የእለት ዜና

የኢሬቻ በዓል ሌላው ገጽታ

ኢሬቻ የምስጋና ቀን ነው። ይህ በዓል በኹለት ቦታዎች እንደሚከበር ስርዓቱን የሚያውቁ ሰዎች ይናገራሉ። የሚከበርባቸው ቦታዎቹም በሐይቆችና ወንዞች እንዲሁም በተራራዎች ላይ ነው። አንደኛው በክረምቱ መግቢያ ወቅት ላይ ሲሆን፣ ክረምቱን በሰላም አሻግረን፣ ውኃ እና እርጥቡን አትንሳን ተብሎ ፈጣሪን የሚለማመኑበት፣ በተራሮች አናት ላይ የሚደረግ ነው።

ኹለተኛው ደግሞ ‹ከክረምቱ አስፈሪ ነጎድጓድ እንኳን ወደ ብርሃን አወጣኸን። ብራውን ሰላም አድርግልን›› በማለት በሐይቆችና ጅረቶች ዙሪያ ምስጋናን በማደረስ የሚከበር ነው። ይህም አሁን በአዲስ አበባ መስከረም 22 እንዲሁም በቢሾፍቱ መስከረም 23/2014 የሚከበረው በዓል ነው።

ጥቂት ስለ ኢሬቻ
ኢሬቻ በገዳ ስርዓት ውስጥ ያለ አንድ አካል ነው የሚሉት በአዲስ አበባ ከሚገኙ የአገር ሽማግሌዎች ውስጥ አንዱ የሆኑትና በየካ ክፍለ ከተማ በሽምግልና የሚያገለግሉት ሀዩ ዘውዱ መግራ ሮቢ ናቸው።
በዓመት ውስጥ ኹለት ጊዜ ኢሬቻ ይደረጋል ያሉት ሀዩ ዘውዱ፣ አንደኛው መስቀልን አልፎ መስከረም መጨረሻ አካባቢ የሚደረግ ሲሆን፣ ኹለተኛው ‹‹አሳሳ›› የሚባለው ተራራ ላይ በመውጣት ምስጋና የሚቀርብበት ነው ሲሉ ያወሳሉ። በይበልጥ ግን እየተከበረ ያለው በቢሾፍቱ እና አዲስ አበባ ሲሆን፣ ከ100 ዓመት በፊት በአዲስ አበባ ይከበር እንደነበር አስታውሰዋል።

የኢሬቻ በዓል የመስማማትና የአንድነት ወቅት ነው ተብሎ ይታሰባል። የክረምቱን ሦስት የጨለማ ወራት አልፈን ወደ ብርሃን የምንወጣበት ነው ተብሎም ምስጋና ይቀርብበታል፤ ደስታም ይገለጽበታል። ሀዩ ዘውዱ በዓሉን እንዲህ ሲሉ ይገልጹታል፤ ‹‹ለምለም ሳር በመያዝ የክረምቱን ወራት አሳልፎ ከጨለማ ወደ ብርሃን ላሻገረ አምላክ በምስጋና መልክ የሚቀርብ ነው። የኦሮሞ ብሔረሰብ በጋራ ከኹሉም ብሔረሰብ ጋር የሚኖር መሆኑን የሚያሳይም ነው።››

በአንጻሩ በ2009 በነበረ የፖለቲካ አለመረጋጋት በቢሾፍቱ በተከበረው የኢሬቻ በዓል የሰዎች ሞት የተከሰተበት እንደነበር ሀዩ አውዱ አንስተዋል። ‹‹የኢሬቻ በዓልን ፖለቲካ ለማድረግ የሚሞክሩ ጥቂቶች ናቸው እንጂ አብዛኛው ታዳሚ ምስጋናን ለማቅረብ ነው የሚሰበሰበው›› ሲሉ ለበዓሉ የሚሰጡ ፖለቲካዊ ዕይታዎች አግባብ እንዳልሆኑ ይጠቅሳሉ።

ባለፉት ኹለት ዓመታት ማለትም አዲስ አበባ መከበር ከጀመረ ጀምሮ የፖለቲካ ትኩሳቱ ሲበርድ፣ በሌላ በኩል የተነሳው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በዓሉን በጥቂት ሰዎች ብቻ እንዲከበር አድርጎታል።

