የእለት ዜና

ለሦስተኛ ዙር የተላለፈው ምርጫ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ስደስተኛውን አጠቀላይ ምርጫ በአንድ ቀን ለማካሄድ አስቦ ሲሠራ ቢቆይም፣ በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ባጋጠሙ የጸጥታ ችግሮች፣ በድምጽ መስጫ ሕትመት ብልሽት እና በፍርድ ቤት የተያዙ የምርጫ ጉዳዮች ባለመጠናቀቃቸው ምክንያት ምርጫውን በኹለት ዙር ለማካሄድ ተገዷል። በመሆኑም የመጀመሪያ ዙር ምርጫ እንዲካሄድ በተያዘለት ጊዜ ሰኔ 14/2013 ተከናውኖ ውጤት ይፋ ካደረገ በኋላ ባሳለፍነው መስከረም 20/2014 ኹለተኛውን ዙር ምርጫ አካሂዷል
ቦርዱ ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ ለማካሄድ የምርጫ ቅድመ ሥራዎችን እያከናወነ ባለበት ጊዜ የምርጫ ሂደቱ በተለያዩ የአገሪቱ አከባቢዎች በተፈጠሩ የጸጥታ ችግሮች ከመደበኛ አከባቢዎች እኩል መሄድ አልቻለም። ከጸጥታ ችግር በተጨማሪም በድምጽ መስጫ ወረቀት ኅትመት ላይ ቦርዱ ችግር እንደገጠመው መግለጹ የሚታወስ ነው።

ባሳለፍነው መስከረም 20/ 2014 የተከናወነው ምርጫ በሐረሪ ክልል ሙሉ በሙሉ፣ በሶማሌ ክልል ሙሉ በሙሉ እና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል ደግሞ በኢትዮጵያ 11ኛውን ክልል ለመመሥረት የሚደረገው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝበ ውሳኔ እንዲሁም በክልሉ ሰኔ 14/2013 ምርጫ ባልተካሄደባቸው አካባቢዎች የተካሄደ ነው።

በእለቱ በሐረሪ፣ በሶማሌ እና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ድምጽ አሰጣጥ እና ሕዝበ ውሳኔ የተከናወነ ሲሆን፣ ነገር ግን ተጨማሪ የድምጽ መስጫ ሰዓት የሚያስፈልጋቸው ምርጫ ክልሎች በመገኘታቸው እና ድምጻቸውን መስጠት የሚፈልጉ ዜጎች እድሉን እንዳያጡ በማሰብ በአዋጅ 1162/ 2011 አንቀፅ 49 (4) መሠረት በሐረሪ ክልልና በደቡብ ክልል ሕዝበ ውሳኔ የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ እስከ ምሽቱ ኹለት ሰዓት ድረስ እንዲመርጡ ተደርጓል።

ኹለተኛ ዙር ምርጫ በተካሄደባቸው ክልሎች የምርጫ ውጤት እስከ መስከረም 30/2014 ድረስ ይፋ እንደሚደረግ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኮምዩኒኬሽን አማካሪ ሶሊያና ሽመልስ በምርጫው ዋዜማ በሰጡት መግለጫ ገልጸዋል። ሆኖም በኹለተኛው ዙር ምርጫ የተካሄደባቸው ክልሎች የፊታችን ሰኞ ለሚኖረው አዲስ የመንግሥት ምሥረታ አይደርሱም።

በመጀመሪያው ዙር ምርጫ ያልተካሄደባቸው ሐረሪ ክልል እና ሶማሌ ክልል ሙሉ በሙሉ ሲሆን፣ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ካሉት ሦስት ዞኖች በኹለቱ ዞኖች ምርጫ አልተካሄደም። በሌሎች ክልሎች የመጀመሪያ ዙር ምርጫ ቢካሄድም ያልተካሄደባቸው አካባቢዎች አሉ። ከእነዚህ መካከል በቤኒሻንጉል ጉመዝ ክልል፣ በኦሮሚያ ክልል እና በአማራ ክልል ይገኙበታል።

