የእለት ዜና

የዴልታ ቫይረስ ወረርሺኝ መስፋፋት

ከኹለት ዓመት በፊት አንድ ብሎ በኢትዮጵያ የመግባቱ ነገር የተሰማው ኮቪድ 19 ወረርሺኝ፣ ከ340 ሺሕ በላይ ሰዎችን አዳርሷል። በመካከል ቀንሶ የነበረው የሞት መጠንም አሁን ሦስተኛ በተባለው የወረርሺኙ ማዕበል ከ40 እያለፈ ሲሆን፣ በትንሽ በትንሹ እየጨመረ እንደ ዋዛ ከአምስት ሺሕ በላይ ሰዎች ሕይወት መጥፋት መንስኤ ሆኗል።

ወረርሺኙ ይህን መልክ የያዘውና እየተባባሰ የመጣው ለኢትዮጵያ እንግዳ የነበረው ‹ዴልታ› የተባለው የቫይረሱ ዝርያ መገኘቱን ተከትሎ ነው። ይህ የዚህ ዝርያ ስርጭት በዚህ መጠን እንዲስፋፋ የተለያዩ ምክንያቶች አሉ ያሉን ደግሞ በጤና ሚኒስቴር የኮቪድ ወረርሽኝ ምላሽ ግብረ-ኃይል አስተባባሪ መብራቱ ማሴቦ ናቸው።

‹‹የኮቪድ ቫይረስን በደንብ መረዳት ያስፈልጋል። አንዳንድ ቫይረሶች በተፈጥሮ በጣም ኃይለኛ ሆነው ከፍተኛ ደረጃ ይደርሳሉ። ከዛ ደግሞ ተመልሰው ይወርዳሉ። አንዳንዶቹ ደግሞ ይጠፋሉ።›› ሲሉ የሚያስረዱት መብራቱ፣ እንደማሳያ የወፍ ጉንፋንን ያነሳሉ። የወፍ ጉንፋን በመካከለኛው ምሥራቅ ላይ ምልክቱ ታይቶ የተወሰኑ ሰዎችን ለሞት ቢዳርግም፣ ቫይረሶቹ ጠንካራ ካለመሆናቸው የተነሳ አካባቢያዊ ሁኔታዎች ተመርኩዞ ቶሎ ጠፍተዋል።

ከኮቪድ ጋር በተያያዘም ቫይረሱ ወይ ይጠፋል አልያም ቀዝቀዝ ብሎ ወደ ጉንፋን ይቀየራል የሚል ዕይታ በአንዳንድ ሰዎች ዘንድ እንደነበር መብራቱ ያስታውሳሉ። አሁን ላይ ወረርሺኙ ኢትዮጵያ ከገባ ኹለት ዓመት ሊሞላው ቢሆንም፣ በዚህ ጊዜ ውስጥ እየተባባሰና ባሕሪውን እየቀየረ ይገኛል። በዚህ መሠረት አሁን አዲስ የተፈጠሩ አምስት ዓይነት የኮቪድ ቫይረስ ዝርያዎች እንዳሉ ታውቋል።

ከእነዚህ መካከል የዴልታ ቫይረስ መከሰት አሁን ላለው ስርጭት መፍጠን ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው የኮቪድ ወረርሽኝ ምላሽ ግብረ-ኃይል አስተባባሪው መብራቱ ነግረውናል። አስቀድሞ የተያዙትንም እንደገና በመያዝ እያጠቃ ይገኛል ያሉ ሲሆን፣ ይህ የዴልታ ቫይረስ ጠንካራ ዝርያ መሆኑንም አክለው ጠቅሰዋል።

ይህ ዴልታ ቫይረስ ጠንካራ በመሆኑ የተነሳ በዓለም ላይ ወደ 160 አገራት ላይ ጉዳቱን አድርሷል። እስከአሁን ከነበረው አንጻርም በዓለም ዐቀፍ ደረጃ በጣም ከፍተኛ የሆነ ስርጭት ያለው ዝርያ ሲሆን፣ ከዚህ በተጨማሪ መግደል የሚችልበትን አቅም ጨምሮ እና ቀድሞ እንደነበሩት የኮቪድ ዝርያዎች ተያያዥ በሽታ ያለባቸውን ብቻ የሚያጠቃ ሳይሆን ሁሉንም የማኅበረሰብ ክፍል በከፍተኛ ሁኔታ እያጠቃ የሚገኝ ነው ብለዋል።
አዲስ ማለዳ ይህን ጥንቅር በምታዘጋጅበት ሰዓት ከ800 በላይ ሰዎች በጽኑ ሕሙማን ክፍል ይገኛሉ፤ በየቀኑም በርካቶች በቫይረሱ የተነሳ ለሞት ይዳረጋሉ።

