የእለት ዜና

የአዲሱ መንግሥት የቤት ሥራዎች

የ2014 ወርሃ መስከረም የአዲስ መንግሥት ምሥረታ ጉዳይ ከነባር የኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮች አንድ አንዱ ሆኗል። ክልሎችና ኹለቱ ከተማ አስተዳደሮች ከሰሞኑ የተወሰኑ ነባር ሹማምንትን ሸኝተው፣ ለየወንበሩ አዳዲስ የተባሉትን ሰይመውና አጽድቀው በ‹መልካም የሥራ ዘመን› ምኞት ወደ ሥራ ዘልቀዋል። የፊታችን ሰኞ መስከረም 24/2014 ደግሞ የ6ኛው አገር ዐቀፍ ምርጫ አሸናፊ ብልጽግና ፓርቲ አዲስ የፌዴራል መንግሥት ይመሠርታል።
አዲስ የሚመሠረተው መንግሥት ምንም እንኳ ኢትዮጵያ አሁን ላይ ላሉባት መልከ ብዙ ችግሮች እንግዳ ባይሆንም፣ በፖለቲካ እና በኢኮኖሚ የውጭ እና ውስጥ ጫና በበረታባት ጊዜ የሚመሠረት እንደመሆኑ ብዙ የቤት ሥራ እንደሚጠብቀው ግልጽ ነው።
ከቀደመው ይልቅ ብዙ የሚጠበቅበት በመሆኑም ፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ከመቅረፍ ባለፈ ለዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እንዲተጋ ይጠበቃል። የአዲስ ማለዳው መርሻ ጥሩነህ ይህን በሚመለከት የተለያዩ ምሁራንና ባለሞያዎችን በማነጋገር ጉዳዩን የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርጎታል።

ኢትዮጵያ ደርብርብ ችግሮች በተደቀኑባት በዚህ ወቅት በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ አሸናፊ የሆነው ብልጽግና ፓርቲ የፊታችን ሰኞ መስከረም 24/2014 አዲስ መንግሥት ይመሠርታል። ይህም አዲስ መንግሥት ብዙ የቤት ሥራዎች ከፊቱ ተደቅነው እየጠበቁት ነው።
ኢትዮጵያ በተለያየ አቅጣጫ ውጥረት ውስጥ ገብታለች። ከተጀመረ አንድ ዓመት ሊሞላ አንድ ወር በቀረውና በሰሜኑ የአገሪቱ አካባቢዎች ከተቀሰቀሰው ጦርነት ጋር በተያያዘ የአውሮፓውን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጫና አለ። ወዲህ ደግሞ ከሕዳሴው ግድብ ጋር በተገናኘ ከጎረቤት አገሮች ከግብጽና ሱዳን ጋር ያልተቋጨ ውዝግብ ላይ ትገኛለች። ከሰሜኑ ጦርነት እና ተያያዥ ችግሮች በተጨማሪ ከሱዳን ጋር ያላት የድንበር ውዝግብና የ‹ኢትዮጵያ ገፋችን› ክስ የቀጠለና እልባት ያላገኘ ጉዳይ ነው።

ከአገር ውስጥ እና ከውጭ የፖለቲካ ችግሮች በተጨማሪ ኢትዮጵያ በኢኮኖሚው ዘርፍም እየተፈተነች እንደሆነ የዘረፍ ባለሙያዎች ያነሳሉ። በኢኮኖሚው የሚፈትናት ዋነኛ ችግር በየጊዜው ያለማንም ከልካይ እያሻቀበ የመጣው የዋጋ ንረት ሲሆን፣ ይህም ዜጎችን ክፉኛ እያስመረረ ይገኛል። የዋጋ ንርቱ በየወሩ እያሻቀበ ይምጣ እንጂ እስካሁን ሁነኛ መፍትሔ ተገኝቶለት በቁጥጥር ስር ሊውል አልቻለም።

