የእለት ዜና

ኢቢሲ በ20 ሚሊዮን ብር 5 መኪና ለኃላፊዎቹ መግዛቱን አረጋገጠ

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ለመከላከያ ሠራዊት ድጋፍ ከሠራተኛ ደሞዝ የቆረጥኩት 15 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ ለተቋሙ ኃላፊዎች የገዛሁት 5 መኪና በ20 ሚሊዮን ብር ነው ሲል አስታወቀ።
የኮርፖሬሽኑ የሕግ ጉዳዮች ዲፓርትመንት ኃላፊ ሞላልኝ መለሰ ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቁት፣ በ12 ወራት ውስጥ የሚቆረጥ የአንድ ወር የተጣራ ደሞዝ በአጠቃላይ 15.4 ሚሊዮን ብር ለመከላከያ ