የእለት ዜና

የእርስ በርስ ጦርነት ዐቢይ መንሥዔ

‹እግርና እግርም ይጋጫል› የሚለው ኢትዮጵያዊ ብሂል በአንድ ሥም የሚጠሩ፣ የሚጋሯቸው ብዙ እሴት ያላቸው ሰዎች መካከል ሳይቀር ግጭቶች ሊከሰቱ እንደሚችሉ ያስረዳል። በኢትዮጵያ የእርስ በርስ ግጭቶች ዋና መንስዔ የዘውግ ፖለቲካ ሳይሆን ኢኮኖሚያዊ ሰበብ ማለትም ፍትሃዊ ያልሆነ የሀብት ክፍፍል ያስከተለው ችግር ነው ይላሉ፤ ሳምሶን ኃይሉ። የፌዴራል ስርዓቱና በስፋት ሲቀነቀን የነበረው የብሔር ፖለቲካም ግን ከደሙ ንጹህ ናቸው ማለት አይደለም ሲሉ ለእርስ በርስ ጦርነት ዐቢይ መንስዔ ያሏቸውን ነጥቦች ያተቱበትን ጽሑፍ በኹለት ክፍል አጋርተዉናል። የመጀመሪያው ክፍል እነሆ፤

ባለፉት ስድስት ዓመታት ኢትዮጵያ እዚም እዛም በሚጫሩ የእርስ በርስ ግጭቶች እና ጦርነቶች ስትታመስ ቆይታለች። ይህ አልበቃ ብሎ በአሁኑ ሰዓት በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ግጭት እና ጦርነት እንደ ሰደድ እሳት እየተዛመተ ነው። በመሆኑም ዛሬ አገራችን ያለችበት ሁኔታ ከመቼውም ጊዜ በላይ እጅግ አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል።

በኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ በተከሰቱ መጠነ ሰፊ የእርስ በርስ ግጭቶችና ጦርነት ምክንያት የአገሪቷ የወደፊት ዕጣ ፋንታ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል። ካለፈው ታሪካችን ተምረን የአስተሳሰብ ልዩነታችንን በዴሞክራሲያዊ ውይይት ከመፍታት ይልቅ ክተት ማወጅን፣ ነፍጥ ማንገብን እና ጦር መስበቅን በመምረጣችን ኢትዮጵያ ወደ ዐዘቅት ውስጥ እየገባች ነው።

የእርስ በርስ ግጭት እና ጦርነት የሚያስከትለው መዘዝ ለኢትዮጵያውያን መንገር ለቀባሪው እንደማርዳት ነው። ከ1960ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ አስከ 1980ዎቹ መጀመሪያ ድረስ የዘለቁ የተለያዩ የውስጥ ግጭቶች ያስከተሉትን መዘዝና ጉዳት ዘርዝሮ መጨረስ አይቻልም። በቀይ ሽብር ጊዜ የአንድ አባትና እናት ልጆች፣ የተለያየ ፖለቲካ አስተሳሰብ አንግበው ወገን ለይተው ሲገዳደሉ ታዝበናል። በደርግና አማፅያን መካከል በነበረ ግጭትና ጦርነት ምክንያት የአገራችን መሬት በደም ሲታጠብም ዐይተናል። በዚህም ኢትዮጵያ ከአገሮች ሁሉ ውራ ሆና ቀርታለች።

ታዲያ የእርስ በርስ ጦርነትን መዘዝ ጠንቅቆ የሚያውቀው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዴት መፍትሔ ማመንጨት አልቻለም? እንደኔ አስተያየት መፍትሔ ማመንጨት ያልቻልነው የችግሩ ዐቢይ መንስዔ (major reason) ገሸሽ እያደረግን ትናንሽ ምክንያቶች (minor causes) እና ትንኳሽ (catalyst) መነሾች ላይ ብቻ ስለምናተኩር ነው።

በወፍ በረር ሲታይ በተለያዩ ጊዜያት የተነሱ የእርስ በርስ ጦርነቶች መነሾ በየጊዜው የሚለዋውጡ ነገር ግን በአብዛኛው የዘውግ ፖለቲካ ይዘት የተላበሱ ምክንያቶች መስለው ይታያሉ። ለምሳሌ ከ1960ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ አስከ 1980ዎቹ መጀመሪያ ድረስ የዘለቀው የርስ በርስ ጦርነት መንስኤ በአገሪቱ ተስፋፍቶ ነበር ከሚባለው የብሔር ጭቆና ጋር ሲያያዝ ይስተዋላል።