እነዚህና ሌሎች እልባት ያላገኙ ችግሮች የተደቀኑባት ኢትዮጵያን ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ለመምራት የፊታችን ሰኞ የሚመሠረትው አዲሱ መንግሥት በፖለቲካውም ይሁን በኢኮኖሚው ዘርፍ ብርቱ የቤት ሥራዎች እና ተግዳሮቶች ከፊቱ እንደሚጠብቁት የተለያዩ ባለሙያዎች እየገለጹ ነው። በተለይ የሰሜኑ ጦርነት እልባት አለማግኘቱና ጊዜው በተራዘመ ቁጥር የሚያደርሰው ዘርፈ ብዙ ኪሳራ ለአዲሱ መንግሥት ከባድ ተግዳሮት ሊሆን እንደሚችል እየተጠቀሰ ይገኛል።

አዲስ ከሚመሠረተው የፌዴራል መንግሥት ምሥረታ ቀድመው ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የሚዘልቅ ምክር ቤት መሥርተዋል። አዲስ መንግሥት ከመሠረቱ ክልሎች መካከል ኦሮሚያ ክልል አዲስ ባዋቀረው ካቢኔ የኦሮሞ ነጻነት ግንባሩን (ኦነግ) አራርሶ ቢቂላን አካትቷል። ኦነግ ለኹለት መከፈሉን ተከትሎ አራርሶ ቢቂላ የሚመሩት ኦነግ መኖሩ ይታወሳል።

አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም ‹አዲስ ምዕራፍ› ብሎ በሠየመውና ባሳለፍነው ማክሰኞ መስከረም 18/2014 ባካሄደው ጉባኤ፣ አዲስ መንግሥት መመስረቱን አስታውቋል። ከተማ አስተዳደሩ ‹አዲስ ምዕራፍ› ብሎ በሠየመው አዲስ መንግሥት፣ ሰኔ 14/2014 በተካሄደው ምርጫ ያልተመርጡ ኹለት የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አባላትን በካቢኔው ውስጥ አካትቷል። ከተማ አስተዳደሩ ያካተታቸው የፖለቲካ ፓርቲ አባላት ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ግርማ ሰይፉን እና ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) የሱፍ ኢብራሂምን ነው።

እነሆ የቤት ሥራ!
አዲስ የሚመሠረተው መንግሥት ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ወቅታዊ ሁኔታ አንፃር በርካታ የቤት ሥራዎች እንደሚጠብቁት ይጠበቃል። ከዚህ መካከል በቀዳሚነት የሚጠቀሰው አሁን ላይ ኢትዮጵያ እየፈተናት የሚገኘው ውስብስብ የፖለቲካ ችግር እና በኢኮኖሚው ዘርፍ በየጊዜው እየታየ ያለው የዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነት ይገኙበታል። የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ የቤት ሥራዎች ጎልተው ይታዩ እንጂ በሌሎች ዘርፎችም ቀላል የማይባሉ ሥራዎች እንደሚጠብቁት ግልጽ ነው።

የባህር ዳር ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም ዐቀፍ ግንኙነት መምህር ታደሰ አክሎግ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ወቅታዊ ሁኔታ አንፃር የአዲሱን መንግሥት ቀጣይ የቤት ሥራ በሚመለከት ሐሳባቸውን አካፍለዋል። እንደ ታደሰ ገለጻ በቀዳሚነት የአዲሱ መንግሥት የቤት ሥራ ሊሆን የሚችለው እልባት ያላገኘውን የሰሜኑን ጦርነት እልባት መስጠት እና የዜጎችን ሰላምና ደኅንነት ማስጠበቅ ነው።

በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት የተፈጠረው የውጪ ጫና እና የዜጎች መፈናቀልና የንብረት መውደም የአዲሱ መንግሥት የቤት ሥራን ቀላል እንዳይሆን ያደርገዋል። ጦርነቱ በፖለቲካም ይሁን በኢኮኖሚ ላይ ቀላል የማይባል ተጽዕኖ አለው ያሉት የፖለቲካ መምህሩ፣ አዲሱ መንግሥት ጦርነቱን በአጭር ጊዜ እልባት በመስጠት አዲስ የፖለቲካ ምህዳር መፍጠር እንደሚጠበቅበት ይጠቅሳሉ።