ኢሬቻን ከቱሪዝም አንጻር
ሙሳ ከድር በቱሪዝም ኢትዮጵያ የቱሪዘም መዳረሻ ልማት ዳይሬክተር ናቸው። እሳቸው እንደሚሉት ኢሬቻን የመሰሉ ሰዎች በብዛት የሚሰበሰቡባቸው በዓላት በቱሪዝም አገላለጽና ሚዛን እንደ ፌስቲቫል ይቆጠራል።
እንደነዚህ ዓይነት ፌስቲቫሎች ሰዎች በብዛት ከተለያየ ቦታ ተሰባስበው አንድ ቦታ ላይ የሚገናኙበት አጋጣሚ ነውና የተለየ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ይኖራቸዋል። ሰዎች ካሉበት ቦታ ተነስተው ፌስቲቫሉን ለማክበር ወደ ማክበሪያ ቦታ ይንቀሳቀሳሉ። በዚህ እንቅስቃሴያቸው ውስጥ ከመነሻቸው ጀምሮ እስከ መዳረሻቸው ወጪ ያወጣሉ።

የበዓሉ ወቅት የትራንስፖርት ከፍተኛ ወጪ ከሚወጣባቸው አገልግሎቶች አንዱ ነው። የበዓሉ ተሳታፊዎች ትራንስፖርት የማይጠቀሙ ከሆነ በራሳቸው መኪና ለመምጣት ነዳጅ ይሞላሉ፤ ወይም ትራንስፖርት ኮንትራት ይይዛሉ። በዚህ መሠረት ከቦረና፣ ከሐረርጌ፣ ከወለጋ እና ከሩቅ የኦሮሚያ አካባቢዎች ተነስተው የሚመጡ የበዓሉ ታዳሚዎች አሉ።

እነዚህ ታዳሚዎች በሚያደርጉት ረጅም የመንገድ ጉዞ በተለያየ አካባቢ ወጪ ያወጣሉ። ይህም ከፍተኛ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እንዲፈጥር የሚያስችል በዓል መሆኑን ሊያሳይ ይችላል ሲሉ ሙሳ ለአዲስ ማለዳ ሐሳባቸውን አካፍለዋል።
ምንም እንኳ የኢሬቻ በዓል በአዲስ አበባ ሲከበር ለሦስተኛ ጊዜ ቢሆንም፣ ወደ ከተማዋ መጥተው በዓሉን የሚያከብሩ ሰዎች የሚያወጧቸው ወጪዎች እንዳሉና ወደፊትም እንደሚፈጠሩ ሙሳ ይጠቅሳሉ።

‹‹አዲስ አበባ እስኪደርሱ ካለው ወጪ በተጨማሪ ከበዓሉ ቀደም ብለው ከመጡበት ቀን ጀምሮ እስከሚመለሱበት ቀን ድረስ ለምግብ፣ ለአልጋ እና ለተለያዩ መዝናኛዎች ወጪ ማውጣታቸው አይቀርም። ይህም ለአዲስ አበባ ከተለመደው የተለያየ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በተጨማሪ ገንዘብ ለማስገኘት አስተዋጽኦ ያበረክታል። እንደነዚህ አይነት ፌስቲቫሎች በሚከበሩበት ወቅት የውጭ አገር ጎብኚም ሆነ የአገር ውስጥ የበዓል ተሳታፊ ስለሚኖር፣ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ከፍተኛ መነቃቃት ይታይባቸዋል›› ሲሉ ሙሳ አስረድተዋል።

በአዲስ አበባ የሚከበረው ኢሬቻ በዓል ላይ ደምቆ የሚታየው አንዱ የአገር ባህል ልብስ ነው ያሉት ሙሳ፣ ሰዎች በዓሉን ለማክበር ብለው ብዙ ወጪ አውጥተው የተለያየ ዲዛይን ያላቸው የአገር ባህል ልብሶችን ይገዛሉ። በዚህ ወቅት የባህላዊ ልብስ ገበያ ይደራል። ከዚህ በተጨማሪ የበዓሉ ዕለትን የሚያደምቁ የዲኮር እና የመድረክ ሥራዎች ከፍተኛ ገቢ የሚገኝባቸው ሥራዎች ናቸው። እነዚህ ኹሉ ተደማምረው ለአገር ውስጥ ቱሪዝም እንቅስቃሴውና ለኢኮኖሚው መነቃቃት ግብዓት ይሆናሉ ብለዋል።