በኹለተኛው ዙር ምርጫ ያልተካተቱትና ወደ ሦስተኛ ዙር የተላለፉት ክልሎች ያላቸው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች በአማራ ክልል 10፣ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል አራት፣ በኦሮሚያ ክልል ሰባት ሲሆኑ፣ በክልል ደረጃ የክልል ምክር ቤት መቀመጫዎችን በኦሮሚያ ክልል ሰባት፣ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል 13፣ አማራ ክልል ዘጠኝ ናቸው።

በአማራ ክልል በጸጥታ ችግር ምክንያት በኹለተኛው ዙርም ምርጫ ያልተደረገባቸው ስምንት የምርጫ ክልሎች ሲሆኑ፣ ማጀቴ (ማኮይ) የምርጫ ክልል፣ አርጎባ ልዩ የምርጫ ክልል፣ ሸዋሮቢት የምርጫ ክልል፣ ኤፌሶን የምርጫ ክልል፣ ጭልጋ አንድ የምርጫ ክልል፣ ጭልጋ ኹለት የምርጫ ክልል፣ አርማጭሆ የምርጫ ክልል እና ድል ይብዛ የምርጫ ክልል ናቸው። አብዛኛዎቹ በሰሜን ሽዋ ዞን ችግር የተከሰተባቸው ናቸው።

በኦሮሚያ ክልል በጸጥታ ችግር የመራጮች ምዝገባ ባለመካሄዱ ምርጫው ወደ ሦስተኛ ዙር የተሻገረባቸው ሰባት የምርጫ ክልሎች ሲሆኑ፣ ቤጊ የምርጫ ክልል (ምእራብ ወለጋ)፣ ሰኞ ገበያ ምርጫ ክልል (ምእራብ ወለጋ)፣ አያና የምርጫ ክልል (ምሥራቅ ወለጋ)፣ ገሊላ የምርጫ ክልል (ምሥራቅ ወለጋ)፣ አሊቦ የምርጫ ክልል (ሆሮ ጉድሩ)፣ ጊዳም የምርጫ ክልል (ሆሮ ጉድሩ) እና ኮምቦልቻ የምርጫ ክልል (ሆሮ ጉድሩ) መሆናቸውን ቦርዱ አስታውቋል።

በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ካሉት ሦስት ዞኖች ውስጥ አጠቃላይ በአንዱ ብቻ ምርጫ የተካሄደ ሲሆን፣ በኹለተኛው ዙር ምርጫ እንደሚካሄድ ተጠብቆ ነበር። ነገር ግን በክልሉ ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት በመተከልና ካማሺ ዞን ሊካሄድ የሚገባው ምርጫ ወደ ሦስተኛ ዙር እንዲተላለፍ ሆኗል።

በድምሩ ኹለተኛው ዙር ምርጫ በሐረሪ፤ በሶማሌ እና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል ብቻ የተካሄደ ሲሆን፣ በኦሮሚያ፣ በቤኒሻንጉል ጉምዝና በአማራ ክልል ምርጫ ያልተካሄደበቸው አካባቢዎች ለሦስተኛ ዙር ምርጫ ተላልፈዋል። ምርጫ ቦርድ ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ በኹለት ዙር ለማጠናቀቅ ቢያስብም ሳይሳካ ቀርቷል። በመሆኑም በኹለቱም ዙሮች ምርጫ ያልተካሄደባቸው አካባቢዎችን ለማስመረጥ እና የሕዝብ ተወካዮችና የክልል ተወካዮች ምክር ቤት ተወካይ እንዲኖራቸው ለማድረግ ሦስተኛ ዙር ምርጫ ለማካሄድ ተገድዷል።


ቅጽ 3 ቁጥር 152 መስከረም 22 2014
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com