አዲሱ መንግሥት አዲስ የፖለቲካ ምህዳር ሲፈጥር በተለይ በትግራይ ክልል ያለውን የፖለቲካ አሰላለፍ በአዲስ መተካት እንዳለበት ይገልጻሉ። ይህን ለማድረግ ደግሞ ለጦርነቱ እልባት መስጠትና መቋጨት እንደሚገባ ያሳስባሉ። እንደ ፖለቲካ መምህሩ ገለጻ በትግራይ ክልል ያለውን የፖለቲካ ምህዳር በዜግነት ላይ መሠረት አድርጎ እንደ አዲስ በአዲስ ኃይል ማደራጀት ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ችግር ለማውጣት እንደ አንድ መንገድ ሊያገልግል ይችላል።

ኢትዮጵያ አሁን ለገጠማት ችግር መነሻ የሆነው ለብሔር አደረጃጀትና ፖለቲካ ሽፋን የሰጠው አሁን ያለው ሕገ-መንግሥት መሆኑን የፖለቲካ መምህሩ ያነሳሉ። በመሆኑም አሁን ኢትዮጵያ ለገጠሟት ፖለቲካዊ ችግሮች መነሻ የሆነውን ሕገ- መንግሥት መቀየር የአዲሱ መንግሥት ኹለተኛ የቤት ሥራ መሆን እንዳለበትም አያይዘው ይጠቁማሉ።

ኢትዮጵያ አሁን ላይ የምትተዳደርበት ሕገ-መንግሥት በብዙዎች ዘንድ ተቃውሞ የሚነሳበት ሲሆን፣ በተደጋጋሚ ሕገ- መንግሥቱ እንዲሻሻል የሚጎተጉቱ ብዙዎች ናቸው። መምህር ታደሰ በበኩላቸው ሕገ መንግሥቱን ማሻሻል ለጥያቄ የሚቀርብ ጉዳይ አለመሆኑን በማንሳት፣ መሻሻል ያለበት የብሔር አደረጃጀትን በሚያስቀር እና የዜግነት ፖለቲካን እና ብዘኀነትን በሚያጎላ መልኩ መሆን አለበት ይላሉ።

ለዚህም የሚመሠረተው መንግሥት ሁሉን አካታች የሆነ የፖለቲካ ውይይት ማድረግ እንዳለበት ያመላክታሉ። ‹‹አዲሱ መንግሥት አሁን ያለውን የፖለቲካ ምህዳር ለመቀየር ቅድሚያ የተበላሸውን የፖለቲካ እና የሕገ-መንግሥት ለውጥ ማድረግ አለበት። ይህን ሲድረግ ደግሞ በቅድሚያ ሁሉን አካታች የሆነ የፖለቲካ ውይይት በማካሄድ የዜጎችን ፍላጎት ያማከል መግባባት ላይ መድረስ ይገባል›› ሲሉም አሳስበዋል።

በኢትዮጵያ አሁን ካለው ወቅታዊ ሁኔታ አንፃር የዜጎችን ደኀንነት ማስጠበቅ እና እንደ አገር ያጋጠመውን ጦርነት ማስቆም ቅድሚያ የሚሰጠው የሕልውና ጉዳይ ነው ይላሉ እኚህ የፖለቲካ መምህር። እናም ያሉትን ችግሮች ከማስተካከል ጎን ለጎን የፖለቲካ ውይይትና አገራዊ መግባባት በፍጥነት ሊደረግ እንደሚገባ፣ ሁነቱ ለነገ እየተባለ ጊዜ ሊሰጠው የማይገባ በመሆኑ በቅርብ መጀመር እንዳለበት ይመክራሉ።

አዲስ የሚመሠረተው መንግሥት ከዚህ ቀደም ከነበረው መንግሥት የጠነከረ ፈተና ሊገጥመው እንደሚችል የሚገልጹት ደግሞ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የንግድ ሥራ ኮሌጅ (ኮሜርስ) ኃላፊ ወርቁ መኮንን (ዶ/ር) ናቸው። ‹ሕወሓት መራሽ› ተብሎ በሚጠራው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዲግ) መንግሥት ዘር ተኮር ፖለቲካ መስፋፋቱን ተከትሎ ችግሮች በፈነዱበት ጊዜ አዲሱ መንግሥት መመሥረቱ ችግሩን ከስሩ የማጥራት የቤት ሥራ እንደሚኖርበት ማድረጉን ይገልጻሉ።