ይህን ለመቀነስና ለመከላከል በሀኢትዮጵያ ኮቪድ-19 የገባ ወቅት ኅብረተሰቡ የመከላከያ መንገዶችን እየተጠቀመ ነበር። ማስክ ማድረግ፣ እጅን መታጠብ፣ ሳኒታየዘር መጠቀምና የመሳሰሉት የሁሉም ሰው የየእለት ተግባር ሆኖ ነበር።
በመንግሥት በኩል የሚተላለፉ መልክቶችም በጣም ጠንካራ ነበሩ። ቀስ በቀስ ግን መንግሥትም ሆነ የሚመለከታቸው አካላት ሌሎች ሥራዎች ላይ በመጠመዳቸው ግንዛቤ ማስጨበጫ መንገዶች እየቀነሱ ሲመጡ ሕጎችም ማጥበቅ እየቀለለ መጣ። ኅብረተሰቡም እየተሰላቸ ወደ ቀደመ የኑሮ ሩጫው በመመለሱ ኮቪድ እኔን አይዘኝም፤ ቢይዘኝም ምንም አያረገኝም በሚል ችላ እንዳለው መብራቱ ጠቅሰዋል።

መብራቱ ጤና ሚኒስቴር ያደረገው ጥናት ያወሳሉ። ጥናቱ እንደሚያሳየው 99 በመቶ የኅብረተሰብ ክፍል ስለኮቪድ ምንነት፣ መከላከያዎቹ እና ጥንቃቄ መንገዶችን በደንብ ያውቃል። ነገር ግን አብዛኛው ሰው በኮቪድ አልያዝም፤ ኮቪድ የሚይዛቸው በእድሜ የገፉና ተያያዥ በሽታ ያለባቸው ናቸው የሚል የተሳሳተ አመለካከት አለው።

‹‹ይህ አኔን አይዘኝም የሚለው አስተሳሰብ የስርጭቱን መጠን በይበልጥ ጨምሮታል›› የሚሉት መብራቱ፣ በፊት የነበረው ጥንቃቄ መቀነሱም ከሁሉም በላይ ለቫይረሱ ስርጭት መጠን መጨመር አስተዋጽኦ ያበረከተ ነው ብለዋል። በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የወጡትን መመሪያዎች ማለትም ከ50 በላይ ሰዎች እንዳይሰበሰቡ፣ በሮችና መስኮቶችን በመክፈት አየር ማስገባት፣ የሰርጎችንና የልደቶችን መከልከል ማስፈጸም አስፈላጊ ነበር ብለዋል። ነገር ግን ይህንን መመሪያ ለማስፈጸም የሕግ አስከባሪ አካላት በአገራዊ ጉዳዮች ምክንያት በሙሉ አቅማቸው እየሠሩ እንዳልሆነ ነው ያነሱት።

አያይዘው ግን ሁሉም በየተቋማቱ የራሳቸው እቅድ እንዲኖራቸውና ኮቪድን እንዴት መከላከል እንደሚገባ በቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ጋር በመሆን የተቋሙ እቅድ ተግባራዊ ለማድረግ እየተሠራ ነው ሲሉ ጠቁመዋል። ለዚህም የሁሉም ክፍለ ከተማ ሥራ አስፈጻሚዎችን ጨምሮ በከንቲባዋ የሚመራ በየ15 ቀን የሚገመገም ግብረ ኃይል እንደገና እንዲደራጅ መደረጉን አስታውሰዋል።

‹‹አሁንም ትልቁ የመፍትሄ ቁልፍ ያለው ኅብረተሰቡ ጋር ሲሆን ጥንቃቄም ብቻ ሳይሆን መከተብም አስፈላጊ መሆኑን መረዳት ይገባቸዋል። ክትባት ከመጠንቀቅም ባለፈ ለሁሉም ሰዎች የሚሠራ የቅደመ መከላከል ተግባር ያለው ነው። ክትባት እንደሚከላከል ማሳያ የሆነው የጤና ባለሙያዎች ናቸው። አሁን እየተስፋፋ ባለው የጽኑ ህሙማን ክፍል የሚገቡ ሰዎች ውስጥ የጤና ባለሙያዎች የሉበትም። ይህ ደግሞ የሚያሳየው የተከተቡ ሰዎች ካልተከተቡ ሰዎች ጋር የመከላከል አቅማቸው መጨመሩን ነው። የተከተቡ ሰዎች ቢያዙ እንኳን ጽኑ ሕመም ሳይሆንባቸው ቶሎ ማገገም ይችላሉ።›› ሲሉም አስረድተዋል።

