የእለት ዜና

ለኢትዮጵያውያን ጤና ባለሞያዎች በአረብ ኢሚሬትስ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ስምምነት ተፈረመ

ለኢትዮጵያውያን ጤና ባለሙያዎች በተባበሩት አረብ ኢምሬትስ የሥራ ዕድል ለማመቻቸት የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ።
የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን፣ የሠራተኛ እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዲሁም የጤና ሚኒስቴር በተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ከሚገኘው ‹ሪስፖንስ ፐልስ ሆልዲንግስ› ጋር በሥራ ዕድል ፈጠራ ዙሪያ ስምምነት ተፈራርመዋል ተብሏል።
ስምምነቱን ኢትዮጵያን ወክለው የፈረሙት የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ሲሆኑ፤ በጤናው ዘርፍ ለተፈጠረው የሥራ ዕድል ምስጋና በማቅረብ ‹‹ስምምነቱ ለኢትዮጵያውያን የጤና ባለሞያዎች ከሥራ ባሻገር የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ዘመናዊ በሆነ ሕክምና የታወቀች በመሆኗ ዕውቀት እና ልምድ ለማግኘት ይጠቅማል›› ሲሉ ተናግረዋል።
ስምምነቱ የኢትዮጵያ መንግሥት በቅርቡ ያሻሻለውን የውጭ አገር የሥራ ስምሪት አዋጅ ተከትሎ የተፈፀመ ሲሆን፤ በየደረጃው ከ200 በላይ የጤና ባለሞያዎችን በታዋቂ ሕክምና ማዕከልና የተለያዩ ትልልቅ ሆስፒታሎች ሥራ ለማስጀመር መሆኑም ነው ያብራሩት።
የሪስፖንስ ፐልስ ሆልዲንግስ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ማጆር ቶም ሉዊስ ‹‹ለጤና ባለሞያዎቹ የሥራ ዕድል ማመቻቸት ከሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን፣ ከሠራተኛ እና ማኅበራዊ ሚኒስቴር እና ከጤና ሚኒስቴር ጋር በጋራ ከምንሠራቸው ሥራዎች መካከል የሚጠቀስ ሲሆን በቅርቡ ድርጅቱ ቢሮውን በኢትዮጵያ ይከፍታል።›› ማለታቸውን የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን በማኅበራዊ የትስስር ገጹ አስታውቋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 152 መስከረም 22 2014
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!