የእለት ዜና

ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት በ2013 የ14 ቢሊዮን ብር ኢንቨስትመንት መሳቡን ገለጸ

የምግብ፣ መጠጥ እና ፋርማሲዩቲካል ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት በ2013 በጀት ዓመት 14.7 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ አዲስ ኢንቨስትመቶች መሳቡን ለአዲስ ማለዳ ገለጸ።
ከተመዘገበው አጠቃላይ 14.7 ቢሊዮን ብር ካፒታል መካከል በአገር ውስጥ አግሮ ፉድ ፓርክ 3.1 ቢሊዮን ብር፣ በፋርማሲዩቲካል ፓርክ 6.4 ቢሊዮን ብር እንዲሁም ከፓርክ ውጪ በተሳቡ ፕሮጀክቶች 5.2 ቢሊዮን ብር ተመዝግቧል ተብሏል።

ኢንስቲትዩቱ ለአዲስ ማለዳ በላከው ሪፖርት እንደገለጸው፣ የኢንቨስትመንት አቅም ለማሳደግ የተለያዩ ተግባራት ተከናውነዋል። በዚህም ወደ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፉ 80 የሚደርሱ የአገር ውስጥ እና የውጪ ባለሀብቶችን ለመሳብ ታቅዶ 60 ባለሀብቶችን መሳብ መቻሉን ተጠቅሷል። ይህም ከዕቅድ አንጻር ሲለካ አፈጻጸሙ 80 በመቶ መሆኑ ነው የተጠቆመው።

ተቋሙ የኢንቨስትመንት ካፒታሉን ለማሳደግ በያዘው ዕቅድ መሠረት ተጠናቀው ወደ ማምረት የተሸጋገሩ አዳዲስ እና የማስፋፊያ ፕሮጀክቶች መኖራቸው ተገልጿል። በዛ መሠረት የአግሮ ፉድ ፓርኮች ግንባታ አፈፃፀም 92 በመቶ መድረሱ ተመላክቷል። ተጠናቀው ወደ ማምረት ከተሸጋገሩ ፕሮጀክቶች መካከልም ‹ቡፍሌት› የብቅል ማምረቻ ፋብሪካ እና ኩሪፍቱ ፓኬጂንግ ይገኙበታል። የኢንቨስትመንት ፕሮሞሽን ሥራዎችን ከመሥራት በተጨማሪም ወደ ግንባታ ለገቡት ሥራዎች የመብራት፣ የውጪ ምንዛሪ እንዲሁም የግብዓት አቅርቦታ ላይ ክትትልና ድጋፍ መደረጉ ተጠቅሷል።

በበጀት ዓመቱ ወደ ፓርክ የሚገቡ ኢንዱስትሪዎችን ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ ለ16 ኢንዱስትሪዎች ክትትል ለማድረግ ታቅዶ የነበረ ሲሆን፣ በአፈጻጸም 13 ኢንዱስትሪዎች ክትትል ተደርጎላቸዋል።
በሌላ በኩል ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የንዑስ ዘርፉን የኢንቨስትመንት አቅም ለማሳደግ በሚደረገው ሒደት ውስጥ ለአካባቢ ተስማሚ የሆኑ ኢንዱስትሪዎችን የማበራከት ተግባር ማከናወኑን ጨምሮ አስታውቋል።

በዚህም ኃይል መቆጠብ የሚችሉ ኹለት ኢንዱስትሪዎች የተለዩ ሲሆን እነርሱም ‹ሮራንክ ሼር ካምፓኒ› እና ባለዛፍ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ ናቸው። ‹ቦልት ማልት› ብቅል ፋብሪካ የኃይል አጠቃቀም ላይ በቀላሉ ሙቀትን በማስተላለፍ ኃይል እንዳይባክን የሚረዳ ቴክኖሎጂ (heat exchanger) ተገንብቶለታል። እንዲሁም ካዲላ ፋርማሲቲካል፣ ቦልት ማልት ብቅል ፋብሪካ፣ ሮራንክ ሼር ካምፓኒ፣ አዋሽ ወይን ጠጅ፣ ብሔራዊ አልኮል፣ ሜታ አቦ፣ ባለዛፍ አልኮል ደረጃውን የጠበቀ ፍሳሽ ቆሻሻ ማስወገጃ ገንብተው የሚጠቀሙ ኢንዱስትሪዎች ናቸው። ይህም የአካባቢን ብክለት ከመቆጣጠር ጎን ለጎን የኢንቨስትመንቱን አቅም ለማሳደግ እና ምቹ የሥራ ሁኔታን ለመፍጠር ይረዳል ተብሏል።

ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት በቀጣይም ዋና ትኩረቱን የኢንቨስትመንት እንዲሁም የቴክኖሎጂ እና የምርምር አቅምን በሚያሳድጉ ሥራዎች ላይ እንደሚያደርግ አስታውቋል። በተጨማሪም እነዚህን የመፈፀምና የማስፈፀም፣ የግንባታ ሥራዎችን እንዲሁም የዘርፉን የተወዳዳሪነት አቅም በሚያሳድጉ ሥራዎች ላይ በማድረግ ከባለፈው ዓመት የበለጠ እንደሚሠራ ገልጿል።


ቅጽ 3 ቁጥር 152 መስከረም 22 2014
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com