የእለት ዜና

ለመምህራን በሽያጭ የሚተላለፉ መኖሪያ ቤቶች ዋጋ በ2009 የ20/80 የመግዣ ዋጋ እንዲሆን ተወሰነ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለመምህራን በኪራይ የተላለፉ የጋራ መኖሪያ ቤቶች በሽያጭ እንዲተላለፉ መወሰኑን ተከትሎ፣ የቤቶቹ የመተላለፊያ ዋጋ በ2009 በነበረው የ20/80 የጋራ መኖሪያ ቤት ማስተላለፊያ ዋጋ እንዲሆን ተወሰነ።
የቤቶቹ የማስተላለፊያ ዋጋ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ውሳኔ መሠረት የ2009 የ20/80 የጋራ መኖሪያ ቤት ማስተላለፊያ ዋጋ ሲሆን፣ በዚህም ለስቱዲዮ 2 ሺሕ 483 ብር በካሬ ሜትር መሆኑ ተገልጿል። ለባለ አንድ መኝታ ቤት 3 ሺሕ 438 ብር በካሬ ሜትር ሲሆን፣ ለባለ ኹለት መኝታ ቤት አራት ሺሕ 394 ብር በካሬ ሜትር መሆኑን አዲስ ማለዳ ያገኘችው የሰነድ ማስረጃ ያስረዳል። እንዲሁም ለመምህራኑ የቤት ዓይነት፣ የሳይት፣ ብሎም የወለል ቅያሬ አይፈቀድላቸውም ተብሏል።

በከተማ አስተዳደሩ ውሳኔ መሠረት ለመምህራን በኪራይ የተሰጡ የጋራ መኖሪያ ቤቶች በሽያጭ በሚተላለፉበት ሂደት ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ አመራርና ባለሙያዎች፣ የመምህራን ማኅበር ባለሙያዎች እንዲሁም የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን አመራርና ባለሙያዎች በጋራ ሆነው መስከረም 11/2014 ባደረጉት ስብሰባና ውይይት ቤቶች ለመምህራን የሚተላለፉበትን መስፈርት የያዘ ሰነድ ማዘጋጀታቸውን አዲስ ማለዳ አረጋግጣለች።

በዚሁ ሰነድ መሠረት ኹለት መምህራን በኪራይ ቤት ከተሰጣቸው በኋላ ጋብቻ ፈጽመው ከሆነ፣ በምርጫቸው ከኹለት አንዱ ቤት ላይ የሽያጭ ውል እንዲፈጽሙ ሲደረግ፤ ቀሪው ቤት ለትምህርት ቢሮ ተመላሽ ይደረጋል።
በዚህም መሠረት መምህራን ከ1997 ወዲህ በራሳቸውም ሆነ በትዳር አጋራቸው ሥም ቤትም ሆነ የቤት መሥሪያ ቦታ የሌላቸው ወይም ከዚህ በፊት ኖሯቸው በሽያጭ ወይም በስጦታ ለሦስተኛ ወገን ያላስተላለፉ መሆናቸው ተረጋግጦ መቅረብ አለበት። መምህሩ/መምህሯ ከ1997 ወዲህ በሞት የተለዩ ከሆነ ከፍርድ ቤት የውርስ አጣሪ ሪፖርት ቀርቦ በመመሪያው መሠረት ወራሽ ማለትም ባል፣ ሚስት እና ልጆች ብቻ መሆናቸው ተጠቅሷል።

በተጨማሪም መምህራኑ በመንግሥት ትምህርት ቤት በማስተማር ሥራ ላይ ያሉ መሆኑን ማረጋገጫ ድብዳቤ ከሚያስተምሩበት ትምህርት ቤትና ከሚመለከታቸው አካላት ማቅረብ አለባቸው። እንዲሁም ከጋራ መኖሪያ ቤት ማኅበራት በኪራይ የተሰጣቸውን ቤት እየኖሩበት መሆኑን የሚገልጽ ማስረጃም ማቅረብ እንደሚጠበቅባቸው ነው በሰነዱ የተገለጸው።

በትዳር አብረው ለሚኖሩ ኹለት መምህሮች መካከል አንዳቸው ከመምህርነት ሥራ ቢለቁ ወይም ሥራ ቢቀይሩ በመምህርነት ሥራ ላይ ባለው ሰው ሥም ውል መፈጸም የሚችሉ ሲሆን፣ በሹመት ከመምህርነት ሥራ ላይ የለቀቁ መምህራን ደግሞ በሹመት ላይ ስለመሆናቸው ከፓርቲ ጽሕፈት ቤት ወይም ከትምህርት ቢሮ ማረጋገጫ ደብዳቤ ማቅረብ እንዳለባቸው ሰነዱ ጨምሮ ይገልጻል።

እንዲሁም በ1997 ወይም በድጋሚ ምዝገባ በ2005 የቤት ምዝገባ ተመዝግበው ከሆነ የተመዘገቡበትን ቤት ዕጣ እንጠብቃለን ለሚሉ መምህራን መጠበቅ የሚችሉ ሲሆን፣ በኪራይ የተሰጣቸውን የቤት ውል መዋዋል ከተጀመረበት ቀን ጀምሮ በሦስት ወር ውስጥ ቤቱን ለመንግሥት ማስረከብ እንደሚገባቸው ሰነዱ ላይ የተቀመጠው መስፈርት ያዝዛል።

በመጨረሻም በአሠራር ሂደት የሚያጋጥሙ ችግሮች ለትምህርት ቢሮ እና ለአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ቀርበው ውሳኔ የሚሰጥባቸው ሲሆን፣ የተጭበረበረ መረጃ የሰጡ፣ ያቀረቡ እና የተቀበሉ ተቋማትም ሆኑ ግለሰቦች በወንጀል ሕግ ተጠያቂ ይሆናሉ ተብሏል። በዚህም በተጭበረበረ ሰነድ የተፈጸመ ውል እንደሚፈርስ እና ተቀባይነትም እንደማይኖረው ተጠቅሷል።


ቅጽ 3 ቁጥር 152 መስከረም 22 2014
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!