የእለት ዜና

በመስቀል አደባባይ የመጀመሪያው የአውቶሞቲቭ ንግድ ትርዒት ሊዘጋጅ ነው

የትርዒቱ ተሳታፊዎች ለሚጠቀሙበት ቦታ በካሬ ሜትር አንድ ሺሕ ብር ይከፍላሉ ተብሏል

የአዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የመጀመሪያውን ግልጽ የሆነ የአውቶሞቲቭ ንግድ ትርዒት ሊያዘጋጅ መሆኑን የምክር ቤቱ ‹የሞተር ሾው ኤቨንት› ከፍተኛ የገበያ ባለሙያ መቅደስ መላኩ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
በንግድ ትርዒቱ ከ70 እስከ 100 የሚደርሱ የአገር ውስጥና የውጪ የአውቶሞቲቭ አምራቾች፣ አስመጭዎች፣ ወኪል የመኪና እና የመለዋወጫ አከፋፋዮች፣ የትራንስፖርት አገልግሎት አቅራቢዎች እና በአውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪው ውስጥ ቀጥታ ግንኙነት ያላቸው ድርጅቶች ይሳተፋሉ ተብሏል።

የንግድ ትርዒቱ የእርስ በርስ የንግድ እና ገበያ ትስስር ለመፍጠር፣ በዘርፉ የተሰማሩ ኩባንያዎችን ከደንበኞቻቸው ጋር ለማገናኘት እንዲሁም የአውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪ እና ቴክኖሎጂው የደረሰበትን ደረጃ ለማሳየት ያለመ መሆኑም መቅደስ ተናግረዋል።
የንግድ ምክር ቤቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚያከናውነው ይህ ትርዒት የውጭ አምራቾችን በስፋት ያማከለ ነው። በዚህም መሠረት ሱዳን፣ ቱርክ፣ ዱባይ እና ዩናይትድ አረብ ኤሚሬትስ በትርዒቱ እንደሚሳተፉ ያረጋገጡ አገራት ናቸው። ከእነዚህ በተጨማሪ ጥሪ የቀረበላቸው አገራት መኖራቸውን መቅደስ ጠቁመዋል።

ይህን የአደባባይ ትርዒት የሚያከናውነው ምክር ቤቱ በአምስቱ ቀናት በኤግዚብሽን ማዕከል ከሚያዘጋጀው የግብርና ቴክኖሎጂ እና የማኑፋከቸሪንግ ቴክኖሎጂ ጋር የተያያዘ መሆኑንም መቅደስ አስታውቀዋል። የግብርና ቴክኖሎጂ ንግድ ትርዒት ለ13ኛ ጊዜ የሚካሄድ ሲሆን፣ ለአራተኛ ጊዜ የሚካሄደው የማኑፋክቸሪንግ ንግድ ትርዒት ደግሞ በመደበኝነት እንዲቀጥል ሆነ የአውቶሞቲቭን ዘርፍ ለብቻው በማውጣት በመስቀል አደባባይ እንዲካሄ ታቅዶ ወደ ተግባር እንደገባ አስረድተዋል።
የአውቶሞቲቭ ዘርፉ ለብቻው እንዲካሄድ የተደረገው ድርጅቶቹ ምርቶቻቸውን ለማስተዋወቅ ነጻነት እንዲያገኙና በስፋት ይዘው እንዲቀርቡ በማሰብ መሆኑንም መቅደስ አክለው ገልጸዋል።

የንግድ ትርዒቱ መኪና ከሚያመርቱ ጀምሮ እስከ መኪና መለዋወጫና መሸጫ ያላቸው ድርጅቶች፣ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች፣ ጎማ አምራቾች እና በዘርፉ ያሉ ሁሉንም አካላት ያሳትፋል። ተሳታፊዎችም በዝግጅቱ ምርቶቻቸውን ለማቅረብ የሚይዙት የቦታ መጠን ትንሹ ዘጠኝ ካሬ ሜትር ነው።

ተሳታፊዎች በሚይዙት ቦታ ላይ ድንኳን በግላቸው የሚጠቀሙ ሲሆን፣ አንዳንድ ድርጅቶች ከ50 እስከ 100 ካሬ ሜትር ድረስ ይይዛሉ። በአንድ ካሬ አንድ ሺሕ ብር የሚከፍሉ መሆኑንም ነው መቅደስ ጠቅሰዋል። በአጠቃላይ አንድ ድርጅት ዘጠኝ ካሬ ሜትር የሚወስድ ከሆነ ለአምስት ቀናት መመዝገቢያውን ጨምሮ 46 ሺሕ 500 ብር ያወጣልም ሲሉ አክለዋል።

በዚህ መሠረት የተሳታፊዎች ቁጥር በትንሹ 70 ቢሆንና አንድ ድርጅት 46 ሺሕ 500 ብር ቢከፍል፤ የአዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት እስከ 3.2 ሚሊዮን ብር ድረስ መሰብሰብ ያስችለዋል።

በተጨማሪም በንግድ ትርዒቱ ላይ ተሳታፊ የሆኑ ድርጅቶች እንደ ፍላጎታቸው ኤል.ኢ.ዲ. ስክሪን በመጠቀም ማስታወቂያ መሳየት የሚችሉ ሲሆን፣ ለዚህም 330 ሺሕ ብር ተጨማሪ በመክፈል የ30 ደቂቃ ማስታወቂያ ለ10 ጊዜ የሚያስተላልፉበት አማራጭ ተዘጋጅቷል ተብሏል። በምክር ቤቱ የተዘጋጀው ይህ ትርዒት እንደ ተቋም የመጀመሪያ ስለሆነ ችግሮች ሊገጥሙ ይችላል ያሉት መቅደስ፣ ሆኖም ለዘርፉ ባለድርሻዎች መገናኛ የሚሆን ትልቅ ዕድልን የሚፈጥር ነው ብለዋል።

በቀደሙት ጊዜያት በሚሊኒየም አዳራሽ የአውቶሞቲቭ ንግድ ትርዒት ቢካሄድም፣ በምክር ቤቱ የተዘጋጀውና ከኅዳር 2 እስከ 6/2014 ለአምስት ቀናት የሚቆየው ይህ ትርዒት በመስቀል አደባባይ የሚካሄድ ግልጽ ትርዒት መሆኑ የመጀመሪያ አድርጎታል ሲሉ መቅደስ ጠቁመዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 152 መስከረም 22 2014
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!