የእለት ዜና

ሕፃናት በጦርነት መካከል

ሕፃናት ካለባቸው ኃላፊነት ይልቅ ያላቸው መብት የበዛ፣ ውሣኔ መስጠት የማይጠበቅባቸው እንዲሁም በወላጆቻቸው ጥበቃና እንክብካቤ ማደግ የሚገባቸው ባለነጠላ ቁጥር ዕድሜ ላይ የሚገኙ ነፍሶች ናቸው። ‹ልጅ የፈጣሪ ስጦታ ነው› ብሎ በሚያምን ማኅበረሰብ ውስጥም፣ ሕፃናት የወላጆች መልካም ስጦታ፣ የአብራካቸው ክፋይ ናቸው።

ሕፃናት የሚገባቸውን አግኝተው ሲያድጉና ነፍስ ሲያውቁ ወይም ለአቅመ አዳም እና ለአቅመ ሔዋን ሲደርሱ፣ ለወላጆቻቸውና አሳዳጊዎቻቸው ጧሪ ቀባሪ፣ የኋላ ኋላም አገር ተረካቢ እንዲሆኑ ይጠበቃል፤ መሆናቸውም ጥያቄ አያስነሳም። ለዚያ እንዲደርሱ ግን ከወዲሁ እንደ ችግኝ መንከባከብ የወላጅ፣ የአሳዳጊና የአገር ድርሻ ነው።

ነገር ግን በበርካታ የዓለም አገራት ሕፃናት መብታቸው ተከበሮ፣ ሳይራቡና ሳይጠሙ፣ በቂ የወላጅ ወይም የአሳዳጊ እንክብካቤና የቤተሰብ ፍቅር አግኝተው ሲያድጉ አይስተዋልም። ይልቁንም ገና ከእናታቸው ማሕጸን ከወጡ ማግስት ጀምሮ ለብዙ ስቃይና እንግልት የሚጋለጡት አያሌ ናቸው። ለአስከፊ የጎዳና ሕይወት፣ ለጉልበት ብዝበዛ፣ ለጾታዊ ጥቃት፣ ለበሽታ እና ለረሀብ የተሰጡትም ጥቂት አይደሉም።

ከዚህ በከፋ ሁኔታ ደግሞ በበርካታ የዓለም አገሮች ሕፃናትን ለጦርነት ዓላማ ማዋል የተለመደ ሆኖ ይስተዋላል። የአጥፍቶ ጠፊ ድርጊትን እንዲከውኑ፣ የስለላ ሥራ እንዲሠሩ ብሎም በጦር ግንባር ተግኝተው ወጊያ ላይ እንዲሳተፉ የሚያደርጉ አዋቂ አጥፊዎች በርካታ ናቸው። ሆኖም የሕፃናትና ልጆች ተፈጥሮ ለሠላም፣ ለቡረቃ፣ ለመማርና ለምቾት እንጂ ለጦረኝነት የማይስማማ ሙሆኑ የማያከራክር ሐቅ ነው።

ከሠላሳ ዓመት በፊት የ196 አገሮች ፊርማ አርፎበት የፀደቀው የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መብት ድንጋጌ ማንኛውም ሕፃን በሕይወት የመኖር፣ ጥበቃና ከለላ የማግኘት እንዲሁም የመማር መብት እንዳለው ይደነግጋል። አክሎም ከቤተሰቦቻቸው ጋር የመኖርና የማደግ መብታቸውንም ማንም ሊነጥቃቸው እንደማይገባ ይገልጻል።

ይኸው ሰነድ ታድያ ከአስራ አንድ ዓመት በኋላ ኹለት ድንጋጌዎችን ጨምሯል። ከእነዚህም መካከል የመጀመሪያው መንግሥታት ከ18 ዓመት በታች የሚገኙ ሕፃናትና ልጆችን ማንኛውም ቡድን ለወታደርነት መመልመል እና ማሠልጠን እንዳይችል ማድረግ እንደሚገባቸው የሚያዝዝ ነው።