በሌላ በኩል ደግሞ ባለፉት ስድስት ዓምታት በአገሪቷ እዚም እዛም ለታዩት የእርስ በርስ ግጭቶች እና ጦርነቶች እንደዋነኛ ምክንያት ሆኖ የሚጠቀሰው ዘውግን መሠረት ያደረገ የፌዴራሊዝም ስርዐትና ዘር ተኮር ፖለቲካ ነው ተብሎ በሰፊው ይታመናል። በአሁኑ ሰዓት በሰሜኑ የአገራችን ክፍል እንደ ሰደድ እሳት እየተዛመተ ያለው ግጭት እና ጦርነት የነዚሁ ምክንያቶች ውጤት ነው ተብሎ ይነገራል።

በተመሳሳይ ሁኔታ እንዲህ ባሉ ግጭቶች እና ጦርነቶች ሲታመሱ ከነበሩና አሁንም እየታመሱ ካሉ ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ አገራት ተሞክሮም ስንረዳ፣ የእርስ በርስ ግጭቶች መነሻ በአብዛኛው ፖለቲካዊ ይዘት የተላበሱ አመንክዮዎች መስለው ይታያሉ። በዚህ ረገድ ሩዋንዳን መጥቀስ ይቻላል። በቀኝ ገዥዋ ቤልጄም ለዘመናት ሲተገበር በቆየው በከፋፍለህ ግዛና ዘውግ ተኮር ፖለቲካ ምክንያት ነፃነቷን ከተቀናጀች ጀምሮ ሩዋንዳ በተለያዩ የርስ በርስ ግጭቶች ውስጥ አልፋለች። ይህ የርስ በርስ ግጭት ተጋግሎ አገሪቱን ስምንት መቶ ሺሕ ቱትሲዎችና ለዘብተኛ ሁቱዎች ሕይወት ለቀጠፈው ጅምላ ጭፍጨፋ ዳርጓታል።

ጉዳዩን ጠለቅ ብለን ስንመለከት ግን ኢትዮጵያን ጨምሮ በአብዛኞቹ ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ አገራት የእርስ በርስ ግጭቶች ዋና መንስኤ የዘውግ ፖለቲካ ሳይሆን ፍትሃዊ ያልሆነ የሃብት ክፍፍል ያስከተለው ኢኮኖሚያዊ ሰበብ ሆኖ እናገኘዋለን። ይህን ለመረዳት የኢትዮጵያን የቅርብ ዘመን የእድገት ጉዞ መመልከት ያስፈልጋል።

ባለፉት አስራ አምስት ዓመታት ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚ ወይም የምጣኔ ሃብት እድገት እመርታ አስመዝግባለች። ባለ ኹለት አሃዝ ዓመታዊ እድገት ከማስመዝገብ ባሻገር ጠቅላላ ዓመታዊ ምርት (gross domestic product) 1997 ከነበረበት 30 ቢሊዮን ዶላር 44 በመቶ አድጎ አሁን 107 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል። በተጨማሪም ከሠላሳ ዓመት በፊት ከመቶ ቢሊዮን ብር በታች የነበረው የአገሪቱም ዓመታዊ ባጀት አሁን ግማሽ ትሪሊዮን ብር አልፏል። እነዚህ ባለፉት አስራ አምስት ዓመታት የተመዘገበው እድገት ትሩፋቶች ናቸው።

በሌላ በኩል ደግሞ ባለፉት ኻያ ዓመታት ድህነት (poverty) በኢትዮጵያ በጣም ጨምሯል። 15 ሚሊዮን አካባቢ የነበረው ከድህነት ወለል በታች የሚኖር ሕዝብ ቁጥር አድጎ አሁን 35 ሚሊዮን አልፏል። አንደኛው ለድህነት መጨመር ምክንያት የሸቀጦች ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ ማሻቀብ ያስከተለው የኑሮ መወደድ ነው። ሌላኛው ለድህነት መስፋፋት አስተዋጽኦ ያደረገው በስፋት የሚታየው የሥራ አጥነት ችግር ነው። በተለይም በወጣቱ የኅብረተሰብ ክፍል የሥራ አጥነት ችግር ጎልቶ ይታያል።

