የእለት ዜና

የብሔራዊ ባንክ መመሪያ አክስሮናል ሲሉ የሪልስቴት አልሚዎች ቅሬታ አቀረቡ

የማይንቀሳቀሱ ንብረቶችን በግዥና በሽያጭ ማስተላለፍ መከልከሉ የንግድ እንቅስቃሴያችንን እየጎዳ ኪሳራ ውስጥ ከቶናል ሲሉ የሪል ስቴት አልሚዎች እና የቤት ገዢዎች ቅሬታ አቀረቡ።
የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች በተለይም ቤትን በግዢና ሽያጭ ማስተላለፍ አለመቻሉ፣ ገዢዎች ለማንኛውም አገልግሎት ቤት መግዛት በሚፈልጉበት ጊዜ የግድ ካርታ በሥማቸው እንዲኖር ስለሚፈልጉ፣ የቤት ሽያጭ መከልከሉ ከፍተኛ ኪሳራ ውስጥ እየከተታቸው እንደሆነ የፍሊንትስቶን ሆምስ የንብረት አስተዳደር ክፍል ኃላፊ ብሩክ ሽመልስ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ፍሊንትስቶን ሆምስ ተገንብተው ያለቁ ሳይሆን እየተገነቡ ያሉ ቤቶችን የሚሸጥ ስለሆነ ባልተጠናቀቁት ፕሮጀክቶች ላይ ከፍተኛ የሚባል ኪሳራ ባይደርስበትም፣ ነገር ግን ያጠናቀቃቸው የተወሰኑ ቦታዎች ገቢ ማስገኘት ስላልቻሉ ሥራ እየተስተጓጎለ ነው ሲሉ ጠቅሰዋል።
ከዚህ በተጨማሪ የካርታ ሥም እየተዘዋወረባቸው የነበሩ ኹለት ፕሮጀክቶች መኖራቸውን የጠቆሙት ብሩክ፣ በመመሪያው የተቀመጠው ክልከላ ትልቅ ኪሳራ አድርሶብናል ነው ያሉት። እንደዚህ ዓይነት አገልግሎቶች ሲቋረጡ ገዢውም ሆነ ሪልስቴቶች ኪሳራ ውስጥ ከመግባታቸውም በላይ ሌሎች ሥራዎች እንዳይከናወኑ ያደርጋል ብለዋል።

የቤት ግንባታ ከሚያስፈልገው ነገር አንዱ ካርታ ነው። ቤት የመሸጥ እና የመለወጥ ሂደት መካከልም ሥም ማዘዋወር ይገኝበታል። በዚህ መሠረት ቤትን በመግዛትና በመሸጥ እንደ ኢንቨስትመንት ከሚጠቀሙ መካከል ቅሬታ ያቀረቡ ቤት ገዢዎችም በበኩላቸው፣ የተጣለው እግድ እስከ መቼ ድረስ እንደሆነ ባለመገለጹ ከፍተኛ ኪሳራ እየገጠማቸው መሆኑን አስታውቀዋል።

‹‹የቤት ልማት በምናከናውንበት ጊዜ አሮጌ ቤቶችን ገዝተንና አፍርሰን አዲስ የመሥራት ሥራ የምናከናውን ስለሆነ አዳዲስ ሥራዎች ለመጀመር ችግር ፈጥሮብናል›› ሲሉ ብሩክ ተናግረዋል። የተጀመሩ ሥራዎችም ቢኖሩ የሥም ማዘዋወር ተግባር ማከናወን ስለማይቻል ተስተጓጉሎብናል በማለት አክለዋል።

እንዲህ ያሉ የንግድ ሥራዎች የማይከናወኑ ከሆነ ገበያው ላይ ከፍተኛ የዋጋ አለመረጋጋት በመፍጠር የቤት ሽያጭ ዋጋ እንዲጨመር እያደረገ ይገኛል። የታገደው የቤት ሽያጭ ከባንክ ጋር የተያያዘ በመሆኑ በፍጥነት ወደ ቀደመ አሠራሩ የማይመለስ ከሆነ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጫና መፍጠሩ እንደማይቀርም ብሩክ አሳስበዋል።