ሆኖም ዘመኗን በሙሉ በጦርነትና በሽብር በተለከፈችው አፍሪካ ውስጥ የሕፃናት ሰቆቃ እጅግ የከፋና ድንጋጌው ከነመኖሩም ያላገናዘበ ነው። በአፍሪካ የሚንቀሳቅሱ የሽብር ቡድኖች በየጊዜው ሕፃናትን ሲያግቱና ለወታደራዊ ድርጊት መጠቀሚያ ሲያደርጓቸው ማየትም ተለምዷል።
በኢትዮጵያ ቀድሞ መንግሥት ሆኖ አገር ሲመራ የነበረው አሁን ደግሞ በሕዝብ እንደራሴዎች ሽብርተኛ ተብሎ የተፈረጀው ህወሓትም፣ የመንግሥታቱ ድርጅት ያስቀመጠውን ድንጋጌ በመጣስ በኢትዮጵያ እምብዛም ባልተለመደ ሁኔታ በጦር ግንባር ሕፃናትን ቀዳሚ ተሰላፊ ሲያደርጋቸው ታይቷል።

ወላጆች የልጆቻቸውን መከራና ሞት እንዲያዩ የተፈረደባቸው ይመስላል። ብዙዎች ልጆችና አዳጊዎች ላይመለሱ በዚያው የጥይት አረር በልቷቸው ወድቀው ሲቀሩ፣ ከቆሰሉትና አካለ ጎደሎ ሆነው ከሚቀሩት እኩል ሠላም ባለባቸው ቦታዎች ሆነው ዕለት በዕለት የጦርነት ዜና እየሰሙና እያዩ የሚያድጉ ሕፃናትም ሕይወት በእጅጉ ያሳስባል። ጦርነት የዛሬን ብቻ ሳይሆን የነገንም ትውልድ ገዳይና አጥፊ ነው።

በዚህም በኢትዮጵያ አሁን ላይ ስላለው ጦርነት ወሬዎችን መስማት ቀላል መሆኑ ተከትሎ አዳጊዎች ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ ተጽዕኖ የከፋ ነው። በብዙ ሕፃናት ልብ እና አዕምሮ ውስጥ የሚጠነሰሰው መልካምም ይሁን መጥፎ ነገር፣ መነሻውና ተያያዥነቱ አብዝተው ከሚሰሙትና ከሚያዩት ነገር ጋር ነው።

ሕፃናትና ልጆች የሚያዩትና የሚሰሙት ነገር ስለጦርነት ሲሆን፣ አዕምሯቸው ፍሬን በሚያፈራ መልካም እውቅት፣ ልባቸውም በእምነትና በበጎ ሰብዕና መሞላቱ ይቀርና የአፍራሽነትና የተነኮል አመል ይዘው ያድጋሉ።
ሕፃን እዝራ መስፍን አዲስ አበባ ተወልዶ ያደገ የሦስተኛ ክፍል ተማሪ ነው። መጫወት የሚወድ ቢሆንም፣ ከዚህ የበለጠ ግን ጎበዝ ተማሪ ሆኖ ትምህርቱን ማጠናቀቅ እንደሚፈልግ ይናገራል። ጎበዝ ተማሪ ሆኖ ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላ ደግሞ መሆን የሚፈልገው ወታደር ነው። የሚገርመው ወታደር መሆን የፈለገበት ምክንያት ነው። ሕፃኑ እዝራ ‹‹ወታደር የምሆነው አገሬን የሚዋጋውን እና ሕፃናትን የሚገድለውን ጁንታውን ለመያዝ ነው›› ሲል ተናግሯል።

ይህ እንግዲህ ጦርነት የልጆችን ሥነ-ልቦና እንዴት አድርጎ እንደሚበክል ማሳያ ነው። እዝራ እሱ ብቻ ሳይሆን ኹሉም ጓደኞቹ ተምረው ወታደር መሆን እንዳለባቸው ነው የሚናገረው። ከእዝራም ሌላ አገር ማለት ጦርነት፣ መገዳደል እና ማፈናቀል የሚመስላቸው በርካታ ሕፃናት አሉ።

በዓለማችን ከፍታ ላይ ያሉ አገሮች ትልቁን ሥራ የሚሠሩት ሕፃናትና ልጆች ላይ ነው። በዚህ ረገድ እንግሊዝን እንደ ዋና ምሳሌ መውሰድ ይቻላል። ‹በልጆች ወስጥ ነገ፣ በሽማግሌ ውስጥ ትዝታ አለ› የሚሉት እንግሊዛውያን፣ ከአዋቂዎች እና ከማንም በላይ ለአዳጊዎች የተሻለ ቦታ እንደሚሰጡ ይነገርላቸዋል። የማትጠልቀዋን የእንግሊዝን ፀሐይ የሚያስቀጥሉት ሕፃናት ናቸው ብለው ስለሚያምኑ ገና በማሕጸን ሳሉ ጀምሮ መልካም ታሪክ እያስደመጡ ያሳድጓቸዋል።

