የእለት ዜና

ሹመት እና መልቀቂያ

ሰሞኑን የአዲስ መንግሥት ምሥረታ ነገር የብዙዎችን ትኩረት ስቧል። አንዳንዶች ፈፅሞ የተለየ አዲስ ነገር እንደሚጠብቁ ያስታውቃል። በእርግጥ ቀጥሎ የሚመጣውን አናውቅም። ለጊዜው ግን አዳዲስ ተሿሚዎች መኖራቸው ግልፅ ነገር ቢሆንም፣ በከፍተኛ የሥልጣን ደረጃ ላይ የሚገኙ ለምሳሌ ከንቲባና አስተዳደር እንደሚቀየር መጠበቅ ብዙ የሚያስጉዝ አይደለም።

ባሳለፍነው ሳምንት መንግሥት መሥርተናል፣ አመራሮችን መርጠን ‹ይበል!› ብለን ተስማምቶን አፅድቀናል ካሉ ክልሎች መካከል፤ ፕሬዝደንት የቀየረው የአማራ ክልል ብቻ ነው። ከተማ አስተዳደሮችም ነባር መሪዎቻቸውን አፅድቀውና ተመራርቀው ነው የተሸኛኙት።
ማኅበራዊ ሚድያ ላይ ይህን ሐሳብ ሲያንሸራሽሩ የነበሩ ሰዎች ጥቂት አልነበሩም። በተለይ ምን እየጠበቃችሁ ነበር የሚሉ አስተያየቶች ተመላልሰዋል። ለምን ቢባል፤ የአንዳንድ ሰዎች አኳኋን ብዙ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሸንፈው ለሹመት እንደሚቀርቡ ዓይነት ነው። ሹመቶችን ሰምተው ‹ያው ነው እንዴ?› ያሉ ሰዎችም ‹ብልጽግናን መርጣችሁ ሳለ እንደምን ከሌላ የፖለቲካ ፓርቲ ተሿሚ እንዲኖር ትጠብቃላችሁ?› የሚል አስተያየት ደርሷቸዋል።

በአንፃሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የምርጫው ሰሞን፣ የምርጫው ውጤት ምንም ሆነ ምን ተፎካካሪ ፓርቲዎች የተወሰነ ወንበር እንደሚያገኙና የሥራ ድርሻ እንደሚሰጣቸው ብለው ነበር። የፊታችን ሰኞ መስከረም 24/2014 የጠቅላዩ መንግሥት ምሥረታ ምን እንደሚያሳየን ባይታወቅም፤ ከወዲሁ ግን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና የአማራ ክልል ላይ የተወሰኑ ይህን ቃል የማስፈጸም ሙከራዎች ታይተዋል።

እንደሚታወሰው ከተማ መስተዳደሩ ከአሸናፊው ብልፅግና ፓርቲ ውጪ ኹለት የተፎካካሪ ፓርቲ አባላትን በተለያየ የኃላፊነት ድርሻ ላይ ሰይሟል። ምንም እንኳ ተሿሚዎቹ ተገኝተው ወንበሩን ያልተቀበሉና በፓርቲያቸው በኩል ‹እንቀበል ወይስ አንቀበል?› የሚል ውይይት ላይ ቢሆኑም፤ ምንአልባት ይህ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በተገባው ቃል መሠረት የተፈፀመ ሊሆን እንደሚችል ብዙዎች አስተያየት ሲሰጡ ሰንብተዋል። እንግዲህ ዋናውን መጠበቅ ነው!

ከዚህ ሳይርቅ ብዙ መነጋገሪያ የሆነው ጉዳይ ደግሞ የሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት የፊልሰን አብዱላሂ ‹በገዛ ፈቃዴ ከሥልጣኔ ለቅቄአለሁ› የሚለው ደብዳቤ ነው። ሚኒስትሯ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስገቡት በእንግሊዘኛ የተጻፈ ይህ ደብዳቤ በአዲስ መንግሥት ምሥረታ ዋዜማ ላይ በመሆኑ ብዙዎችን ‹ምን አስበው ነው?› አሰኝቷል።

አንዳንዶች እንደውም የደብዳቤውን አጻጻፍ ተመልክተው ‹በዚህ እንግሊዘኛ ምነው ለተጽእኖ አሳዳሪ አገራት እጃችሁን ከኢትዮጵያ አንሱ ብለው ደብዳቤ ቢጽፉበት› የሚል አስተያየት ሰጥተዋል። ሚኒስትሯ ጥቂት ቀናትን ታግሶ የአዲሱን መንግሥት ምሥረታና ሹመት ለመጠበቅ መታገስ ለምን እንዳቃታቸው ባናውቅም፣ ነገሩ ከብዙ ተቺ አፍ አስገብቷቸዋል።

እንደውም መሥሪያ ቤቱ እምብዛም ፖለቲካዊ ክብደት የማይሰጠው በመሆኑ እንጂ፣ ቢሆን ኖሮ የመልቀቂያ ደብዳቤው ከዚህ የበለጠ ሰፊ ትኩረት ሊያገኝ እንደሚችል ጥርጥር የለውም። ለነገሩም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱም አዲስ አደረጃጀትና ሥያሜ እንደሚጠብቀው ማሳያዎች አሉ። እንግዲህ ለተሿሚዎች መልካም ሥራ ዘመን እንመኛለን።


ቅጽ 3 ቁጥር 152 መስከረም 22 2014
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!