የአገር ባህል ልብሶችን ወቅት ያገናዘቡ በማድረግ በተለያየ ዲዛይን የምትሠራው ጸዳሉ መርጊያ ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ አድርጋለች። ጸዳሉ የአገር ልብስ ዲዛይን በማድረግ ሥራ ውስጥ ለሰባት ዓመት ያህል የቆየች ወጣት ናት። እንደ አዲስ ዓመት፣ መስቀል፣ ኢሬቻ፣ ጥምቀት እና ሌሎች ክብረ በዓላት ሲኖሩ ለበርካታ ሰዎች የተለያየ ዲዛይን ያላቸውን የአገር ልብሶችን ትሠራለች።

‹‹የኢሬቻ ቀንን የሚገልጽ የሴት ቀሚሶች፣ የወንዶች ኮት እንዲሁም ቤተሰብ በጋራ ሆነው ተመሳሳይ የበዓሉ መገለጫ ልብሶች ያሠራሉ። ኢሬቻን የሚገልጽ ቀለም ያለው እና በዓሉ ላይ ጎልቶ የሚያወጣቸውን የልብስ ዲዛይን ሰዎች ያዝዛሉ። የወንድ ኮት ከአንድ ሺሕ አምስት መቶ እስከ ሦስት ሺሕ ብር እና የሴቶች ቀሚስ ከኹለት ሺሕ እስከ አምስት ሺሕ ብር ድረስ እየሠራሁ ነው›› ስትል ትገልጻለች።

የልብሶቹ ዋጋ በዲዛይኖቹ እና በመረጡት የጨርቅ ዓይነት ዋጋ እንደሚለያይ የገለጸችው ጸዳሉ፣ ተሠርተው ያለቁ ለሽያጭ የቀረቡ የኢሬቻ በዓል የሚሆኑ ልብሶችንም እንደምታቀርብ ገልጻለች።
የአገር ባህል ልብስ ወቅት የሚፈልግ አለባበስ እንደመሆኑ በአሁኑ ሰዓት የኢሬቻን ልብስ የሚፈልጉ በርካታ ትዕዛዞችም አሏት። ከሌላው ቀን በተለየም በዓሉን የሚገልጹ የአገር ባህል ልብስ የሚያሠሩ ሰዎች ከፍተኛ የገቢ ምንጭ እንደፈጠረሉት ትናገራለች።
ሙሳ በበኩላቸው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ፌስቲቫሎችን እንደ ቱሪዝም ምርት የማስተዋወቅ ሥራ በከፍተኛ ሁኔታ እየተሠራ መሆኑን ያነሳሉ። ኢሬቻ ይልቁንም በቢሾፍቱ/ደብረዘይት ለረጅም ጊዜ ሲከበር የቆየ እንደመሆኑ፣ ከድሮም ጀምሮ ቢሆን የውጭ አገር ዜጎች፣ ዳያስፖራዎች እና የአገር ውስጥ ቱሪስት ይታደሙበታል። በተለይ ከውጭ የሚገቡ ጎብኚዎች በሚታደሙበት ወቅት የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት ያግዛል ብለዋል።

ከዚህም በላይ ልዩ የሚያደርገው ኢሬቻ ኹሉም ብሔር ብሔረሰቦች ተወክለውበት የሚከበር አንድነትን የሚያጠናክር ባህላዊ ፌስቲቫል ነው። ይህንን የባህል መስተጋብር ለማየት የሚመጣው ዜጋ ቁጥርም ቀላል አይባልም።
ከኢሬቻ የቱሪዝምና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው አንጻር ሀዩ ዘውዱ ሲናገሩ፣ በዓሉን በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ለማስመዝገብ እየተደረገ ያለውን ጥረት አንስተዋል። ያም ከተሳካ በዓሉ ለአገሪቱ ትልቅ የኢኮኖሚ ምንጭ መሆን እንደሚችል ይናገራሉ።

በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣንና በኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የኢሬቻ በዓልን ዩኔስኮ ላይ የማስመዝብ ሥራ እየተሠራ እንደሆነ ሙሳ ይናገራሉ። አክለውም ቱሪዝም ኢትዮጵያ ለዚህ የማስመዝገብ ጥረት የቴክኒክ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል። እንዲሁም እንደ አንድ የቱሪዝም ምርት በምን አይነት መልኩ ለገበያ መቅረብ እንዳለበት የሚለው ላይ ድርጅቱ እየሠራ ይገኛል ሲሉ ገልጸዋል።