በእንግሊዝ ሕፃናት ከወላጆቻቸው ጋር እኩል ቁጭ ብለው ዜና አያዳምጡም። ይልቁንም ወላጆች ለልጆች ተብሎ የሚተላለፈውን የቴሌቭዥን መርሀ-ግብር ልጆቻቸው እንዲያዩ ካደርጉ በኋላ ማስተኛት ይጠበቅባቸዋል። ልጆቻቸውን ካስተኙ በኋላ አገራዊና ዓለም ዐቀፋዊ ጠንከር ያሉ ዜናዎችን ብቻቸውን ሆነው መከታተል ይችላሉ። ይህን ባያደርጉም ቅጣት ይጠብቃቸዋል።

ከዚህ በተቃራኒ ደግሞ ከአባቱ ጎን ቁጭ ብሎ በጦርነት የተቆራረጠ የሰው ልጅ ገላ እና በየቦታው የረገፈ አስከሬን በቴሌቪዥን መስኮት የሚያይ ሕፃን ምን ዓይነት አስተሳሰብ ይዞ ሊያድግ እንደሚችል መገመት አያዳግትም።
አዲስ ማለዳ ሌላ ባለታሪክ አናግራለች፤ ልዑል አበባው ይባላሉ። የሦስት ልጆች አባት ናቸው። እርሳቸው አሁን ላይ በኢትዮጵያ ያለው ጦርነትና የጦርነት ወሬ የነገ አገር ተርካቢዎችን በእጅጉ የሚጎዳ መሆኑን ይገልጻሉ።

‹‹ከሦስቱ ልጆቼ ኹለቱ ሕጻናት ናቸው›› የሚሉት ልዑል፣ እንደ አገር የአዳጊዎችን መልካም ሥነ-ልቦና እና አዕምሮ ለመገንባት የሚደረግ ነገር አለመኖሩ ያሳስባል ብለዋል። ለልጆቻቸው ሲሉ ብዙ ቀን በዜና ሰዓት ቴሌቪዥን እንደማይከፍቱ ገልጸው፣ ሆኖም ግን መረጃው ሳይፈልጉም ቢሆን በቀላሉ ስለሚደርሳቸው ደካማ አስተሳስብና ፍርሀት ይዘው እንዳያድጉ ሁሌም እሰጋለሁ ይላሉ።

እንደርሳቸው ገለጻ ከሁሉም የሚከፋው ሕፃናትን ለጦርነት ተግባር ማዋል ሲሆን፣ ቤታቸው ውስጥ ቁጭ ብለው ስለጦርነት የሚሰሙትም ክፉኛ ተጎጅ መሆናቸውን አብራርተዋል።
‹‹በጣሊያን ወረራ ጊዜ እንኳን በትንሹም ቢሆን የተወሰኑ ሕፃናት ወራሪውን የፋሽስት ኃይል ለመዋጋት ከአባቶቻቸው ጋር ሆነው የአርበኝነት ሥራ ይሠሩ ነበር። ያ የሆነው ተገድደው ሳይሆን የጀግና ልጅ ሕፃንም ሆኖ ጀግና ስለሆነ እና የአገርን ፍቅር ስለሚያውቅ ነው›› ይላሉ።
ያን ግዜ የነበረው ጦርነት በሕፃናት ልብ ሳይቀር የአገርን መውደድ የሰነቀረ ነው ሲሉ አነሱ። አክለውም ‹‹አሁን ላይ ያለው ጦርነት ግን በሠላም ቤታቸው የሚኖሩ ልጆቻችንንም በቁም የሚገድል እና ግራ የተጋባ ማንነት እንዲኖራቸው የሚያደርግ እንጂ፣ ልጆቻችንን ስለአገራቸው እንዲያውቁና መልካም እንዲያስቡ ሲያደርግ አናይም›› ይላሉ።

በመንግሥትም ሆነ በማኅበረሰቡ ዘንድ በልጆች አስተዳደግና የሥነ-ልቦና ግንባታ ላይ የሚሠራው ሥራ በእጅጉ አናሳ ነው። በስፋት የጦርነት ወሬ በመስማት ያደጉ ልጆች ከፍ ሲሉም የሚጠብቃቸው ይኼው ያደጉበት ወሬ ታሪክ ሆኖ ነው። በዚህም የተሻለ ዕሳቤና ግልጽ የሆነ የሕይወት ዓላማ እንዳይኖራቸው ያደርጋል። በተበከለ አስተሳሰቡ ያለዓላማ ያደጉ ሕፃናት ደግሞ ከፍ ቢሉም ለሱስ እና ለዝርፊያ የሚውል ዕሳቤ እንጅ ሌላ አይኖራቸውም። በከንቱ ሲዘባነኑ ከመኖር ሌላም ያደጉበት የጦርነት ወሬ እንደ ልጓም እየመራቸው አገርን በሚበታትን የሽብር ድርጊት ውስጥ መቀላቀላቸው አይቀርም።