ኢሕአዲግ ኢትዮጵያን በገዛባቸው ዓመታት የተከተለው መንግሥታዊ አደረጃጀት ብሔር ተኮር እንደነበር የሚያነሱት ወርቁ፣ አደረጃጀቱ አሁን ላይ በአገሪቱ ውስብስብ ችግሮች እንዲጋረጡ አድርጓል ይላሉ። በመሆኑም አዲሱ መንግሥት በቀድሞው መንግሥት ብሔር ተኮር አደረጃጀት የተበላሸውን የፖለቲካ ምህዳር መቀየር እንዳለበት ጠቁመዋል።

የአዲሱ መንግሥት መንግሥታዊ አደረጃጀት ከላይ የተንሳፈፈ እና የሕዝብን ፍላጎት ያላማከል እንዳይሆን መጠንቀቅ እንደሚገባ የሚያሳስቡት ዶ/ር ወርቁ፣ አዲሱ መንግሥት አደረጃጀቱን እንደቀድሞው ከላይ ከማድረግ ይልቅ ከታች ጠንካራ መሠረት ማስያዝ እንዳለበት መክረዋል።

‹‹አደረጃጀት የሁሉም ነገር መሠረት ነው›› የሚሉት ምሁሩ፣ አሁን የሚታዩ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊና ሌሎችም ችግሮች የሚፈቱት የሕዝብን ፍላጎት መሠረት ባደረገ ጠንካራ አደረጃጀት መሆኑን ያምናሉ። ‹‹ሥራ ያለው ከታች ነው፣ ከላይ የሚሠራ ሥራ ስሩ የተንጠለጠለ ነው›› ሲሉም አዲሱ መንግሥት ከታችኛው የመንግሥት እርከን ለውጥ ካላመጣ እንደ ቀድሞው መንግሥት ከላይ የሚታይ እንጂ የሕዝብ አገልጋይ መሆን እንደማይችል አንስተዋል።

አክለውም የሕዝብ አገልጋይነትን ሲገልጹ፣ ‹‹ሕዝብ ማገልገል ማለት የአንድ ከተማ ከንቲባ መስመር ላይ ወጥቶ መንገድ መጥረግ ሳይሆን፣ ታች ወርዶ የሕዝብን ፍላጎት ማሳለጥ ነው›› ይላሉ። ታዲያ አዲሱ መንግሥት ከላይ መስሎ ለመታየት ሳይሆን ከታች ወርዶ የሕዝቡን ፍላጎት መሠረት ያደረገ ሥር ነቀል ለውጥ ማድረግ ይኖርበታል ባይ ናቸው። የሕዝብን ፍላጎት መሠረት ያደረገ ሥራ የሚሠራ መንግሥት አደረጃጀቱን ከስር መጀመር አለበት የሚሉት ምሁሩ፣ የሕዝብ ችግር የሚቀረፈው ከላይ በወረደ አመራር ብቻ ሳይሆን ከሥር ባሉ አስፈጻሚዎች የአገልጋይነት ስሜት መሆኑንም አያይዘው ይገልጻሉ።

ኢትዮጵያን ወጥሮ የያዛት የብሔር ፖለቲካ አደረጃጀት በተለይ በወጣቱ ትውልድ ላይ ስር መስደዱን የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ። በኢሕአዴግ መንግሥት እንደተጋነነ የሚነገርለት የብሔር አደረጃጀትና አስተሳሰብ ለአዲሱ መንግሥት ቀላል የማይባል የቤት ሥራ መሆን የሚገልጹት ዶ/ር ወርቁ በበኩላቸው፣ አዲሱ መንግሥት የብሔር አደረጃጀትን ለማቀስረት በሕዝቡ ሥነ ልቦና ላይ ሰፊ ሥራ መሥራት እንዳለበት ያስገነዝባሉ። የብሔር ፖለቲካ በቀላል የማይቀየርና ጊዜ የሚፈጅ ጉዳይ ቢሆንም ከታች ከመሠረቱ ተጀምሮ በጊዜ ሒደት መቅረት እንዳለበት ዕይታቸውን አካፍለዋል።

