረጃዎች በሙሉ በውጭ አካላት የሚሠሩ ስለሆኑ የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ መረጃ አይኖረውም ማለት ነው። ይህን ደግሞ በአገራችን የተሠራ በማድረግ የኢኮኖሚ ጥቅም ማስገኘት ይገባዋል። ከዚህ በተጨማሪ እንደ አገር የከፍታ መረጃ ባለመኖሩ የተለያዩ ችግሮች እየተፈጠሩ ነው። ለምሳሌ ያለአግባብ የተሠሩ መንገዶችን ዐይተን ለምን እንደዚህ ተሠራ እያልን እንተቻለን። ይህ የመጣው የከፍታ መረጃ ባለመኖሩ ነው። ስለዚህ መንገዶች፣ ድልድዮች፣ ግድቦችና እና የእርሻ ሥራ ለመሥራት የከፍታ መረጃ አስፋላጊ ነው።

ተቋማችን የት አካባቢ ነው ዳገታማ እና ሜዳማ በማለት የመለየት ሥራንም ይሠራል። እርሻም ሆነ ሌሎች ልማቶች እንዴት መከናወን አለባቸው የሚለውንም የመለየት ተግባር በማከናወን ውጤታማ ሥራ ለመሥራት ያስችላል።
ዓባይ ግድብ የሚገደብበት ቦታ የተመረጠው ካለው አካባቢያዊ የኢኮኖሚ ጠቀሜታ እና የመሬት አቀማመጥ በከፍታ መረጃ በመገንዘብ ነው። በአሁኑ ሰዓት በተቋሙ አፈጻጻም መሠረት በአገሪቱ 43 በመቶ የከፍታ መረጃ ያለ ሲሆን፣ በዚህ 10 ዓመት ውስጥ መቶ በመቶ ለማከናወን እየተሠራ ይገኛል። በዚህ የከፍታ መረጃ የመንገድ ትራንስፖርት፣ ሥራ ተቋራጭ ድርጅቶች እና በርካታ ግለሰቦች ይጠቀሙበታል።

በተለያዩ አካባቢዎች የመጠቆሚያ አድራሻ የተሠሩት ለምን አገልግሎት ነው?
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና በከተማ ልማት ኮንስትራክሽን አማካይነት የተሠሩት እነዚህ መጠቆሚያዎች ለበርካታ አገልግሎቶች ተፈልገው የተሠሩ ናቸው። የተቋማትና የግለሰቦችን ፍላጎት ለማሟላት የካርታ መስፈርት፣ የከፍታ መረጃ እና ቀጥተኛ አድራሻ ያስፈልጋል። አሁን ያለው የተለመደው አገልግሎት ሰዎች ያሉበትን ቦታ እና መድረስ የሚፈልጉበትን ቦታ በመናገር የመጓጓዣ እና የዴሊቨሪ አገልግሎት ማግኘት የሚችሉበት ነው።

ይህን አገልግሎት የሚያገኙት በውጭ አካላት በተሠሩ መረጃዎች ነው። ይህ የውጭ አካላት የሚሠሩት መረጃ ታማኝነት ከማጣቱም በላይ የባለቤትነት ጉዳይ ሊያስነሳ ይችላል። እነዚህ የውጭ አካላት ክፍያ እንኳን ቢጠይቁ መክፈል ግዴታ ሊሆን ነው።
ይህንን የውጭ አካላትን ሥራ በአገር ደረጃ በባለቤትነት ወስደን የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ከተማዎችን ለማዘመን መንገዶች ሥም በቁጥር ለመተካት ያቀደ ሥራ ጀምሮ ነበር። በተለምዶ የሰፈር ሥያሜን ለማስቀረትና ዘመናዊ አሠራርን ለመከተል በየሰፈሩ የሚቆሙ ታፔላዎች በመትከል ክፍለ ከተማውን፣ ወረዳውንና ቀበሌውን የሚገልጽ ለኹለተኛ ጊዜ የተሞከረ የመንገድ ላይ አድራሻ (street addressing) ነው። ይህም ሰዎች በሰፈር ሥያሜ ሳይሆን በመንገድ ቁጥር በመግለጽ በትክክል ቦታው ላይ እንዲመጡ ያደርጋል። ዋናው ጥቅም ደግሞ በትክክል ቦታው ላይ የመገኘት ዕድል መፍጠሩ ሲሆን፣ በመቀጠል የከተማዋን ዘመናዊነት እና የሰዎችን ኑሮ ቀላል የማድረግ ትልቅ ጥቅም አለው።