ክትባቶች በሁሉም የጤና ጣቢያዎች የሚሰጥ መሆኑን የገለጹት መብራቱ፣ የሚከተበው የሰው ብዛት ግን በሚፈለገው ደረጃ አይደለም ብለዋል። ይህ ደግሞ ኅብረተሰቡ ጋር ከፍተኛ የግንዛቤ እጥረት መኖሩን ያሳያል። ሰው በክትባት መዳን እየቻለ በሚናፈሱ የተሳሳቱ መረጃዎች ውዥንብር ውስጥ በመግባት ክትባትን ፈርቶ አለመከተቡ የቫይረሱን ስርጭት እንዲጨምር አድርጎታል።

ምን ይደረግ?
እንደ መብራቱ ገለጻ ጤና ሚኒስትር እንደ ተቋም መመሪያዎችን ለማጥበቅ ያቀደ ሲሆን፣ የተለያዩ የመንግሥት አካላት በጋራ ሆነው እንዲሠሩ እየተደረገ ነው። ነገር ግን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ብቻውን ለውጥ ማምጣት ስለማይችል ተከታትሎ የሚያስፈጽሙት የመንግሥት አካላትና ኅብረተሰቡ ጋር በጋራ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል።

በቅርቡ የሚጀመረውን ትምህርት ተከትሎ መምህራን መከተብ ግዴታ እንዳለባቸው መገለጹ ያወሱት መብራቱ፣ በመሆኑም መምህራን በየትኛውም ዓለም የመከተብ ግዴታ አለባቸው ሲሉ ጠቁመዋል። ‹‹ሰዎች መረዳት ያለባቸው ይህ የዴሞክራሲ ወይም የነጻነት መብት ጉዳይ አይደለም። የግለሰብ ነጻነትን መተግበር የሚቻለው ሌሎችን የማይጎዳ ሲሆን ብቻ ነው። ሰዎች ልጆቻቸውን ትምህርት ቤት እየላኩ መምህራኖች አንከተብም የሚሉ ከሆነ ሕጻናትን አደጋ ላይ ለመጣል እንደተዘጋጁ ይቆጠራል።›› ሲሉ አሳስበዋል።

ሳልከተብ አስተምራለው የሚሉ መምህራን ካሉ፣ ሌሎችን በተለይ ደግሞ ሕጻናትን አደጋ ላይ በሚጥል ሁኔታ መቀጠል መፈለጋቸው ለሞራላቸው ራሱ ሊከብዳቸው ይገባል ብለዋል። መምህራን ለሌሎች ሞዴል መሆን ይገባቸዋል እንጂ ያሉ ሲሆን፣ በጤና ሚኒስትር በኩል ያለው አስገዳጅ ሕግ ከሚተገበሩ መከላከያዎች ጋር እንጂ ከክትባት ጋር በተያያዘ በግድ ተከተቡ የሚል እንዳልሆነም ገልጸዋል።

በድምሩ ግን ተላላፊ በሽታ ያለበት ሰው የጥንቃቄ መንገዶችን አለመጠቀሙ በራሱ ወንጀል ነው ብለዋል። ምክንያቱን ሲያስረዱም፤ ‹‹በግለሰቡ አለመጠንቀቅ ኀብረተሰብ ይጎዳል። የሌላን ሰው ሕይወት የሚጎዳ ነገር ላይ ጥንቃቄ አለማድረግ በየትኛውም አገር ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም። የኮቪድ ወረርሺኝ ደግሞ ሞት ድረስ የሚያደርስ ነው። ክትባቱ የራሱ የሆኑ የጎንዮሽ ጉዳት ቢኖረውም ለጥቂት ሰዓታት የሚቆይ ነው። ትንሽ ሰዓት ለክትባት መታገስ ባለመቻል እስከ ሞት በሚያደርስ በሽታ መጠቃት የሚፈልግ ሰው ያለ አይመስለኝም።›› ሲሉም ዕይታቸውን አካፍለዋል።

በተለይ በአሁኑ ሰዓት ባህሪውን ቀይሮ የመጣው የዴልታ ቫይረስ ሁሉንም የሚያጠቃ ስለሆነ በቀን ከ30 ሰዎች በላይ እየሞቱ ነው። ከእነዚህ የሚሞቱ ሰዎች መካከል ደግሞ የቤተሰብ አስተዳዳሪ እና የልጅ አሳዳጊዎች ይኖራሉ፤ አሉም። ከአንድ ቤተሰብ አራት ሰው ያህል እየሞተ ነው ተብሎ እየተገለጸ አሁንም ክትባቱን የሚወስደው በጣም ጥቂት ናቸውና ማኅበረሰቡ ሁኔታውን ተረድቶ የጥንቃቄ እርምጃን ጨምሮ ክትባቱንም ሊወስድ ይገባል ሲሉ መብራቱ መክረዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 152 መስከረም 22 2014
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!