የፖለቲካ መምህሩ ታደሰ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የተንሰራፋው የብሔር አደረጃጀት ኢትዮጵያ አሁን ለገጠማት ችግር መነሻና መሠረት መሆኑን ይገልጻሉ። ችግሩን ለመፍታት ሰፊ ጊዜ እንደሚጠይቅ የዶ/ር ወርቁን ሐሳብ የሚጋሩት መምህሩ፣ ከአሁኑ ጀምሮ በብሔራዊ ደረጃ ዕርቅና መግባባት እንደሚያስፈልግም አያይዘው አንስተዋል።

‹‹ጥላቻ እና በቀልን ወደ ኋላ ማስቀረት ካልተቻለ ወደ ፊት መሄድ አይቻልም›› የሚሉት የፖለቲካ መምህሩ፣ ጥላቻና በቀልን ለማስቀረት ከልብ የሆነ ብሔራዊ መግባበት እና ዕርቅ አስፋለጊ መሆኑን ጠቁመዋል። በብሔር አደረጃጀት እና ፖለቲካ በተለያየ የኢትዮጵያ ክፍል የተፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት የተቋቋመው የሠላም እና ዕርቅ ኮሚሽን እስካሁን መሥራት ያለበትን ሥራ አለመሥራቱን አውስተው፣ አዲሱ መንግሥት ጉዳዩን በትኩረት ተመልክቶ ኮሚሽኑ ሥራውን እንዲሠራ ማስቻል አለበት ብለዋል።

አዲሱ መንግሥት ከውስጥ ችግሮች ባሻገር ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የተነሳ ከሱዳንና ከግበጽ ጋር፣ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ባለው ጦርነት የምዕራባውያን ጫና እንዲሁም በድንበር ጉዳይ ደግሞ ከሱዳን ጋር ያለው ያልተቋጨ ውዝገብ ከፊቱ ተደቅነዋል። እነዚህ ችግሮች የአዲሱ መንግሥት የቤት ሥራዎች መሆናቸውን የሚገልጹት የፖለቲካ መምህሩ ታደሰ፣ ያልተቋጩ የውጭ ችግሮችና ጫናዎች በፖለቲካውም ይሁን በኢኮኖሚው ላይ ጫና ማሳደራቸው እንደማይቀር ገልጸዋል።

ከዚህ አንፃር አዲሱ መንግሥት የውጭ ጫናዎች መቋቋም የሚያስችል ስልት መቀየስ ለነገ የማይባል ቀዳሚ የቤት ሥራው ሊደርግ ይገባል ብለዋል። አሁን ያለው የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ቁመና ጥሩ አለመሆኑን የሚገልጹት ታደሰ፣ በውጭ ጫና እና በውስጥ የዋጋ ንረት እንዲሁም በጦርነት ዓውድ ውስጥ የሚገኝ እንደመሆኑ ከፖለቲካው ባሻገር ኢኮኖሚው ልዩ ትኩረት የሚሻበት ጊዜ ላይ ይገኛል ሲሉ አክለዋል።

ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ወቅታዊ ሁኔታ አንፃር ያለው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ልዩ ትኩረት የሚሻ መሆኑን በተደጋጋሚ ሲነሳ ይሰማል። አዲስ ማለዳ ከዚህ ቀደም “ጦርነት እና ኢኮኖሚ” በሚል ርዕስ በሠራችው ሐታተ፣ በጦርነት ወቅት የሚኖር ኢኮኖሚ ከወትሮው የተለየ ትኩረትና አካሄድ እንደሚፈልግ ከባለሙያዎች መረዳቷ ይታወሳል። ዶ/ር ታደሰም ይህንን ሐሳብ ይጋራሉ። በተለይ በጦርነቱ የሚዳከመው ኢኮኖሚ እና ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ ለመጣል የሚደረጉ ጥረቶች ትኩረት የሚሹ ናቸው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በፖለቲካዊ እና በኢኮኖሚያዊ ትኩሳቶች እየተፈተነች እንደምትገኝ ብዙ ማሳያዎችን መጥቀስ ይቻላል። በኢኮኖሚው ዘርፍ የሚታዩ ትኩሳቶች ከፖለቲካ ትኩሳት የመነጩ መሆናቸውን ደግሞ የየዘርፉ ምሁራን በሚሰጧቸው አስተያየቶች ያነሳሉ። በዋናነት አሁን ላይ በኢትዮጵያ ከሚታዩ የኢኮኖሚ ችግሮች መካከል የተጋነነ የዋጋ ግሽበት፣ በጦርነት የሚባክን ሀብትና የተከሰተ ውድመት እንዲሁም ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ የማዕቀብና የብድር ክልከላ ዝንባሌዎች ይጠቀሳሉ። እነዚህን ችግሮች ለመቋቋም አዲሱ መንግሥት፣ አላስፈላጊ ወጪዎችን መቀነስ እንዳለበት ታደሰ ጠቁመዋል።