ስለዚህ በ10 ዓመት ዕቅድ የሚሠራው የተቋሙ የካርታ ሥራ ዘመናዊነትና ታማኝነት በተላበሰ መልኩ ባለቤት ያለው አገልግሎት የሚሰጥ ነው። በአሁኑ ሰዓት የሙከራ ሥራ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የተጀመረ ሲሆን፣ በ73 ከተሞች ተግባራዊ ለማድረግ ዕቅድ ይዘናል።
በአብዛኛው አዲስ አበባ ባሉ 10 ክፍለ ከተሞች የሚተገበረው ይህ የካርታ ሥራ አገልግሎት፣ የከተማዋ የመንገድ አሠራር እና የኑሮ ሁኔታ ውስብስብ በመሆኑ ለማስተካከል እንኳን ቢፈለግ ወደ ክልል ከመሄዱ በፊት ቶሎ ማስተካከል እንዲቻል ዕድል ይፈጥራል።
ለሙከራ የተሠራበት ክፍለ ከተማ በ2013 የተጀመረ ሲሆን፣ በዚህ ዓመት የተሰበሰበውን አጠቃላይ መረጃ ወደ ሥርዓት (ሲስተም) ገብቶ ተግባራዊ ለማድረግ ታቅዷል። ይህ ሙከራ ከተሳካ በኹሉም ክፈለ ከተማዎች በመዘዋወር መረጃ በመሰብሰብ ኅብረተሰቡ እንደ ጎግል ማፕ እንዲጠቀም ይደረጋል።

ይህ ካርታ በአገር ኢኮኖሚ ላይ ያለው ጠቀሜታ ምንድነው?
በኢኮኖሚ በኩል ለከፍታ መረጃ ዳታ የሚሆን ወጪ እስከአሁን እንደ አገር አውጥተን አናውቅም። ለምሳሌ አንድ የከፍታ መረጃ የሚፈልግ ግለሰብ በራሱ ወጪ ለመሥራት ቢያስብ እጅግ ከፍተኛ ገንዘብ ማውጣት ይኖርበታል። ከገንዘቡም በላይ በባለሙያ ላይሠራ ይችላል። የጂኦስፓሻል ተቋም ግን የ60 ዓመት ልምድ ያለው በመሆኑ እና ወጪን ለመቆጠብ ሲባል በኛ ተቋም የጂኦስፓሻል መረጃን ለማምረት እየሠራ ነው።

ስለዚህ የውጭ አካላት ከሚያመርቱት ይልቅ በአገር ውስጥ ተቋም በመሥራት ጥራቱን የጠበቀ መረጃ መሰብሰብ እና ወጪን መቀነስ ይቻላል። ከዚህ በተጨማሪ ይህን ዳታ ለመሥራት እንደ አገር አንድ ጊዜ ብቻ ወጪ በማውጣት በቀጣይ ጊዜ ደግሞ በማሻሻል ለተጨማሪ ወጪ የሚዳረጉትን ያስቀራል።

ተቋሙ በዲጂታል ቴክኖሎጂ መሥራት በጀመረ በስድስት ዓመታት ውስጥ የካርታ ዳታ ለመሥራት ያቀደ ቢሆንም፣ በሚቀጥሉት አስር ዓመታት ይህንን ቴክኖሎጂ መሥራቱ በቀጣይ መንግሥት ምንም ወጪ እንዳያወጣ ያደርገዋል። ነገር ግን በአንድ ጊዜ ብዙ ገንዘብ ፈሰስ ማድረግ አለበት። በመሆኑም አሁን በሙከራ ላይ የሚገኘው የካርታ መረጃ ሥራ ስምንት ቢሊዮን ብር የሚፈጅ ሲሆን፣ በሂደት ቴክኖሎጂዎች እየተቀየሩ ሲመጡ እንዲሻሻል ለማድረግ የሚመች ሆኖ የሚሠራ ነው።

ይህ ቴክኖሎጂ ስለሆነ እንደ ማንኛውም መሠረተ ልማት የሚፈርስ፣ የሚበላሽ እና የሚያረጅ አይደለም። ቴክኖሎጂውን የሚጠቀሙት የአገልግሎት ክፍያ በመክፈል ስለሆነ ትልቅ ገቢ ማስገኘት የሚያስችል ነው። የዚህ ቴክኖሎጂ ወጪ ስምንት ቢሊዮን ብር ቢሆንም፣ 50 ቢሊዮን ብር ደግሞ ዓመታዊ ገቢ ለማግኘት የሚያስችል ተደርጎ የሚሠራ ነው።

በውጭ አካላት የተሠራውን የካርታ መረጃ ለማግኘት በዶላር የሚከፈለውንም ገንዘብ መቆጠብ የሚያስችል ነው። ከዚህ በተጨማሪ መረጃውን የሚፈልገው አካል ተቋሙን በቅርብ ማግኘት ስለሚችል በኢሜይል አድራሻ ደብዳቤ መጻጻፍ አይጠበቅበትም። ያለምንም ውጣውረድ አንድ የመጠየቂያ ደብዳቤ በመጻፍ ከጂኦስፓሻል መረጃ ማግኘት ይቻላል።

