የእለት ዜና

ባሳለፍነው ሳምንት ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች አዲስ መንግሥት መሥርተዋል

በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ገዥው ብልጽግና ፓርቲ አሸናፊ መሆኑን ተከትሎ፣ ባሳለፍነው ሳምንት ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች አዲስ መንግሥት መሥረተዋል።
አዲስ መንግሥት የመሠረቱ ክልሎች መካከል አማራ ክልል አንዱ ሲሆን አዲስ ርዕሰ መስተዳደር ሾሟል። አዲሱ የአማራ ክልል ምክር ቤት የአማራ ክልል ፕሬዝዳንት አድርጎ ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) አድርጎ ሾሟል። ክልሉን ከሰኔ 2011 ጀምሮ ሲመሩ የነበሩት አገኘሁ ተሻገር በይልቃል ተተክተዋል። 75 በመቶ አዲስ ሥራ አስፈፃሚዎች ሲሆኑ 25 በመቶ ነባር ናቸው።

ኹለት የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አባላትም ሹመት አግኝተዋል። በዚሁ መሠረት የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ጣሂር ሙሃመድ የቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ሲሆኑ፣ የአማራ ዴሞክራሲ ኃይል ንቅናቄ (አዴሃን) ሊቀመንበር ተስፋሁን ዓለምነህ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ኃላፊ ሆነው ተመርጠዋል።

ሌላኛው አዲስ መንግሥት የመሰረተው ኦሮሚያ ክልል ሲሆን፣ ክልሉን በመምራት ላይ ያትን የ ሽመልስ አብድሳን ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የክልሉ ፕሬዜደንት አድርጎ መርጧል። በኦሮሚያ ክልል አዲስ በተመሰረተው መንግሥት እራሱን ከምርጫ ያገለለው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር(ኦነግ) አንደኛው ክንፍ መሪ የሆኑትን አራርሶ ቢቆላን የክልሉ ሰራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ አድርጎ ሾሟል።

አዲስ መንግሥት የመሠረተው የሲዳማ ክልል ደግሞ ደስታ ሌንዳሞን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አድርጎ ሾሟል። የጋምቤላ ክልልም በተመሳሳይ አዲስ በመሠረተው መንግሥት ኡሞድ ኡጁሉን የክልል ፕሬዝዳንት አድርጎ መርጧል። አፋር ክልልም እንደዚሁ አወል አርባን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አድርጎ ሾሟል።

በከተማ አስተዳደር ደረጃ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና ድሬድዋ ከተማ አስተዳደር አዲስ መንግሥት መሥርተዋል። አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በምክትል ከንቲባነት እያገለገሉ የነበሩትን አዳነች አቤቤን ከንቲባ አድርጎ የመረጠ ሲሆን፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አዲስ ካቢኔ ኹለት የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አባላት ተካትተዋል። ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ግርማ ሰይፉ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሆነው ሲሾሙ፣ ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የሱፍ ኢብራሂም ደግሞ የመንግሥት ንብረት አስተዳደር ባለሥልጣን ሆነው ተሾመዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 152 መስከረም 22 2014
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!