እነዚህን ጉራማይሌ የኢኮኖሚ እድገት ትሩፋቶችን ስንመለከት የእድገቱ ተጠቃሚ ማን ነበረ ታዲያ ብለን እንድንጠይቅ ያስገድደናል። ሃያ ሰባት ዓመት አገሪቷን ባስተዳደረው የኢሕአዴግ ዘመን ከልማቱ ተጠቅመዋል ሊባሉ የሚችሉት በግንባሩ ውስጥ ተሰግስገው የነበሩ ሥነ-ምግባር የጎደላቸው ባለሥልጣናትና ለነሱ የቀረቡ ሰዎች ነበሩ።

ይህን ለመገንዘብ በተለይም በከተሞች ላይ የሚታየውን የተዛባና ፍትሃዊ ያልሆነ የሃብት ስርጭትን ማጤን ያሻል። በቅርብ ዓመታት እንደታዘብነው የሀብታሞች ቁጥር በኢትዮጵያ ጨምሯል። ሰማይ ጠቀስ ፎቆች፣ የተቀናጡ የመኖሪያ ቤቶች፣ መኪናዎች እና መዝናኛ ቦታዎች እንደ አዲስ አበባ ባሉ ከተሞች ማየት ብርቅ መሆኑ እየቀረ መጥቷል።

ባለፉት ዓመታት አገሪቱ በዚህ መንገድ ጥቂት ሀብታሞችን ስታፈራ ብዙ ድሆችንም እየፈጠረች ነበር። እንደ መሬት ያሉ የተፈጥሮ እና ሌሎች አገራዊ ሀብቶች አጠቃቀምና ክፍፍል ዙሪያ ግልጽነት በመጥፋቱ ብዙ ጥያቄዎች እየተመዘዙ ቢወጡም ምላሽ ግን ሳያገኙ ቀርተዋል። በመሆኑም አብዛኛው ሕዝብ የእድገቱ ትሩፋት ተቋዳሽ ሳይሆን ቀርቷል። ይህ ዓይነቱ የተንሸዋረረ እድገት ለቅራኔ ምክንያት መሆን ብቻ ሳይሆን ለግጭትም መነሻ ሊሆን በቅቷል።

በተለይም የኢሕአዴግ አስኳል ከነበረው ከ‹ሕወሓት› ጋር ባንድ ወይም በሌላ መንገድ ግንኙነት ያላቸው በርካታ ባለሥልጣናትና በዙሪያቸው ያሉ አጋሮቻቸው፣ ወዳጆቻቸው፣ ዘመዶቻቸው፣ ጓደኞቻቸውና የጥቅም ተጋሪዎቻቸው ያላግባብ ተጠቃሚ እንደነበሩ ለማወቅ የግድ ድንጋይ መፈንቀል አያስፈልግም። በዚህም ምክንያት የሀብት ክፍፍሉ በአብዛኛው ለአንድ ብሔርን ጥቅም ያደላ አስመስሎታል።

እዚህ ላይ ሊሰመርበት የሚገባው ሕወሓትን ከመረጠውም ሆነ ከጠቅላላው የትግራይ ሕዝብ አንጻር ሲታይ ፍትሃዊ ያልሆነ የሃብት ክፍፍል ተጠቃሚዎች ቁጥር በጣም ትንሽ ነው። ነገር ግን በአብዛኛው ወደ ሀብት ማማ የወጡት ከአንድ ብሔር የወጡ ሰዎች መሆናቸው የሚካድ አይደለም። በዚህም ምክንያት በስፋት የተንሰራፋው ፍትሃዊ ያልሆነ የሀብት ክፍፍል መልኩን ቀይሮ የጎሳ ፖለቲካ መልክ ሊይዝ ችሏል።

በሩዋንዳም የታየው ተመሳሳይ ነገር ነው። ምንም እንኳን በሩዋንዳ ለነበረው የእርስ በርስ ግጭትና ጅምላ ጭፍጨፋ የጎሳ ፖለቲካ መንስኤ ቢመስልም፣ ዋነኛው ግን ፍትሃዊ ያልሆነ የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ሀብት ክፍፍል ሆኖ እናገኘዋለን። የሩዋንዳ ቀኝ ገዢ የነበረችው ቤልጄም የቱትሲ ጎሳ አባላት ወደ ሥልጣን በማቅረቧ ከነፃነት በኋላ በቁጥር አናሳ የሆኑ የቱትሲ ጎሳ አባላት የኢኮኖሚያዊ የበላይነት እንዲጨብጡ አስችሏል። ምንም እንኳን የዚህ ፍትሃዊ ያልሆነ ሃብት ክፍፍል ተጠቃሚዋች በጣም ጥቂት የሆኑ ቱትሲዎች ቢሆኑም፣ ጉዳዩ የዘውግ ፖለቲካዊ መልክ ከመያዝ አላገደውም።