በተለያዩ አቅጣጫዎች ከፊቱ ተግዳሮት የሚጠብቀውን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከችግር ለመታደግ የአገር ውስጥ ገቢን ከማሳደግ ጀምሮ የውጪ ምንዛሬ ወጪን እስከመቀነስ የሚደርስ አሠራር መከተል እንደሚገባ ተጠቁሟል። በተለይ የአገር ውስጥ ኢኮኖሚ የሚያድግበትን ስልት መከተል ቀዳሚ የኢኮኖሚ ሥራ መሆን እንዳበት የተመለከተ ሲሆን፣ የውጭ እርዳታ ቢቆም ኢትዮጵያ ራሷን ችላ የምትቆምበት የኢኮኖሚ ስልት መከተል የአዲሱ መንግሥት የኢኮኖሚ ዘርፍ የቤት ሥራ ነው።

ኢኮኖሚውን ከሚፈትኑ የፖለቲካ ትኩሳት የወለዳቸው መፈናቀሎችና ንብረት ውድመቶች፣ በፖለቲካውም ይሁን በኢኮኖሚው ላይ ቀውስ እንዳይፈጥር በአፋጣኝ መፍትሔ መፈለግ እንደሚበጅ የሚገልጹት ታደሰ፣ በተለይ በጦርነቱ የተፈናቀሉና የተጎዱ ዜጎችን በዘላቂነት መልሶ ማቋቋም ጦርነቱን እልባት ከመስጠት ጎን ለጎን የመንግሥት ቀዳሚ ተግባር ሊሆን እንደሚገባ ጠቁመዋል። አሁን ላለው ጦርነት እልባት በመስጠት በጦርነቱ የተጎዱና የተፈናቆሉ ዜጎችን መልሶ ማቋቋም ካልተቻለ የተፈናቃዮች ብሶት አሁን ባለው ችግር ላይ ተጨማሪ ችግርና አመጽ ሊፈጥር እንደሚችልም ስጋታቸውን ገልጸዋል።

በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በማኀበራዊ ዘርፍ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት እና ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ዘርፈ ብዙ ችግር እንድትወጣ አዲሱ መንግሥት ከባለፈው መንግሥት ውድቀቶች ማመር እንዳለበት ተመላክቷል።
በመሆኑም አዲስ የሚመሠረተው መንግሥት ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታ ያገናዘበ አካሄደ መከተል እንዳለበት ባለሙያዎቹ የጠቆሙ ሲሆን፣ በፖለቲካው ዘርፍ ያሉ ችግሮች ለኢኮኖሚ፣ ለማኅበራዊና ለሌሎች ችግሮችም መነሻ መሆናቸውን በመገንዘብ በብሔር ሳይሆን በኢትዮጵያዊነትና በዜግነት ላይ የተመሠረተ የፖለቲካ ምሕዳር መፈጠር እንዳለበት ምክረ ሐሳባቸውን አቅርበዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 152 መስከረም 22 2014
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

Comments: 1

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

  1. I AM CONFIDENT DR ABIY HAS LEADERSHIP CAPACITY TO TRANSFORM TO DO WHAT YOU ARE SAYING AND TRANSFORMING eTHIOPIA IN HIS FIRST TERM. His lecture to African academy of leadership where he assembled 100 cabinet members ministers and deputees is excellent. It shows knowledge what it takes to get things done create effective administration by taking personal responsiblity as well collaborating
    Cheers
    Sisay Asefa,PhD, Emeritus professor of Economics

This site is protected by wp-copyrightpro.com