ሰዎች ለመኖሪያ ብቻ ሳይሆን ለተለያየ ዓላማ ነው ቤት የሚገዙት የሚሉት ብሩክ፣ ለባንከ ብድር፣ ለማከራየት፣ መልሶ ለመሸጥ ቤትን እንደ ኢንቨስትመንት ለሚጠቀሙ ገዢዎች መንገድ ስለሚዘጋ የንግድ እንቅስቃሴውንም እየጎዳ ነው ሲሉ ያለውን ችግር አስረድተዋል። እነዚህ የንግድ እንቅስቃሴዎች የሚወሰኑት የመሬት ልማት አገልግሎት ሲኖር በመሆኑ፣ የተጠናቀቁ ቤቶችን የሚሸጡ የሪልስቴት አልሚዎች በዋናነት ተጎጂ መሆናቸውንም አንስተዋል።

ባሳለፈነው ወር ብሔራዊ ባንክ ማንኛውንም የማይንቀሳቀስ ንብረት በተለይ ደግሞ ቤትን አስይዞ የሚሰጥ ብድር መከልከሉ ይታወሳል። በንግድ ባንክ የሚከናወኑ የ20/80 እና 40/60 በብድር የሚገዙ ቤቶች ሽያጭ እየተከናወነ ነው።

አንድ ሪል ስቴት ለመግዛት የተወሰነ ክፍያ ከተከፈለ በኋላ ሙሉውን ክፍያ እንዲጨርስ ባንኮች ቤቱን በመያዝ ብድር ይሰጣሉ። ነገር ግን አሁን ብሔራዊ ባንክ ባወጣው መመሪያው የተጠቀሱት ተቋርጠዋል የተባሉት የብድር ዓይነቶች የቆሙ ንብረቶች ግዢና ሽያጭ ላይ ነው። በመሆኑም ሪልስቴቶችን አይመለከትም። እግዱ የሚመለከተው ተሠርተው አልቀው ባለቤት ያላቸው ግንባታዎችን ለሌሎች ባለንብረቶች ለማስተላለፍ የሚደረገው እንቅስቃሴ ላይ ነው የሚሉት የቀድሞው የቡና ባንክ ፕሬዝዳንት፣ የጎህ ባንክ መስራች እና የባንክ ባለሙያ የሆኑት እሸቱ ፋንታዬ ናቸው።

የካርታ ማዘዋወር ሥራ ከተቋረጠ ቆይቷል የሚሉት እሸቱ፣ ብሔራዊ ባንክ ያወጣው መመሪያ በቀጥታ ባንኮቹ ከብሔራዊ ባንክ በነበራቸው ግንኙነቶች ያሏቸውን ውሎች ሁሉ የሚመለከት ስለሆነ፣ ሥራንና የሪልስቴቶችን ሕልውና አደጋ ላይ እንደሚጥል አመላክተዋል።
ምክንያቱም ሪልስቴቶች ከገዢዎች ያገኙት የነበረውን ገንዘብ ባለማግኘታቸው አዳዲስ ፕሮጀክት ለመጀመር አይችሉም። ይህ ደግሞ ሪልስቴቶቹ በባንኮቹ በኩል የሚያደርጉትን የገንዘብ ዝውውር ያዳክመዋል። ይህ እግድ ሪልስቴቶችን ያካተተ ከሆነ ባንኮቹ ራሱ ብሔራዊ ባንክን መጠየቅ ይገባቸዋል ብለዋል።

የብሔራዊ ባንክ መመሪያ ትርጓሜ በሪልስቴት አልሚዎች እና በባንኮቹ ያለው የተሳሳተ ሆኖ እንጂ የቤት ባለቤት ለመሆን እየቆጠቡ ያሉ ግለሰቦች ሙሉ ለሙሉ ቤቱን አትወስዱም የሚል መመሪያ አይደለም። በብሔራዊ ባንክ የወጣው መመሪያ ቋሚ ንብረት በግዥና ሽያጭ ማስተላለፍ የውጭ ምንዛሬ ዋጋን አናግቷል በሚል የወጣ መመሪያ ሲሆን፣ ገበያውን ለማረጋጋት የተደረገ እግድ ነው።


ቅጽ 3 ቁጥር 152 መስከረም 22 2014
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!