ይህ ማለት ግን የፌዴራል ሥርዓቱና በስፋት ሲቀነቀን የነበረው የብሐየር ፖለቲካ ለርስ በርስ ግጭቶች አስተዋጽኦ አላደረጉም ማለት አይደለም። እንደውም በተቃራኒው ፍትሃዊ ያልሆነ የሀብት ክፍፍል በኢትዮጵያ እንዲሰፍን የፌዴራል ሥርዓቱና የብሔር ፖለቲካው ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል።

የፌዴራሉ ስርዓት በኢትዮጵያ የተተገበረው ለመልካም አስተዳደር፣ ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ፣ የኢኮኖሚ እድገትን ለማፋጠንና ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል ለማስፋን ይረዳል ከሚል ድምዳሜ ነው። እነዚህ ግቦች እንዲሳኩ ግን የፖለቲካ አወቃቀሩ በሚገባ ማዋቀርን በተለይም ዋናዎቹ የፖለቲካ ተቋሞች ማለትም ሕግ አውጭው፣ ሕግ ኣስፈጻሚውና ሕግ ተርጓሚው እርስ በርስ እንዲተራረሙ የሚያስችል እና ሚዛናዊ የሆነ ተጠያቂነት ያለበት ሥርዓት መፍጠርን ይጠይቃል።

በኢትዮጵያ የነበረው የፌዴራሉ ሥርዓት ግንባታ ግን ይህን መሠረታዊ መርህ የተከተለ አልነበረም። በግልፅ እንዳየነው ሕግ አውጭው፣ ሕግ ኣስፈጻሚውና ሕግ ተርጓሚው የጥቂቶች ፍላጎት አስፈጸሚ ሆነው ቀርተዋል። ተጠያቂነት በመጥፋቱ ሥልጣን ከሕዝብ ወጥቶ የጥቂቶች ፍላጎት መፈጸሚያ ሆኗል። አንዳንድ ባለሥልጣናትና ግለሰቦች እነዚህን የፖሊቲካ ተቋሞች እንደ መሣሪያ ተጠቅመው ሀብት ለማጋበዝና አገሪቱን ለመበዝበዝ በቅተዋል። በራሱ የችግሩ ምንጭ ባይሆንም የፌዴራል ሥርዓቱ በዚህ መልኩ በጥቂቶች ተጠልፎ ፍትሃዊ ያልሆነ የሀብት ክፍፍል ማስፈፀሚያ መሣሪያ እንዲሆን ተገዷል።

ለችግሩ መፍትሄ ለማግኘት ግን በመጀመሪያ መነሻውን ጠንቅቆ ማወቅ ያስፈልጋል። እንደ ፍትሃዊ ያልሆነ የሀብት ክፍፍል ዓይነት ሕፀጾችን ለማስወገድ ሊወሰዱ የሚገቧቸውን እርምጃዎች በሚቀጥለው ጽሑፌ በሰፊውና በጥልቀት የምዳስሰው ይሆናል። ነገር ግን የፌዴራል ሥርዓቱን ያለጥናትና ዝግጅት ማስወገድ መፍትሄ ሊሆን አይችልም።

በሌሎች አገራት እንዳየነው የፌዴራል ሥርዓት አካታች የሆነ የኢኮኖሚ እድገት ከማምጣት ባሻገር የዜጎችን መብት ለማስጠበቅና የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ዋነኛ ግብአት ነው። በመሆኑም የፌዴራል ሥርዓቱን እና የብሔር ማንነትን ማስወገድ ሳይሆን ራስን በራስ ለማስተዳደር በር በሚከፍት እና ፍታሃዊ የሆነ የሀብት ክፍፍልን በሚያረጋግጥ መልኩ ማሻሻልን ይጠይቃል። ይህም በዋነኛነት አሳታፊ፣ ሁሉን አቃፊና ገለልተኛ የሆኑ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና ማኅበራዊ ተቋሞችን መፍጠርንና ማዋቀርን ይጠይቃል።


ቅጽ 3 ቁጥር 152 መስከረም 22 2014
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com