ስለሆነም የልጆችን የነገ ማንነት መልካም በሚባል ሰብዕና በመገንባት የተሻሉ አገር ተረካቢዎች ማድረግ ይገባል። ጆሯቸው የጥይት እና የፍጅት ወሬ እየሰማ፣ ዐይናቸውም የደም ዥረት ዕያየ ያደጉ ልጆች ነገ ራሳቸው ሠላም ሆነው ለሌላው ሠላም ያስገኛሉ ብሎ ማሰብ ሞኝነት ነው። ሠላም የረበበባት መልካም አገር ለመገንባትና እሷንም ለማስቀጠል ሕፃናት ላይ መሥራት ዋናውና ቀዳሚው መፍትሔ ነው። መልካም ዕያዩና መልካም እየሰሙ፣ መልካም እያሰቡ እንዲያድጉ ያለማቋረጥ ወጥ በሆነ መልካም ሥራ ሥነ- ልቦናቸውን መቅረፅ እንደሚያስፈልግ ዕሙን ነው።

በዚህ ላይ የሥነ-ልቦና ባለሙያዋ ትዕግስት ዘሪሁን፣ ሕፃናት በለጋ ዕድሜያቸው የሚያዩትን እና የሚሰሙትን ነገር የሚተረጉሙበት መንገድ የተለየ ነው ይላሉ። እንደ አዋቂ ሰው ማመዛዘንና ክፉውን ከደጉ መለየት ስለሚያቅታቸው ስለምናሳያቸውና ስለምናስደምጣቸው ነገር ሁሉ መጠንቀቅ ተገቢ ነው ሲሉ ያሳስባሉ።

ባለሙያዋ አክለውም ልጆች በሕፃንነታቸው የሚያዩትና የሚሰሙት ነገር መልካም ካልሆነ ከራሳቸው፣ ከወላጆቻቸውና ከጓደኞቻቸው ብሎም ከዓለም ጋር ያላቸው ግንኙነት እንዲሁም ምልከታ የተዛባ ይሆናል ብለዋል።
ማንም ሰው ከማኅበረሰቡና ከዓለም ጋር የሚኖረውን ግንኙነት የሚያዳብረው ገና ከልጅነቱ ነው የሚሉት ባለሙያዋ፣ ልጆች የሚውሉበት ስፍራ በፍርሀት፣ በጭንቀትና በከፍተኛ ቁጥጥር የተሞላ ከሆነ በቋሚነት ምቹ ያልሆነ ባህሪ ይኖራቸዋል ሲሉ አስረድተዋል።
ባለሙያዋ በሰሜን ኢትዮጵያ በቀጠለው ጦርነት ወላጆቻቸው ሲገደሉ ያዩና የሚያዩ፣ ጦር ግንባር ላይ የተሰለፉ፣ በመጠለያ ቦታ ጦርነት ሸሽተው በረሀብና በችግር የሚገኙ ሕፃናት መኖራቸውን ያወሳሉ። በዚህም ሕፃናት የአዕምሮ እና የማንነት ቀውስ ብሎም ማኅበራዊ ውድቀት እንዳያጋጥማቸው ዛሬ ላይ ያለው የአገራችን ቀውስ ቢያንስ እነሱና እንዳይጎዳ ወላጆች መጠንቀቅ አለባቸው ባይ ናቸው።

ትዕግስት በንግግራቸው ይህን አሉ፣ ‹‹ሕጻናት ከቤተሰቦቻቸውና ከአካባቢያቸው የሕይወታቸውን መሠረት ይይዛሉ። በዚህ መሠረትም እኛ በጎ ከሆን በጎ ሰዎች ይሆናሉ፤ መጥፎ ከሆንና መጥፎ ነገር እያሳይን ካሳደግናቸው ደግሞ እስከ መጨረሻው መጥፎ ሰዎች ሆነው የመቅረታቸው ዕድል ሰፊ ነው።››


ቅጽ 3 ቁጥር 152 መስከረም 22 2014
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!