‹‹አንድን ቅርስ በዩኔስኮ የማስመዝገብ ሒደት ብዙ ነው። ነገር ግን ለዩኔስኮ ቀርበው እንዲጸድቁ ወረፋ ከተያዘላቸው ቅርሶች ውስጥ አንዱ ሆኗል›› ሲሉ ሙሳ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ አስታውቀዋል።

ኢሬቻ 2014
ኢትዮጵያ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የተነሳውን ጦርነት እንዲሁም ያንን ተከትሎ የመጡ ውጫዊ ጫናዎችን ተሸክማ ትገኛለች። ከዚነዚህ በተጨማሪም ሦስተኛው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ማዕበል አገሪቱን ክፉኛ እያናወጣት ይገኛል።
እንደሚታወሰው ባለፈው ዓመት የኢሬቻ በዓል በዚህ ወረርሽኝ ሳቢያ በጥቂት በተመረጡ ሰዎች ተሳታፊነት ተከብሯል። ዘንድሮም ከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚደረግ ተነግሯል፤ አደራም ተጥሏል። ኹኔታዎችን ለጎብኚዎች ምቹ በማድረግ፣ የጥንቃቄ መተግበሪያዎችን በሙሉ በመጠቀም ማንኛውም ሰው ተሳታፊ የሚሆንበት ዕድል ተመቻችቷል ተብሏል።

እንደ ኢሬቻ ያሉ የጋራ በዓላት ብዙ ሰዎች የሚሳተፉባቸው እንደመሆኑ መጠን ከፍተኛ ጥንቃቄ ይፈልጋሉ። ሙሳ በበኩላቸው ተሳታፊዎች ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ያወጣቸውን መስፈርቶች በመከተል ማክበር ይገባቸዋል ሲሉ አሳስበዋል።
‹‹ከኹለት ዓመት በፊት ተከብሮ የነበረው በሚሊዮን የሚቆጠር ታዳሚ የተገኘበት የኢሬቻ ክብረ በዓል ባሳለፍነው ዓመት በኮቪድ ምክንያት በተመረጡ ሰዎች ብቻ መከበሩ ከፍተኛ ገቢን አሳጥቶናል። ያኔ የበዓሉ ተሳታፊዎችና ጎብኚዎች በመጀመሪያው ቀን አዲስ አበባ፣ በቀጣይ ቀን ቢሾፍቱ/ደብረዘይት ሔደው ነበር። በእነዚህ ቀናት ውስጥ በሚሊዮን የሚቆጠረው ታዳሚ ያወጣ የነበረውንና በኹለቱ ከተሞች ላይ ይገኝ የነበረውን ገቢ አጥተናል›› በማለት ሙሳ አስታውሰዋል።

ሀዩ ዘውዱ በንግግራቸው መቋጫ፤ ‹‹አገራችን በዓላትን እየጠበቅን ብቻ ሳይሆን የመንግሥት ሠራተኛው፣ ገበሬው፣ የግል ባለሀብቶች እንዲሁም ምሁራን አቅማቸውን እያሳደጉ አገሪቷን በመለወጥ ለዓለም ማስተዋወቅ ይገባናል። ይህን ማምጣት የምንችለው በመግባባት እና በአንድነት ነው። አንድ ሰው አንድ እርምጃ ሲራመድ ሌላኛው ወደኋላ የሚጎትት መሆን የለበትም። አንድ መሆን ይገባናል። በአዕምሮአችን ውስጥ ያለውን የጥላቻ ስሜት በማስወጣት አገርን ለማሳደግ እንጣር›› ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በዓሉን ለማክበር የጸጥታ አካላት፣ መከላከያ፣ በክፍለ ከተማ እና በየወረዳው ያሉ ጥበቃና ፍተሻ የሚያደርጉ አካላት ተሰማርተዋል። በበዓሉ ዕለት ወደ አዲስ አበባ የሚመጡ አባ ገዳዎች የምርቃትና የምስጋና ሥነ-ስርዓት የሆነው ኢሬቻ ይከናወናል። በቦታው የተገኙ የበዓሉ ታዳሚ እየሄዱ እርጥብ ሳር እና አበባ በመያዝ፣ የባህል ልብስ በመልበስ ምስጋና ያቀርባሉ። ዓመት ዓመት ያሻግረን ይላሉ። እኛም ዓመት ዓመት ያድርሰን እንላለን!


ቅጽ 3 ቁጥር 152 መስከረም 22 2014
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com