በተለይ ደግሞ በቅርቡ ያከናወነውን የላይዳር ቴክኖሎጂ ግዢ አሠራሩን ይበልጥ ያቀላጥፍለታል። የላይዳር ቴክኖሎጂ በቀንም ሆነ በማታ የሚሠራ የመሬትን እና በመሬት ላይ ያሉ ቁሶችን አቀማመጥ፣ ቅርጽና ከፍታ በሚሊሜትር ትክክለኛነት የሚሰበስብ የጂኦስፓሻል ቴክኖሎጂ ነው። ይህ ቴክኖሎጂ የመብራት ገመዶችን የመሰሉ ቀጫጭን ቁሶችን መለየት እና ሞዴል ማድረግ የሚችል መሣሪያ ሲሆን፣ ከዚህም በተጨማሪ ከደን ውስጥ ያሉ ቁሶችንና የመሬት አቀማመጥን ደኑን ዘልቆ በመግባት መሰብሰብ የሚያስችል ነው።

ኅብረተሰቡ በአጠቃላይ በጉዳዩ ላይ ያለውን ግንዛቤ በማሳደግ እንዴት በቀላሉ መተግበር ይቻላል?
የስፓሻል ዳታ (የካርታ መረጃ) ትልቁ ችግር ሰዎች ፍላጎት እያላቸው መረዳት አለመቻላቸው ነው። አሠራሩ እና ሂደቱ አብዛኛውን ነገሮች ስለሚያቀልላቸው ሰዎች ከተለመደው አሠራር ለመውጣት እንደ ከባድ የማየት ችግር አለ።
የካርታ መረጃ ሰዎች በቀላሉ እንዲረዱት ተቋሙ በርካታ ሥራዎችን ሠርቷል። ነገር ግን ስለ ካርታ ብቻ እንጂ ዘመናዊ ወደ ሆነው የመንገዶች ቁጥር ወይም ቴክኖሎጂ አልተሸጋገሩም። ይህን መፍጠር የሚቻለው በሂደት ነው። ለምሳሌ የታክሲ አገልግሎት ከመነሻ መዳረሻ የሚለውን በታፔላ መሆን ሲጀምር ሰዎች ግራ ተጋብተው ነበር። ነገር ግን በሂደት ተላምደውታል።

ሌላኛው ቀላል ምሳሌ ቴሌ ብር ነው። ኢትዮ ቴሌኮም ያለውን አሠራር በሙሉ በቴሌ ብር በኩል በማድረግ ሰዎች ወደው ሳይሆን በግድ ወደ ሲስተሙ ማስገባት ችሏል። አሁን ወደ ተግባር የሚገባው የካርታ መረጃም እንደዚሁ ነው። መንግሥትም ሆነ ተቋማት አሠራራቸውን በመቀየር ካርታን መረጃ መጠቀም ሲጀምሩ ኹሉም ሰው ወደደም ጠላም ይጠቀማል።

ከዚህ በተጨማሪ ተቋማችንም ግንዛቤ እየፈጠረ እያበረታታ መሔድ አለበት። የተለመደ ነገር መጠቀም ሰዎች ይቀላቸዋል። ጥቅም ያለው ነገር ስለሆነ ሰዎች አልከተልም አይሉም። ጥቅም የሚያገኙበትን መንገድ ማሳወቅ ደግሞ የተቋማችን ኃላፊነት ነው።

በዚህ ሥራ የተሳተፉ ባለድርሻ አካላት እና ባለሙያዎች እነማን ናቸው?
የካርታ መረጃ ሥራ የኹሉንም አካላት አጋርነት ይፈልጋል። ሥራው በባህሪው መረጃ በመሰብሰብ የሚሠራ ስለሆነ ከኹሉም ጋር መሠራት አለበት። የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ በየወረዳው ያሉ አስተዳደሮች፣ ዩኒቨርሲቲዎች እና በርካታ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ተሳትፈዋል።

ኹሉም የማኅበረሰብ ክፍሎች እና ማንኛውም ግለሰብ አንድ አካል ናቸው። ይህን ሥራ ለመሥራት የጂኦግራፊ፣ የሰርቬይንግ እና የፎቶግራፍ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

አሁን ላይ ታድያ እንዴት መጠቀም ይቻላል?
በአሁኑ ሰዓት ወደ ትግበራ ባለመግባቱ ካርታውን ማግኘት አይቻልም። አንድ ክፍለ ከተማ ላይ ብቻ የተሞከረ ስለሆነ የአዲስ አበባ ኹሉም ክፍለ-ከተማዎች ሲጠናቀቁ በድረ-ገጽ (ዌብሳይት) እና በሞባይል መተግበሪያ እንዲለቀቅ ይደረጋል።
ማንኛውም ሰው የተቋሙን ድረ-ገጽ (ዌብሳይት) በመጠቀም ማግኘት ይችላል። ምናልባት የተቋማችን ሥም ለመያዝ የሚያስቸግር ከሆነ መንግሥት በሚስማማበት ቀላል ቃል በመተካት ለአብዛኛው ሰው ተደራሽ ይደረጋል። እንደ ተቋም ግን ሰዎች ለመልመድ ትንሽ ጊዜ ይወስድባቸው ይሆናል እንጂ የተቋማችንን ሥም በማለማመድ ወደ ሥራ እንዲገባ ከፍተኛ ፍላጎት አለ።


ቅጽ 3 ቁጥር 152 መስከረም 22 2014
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com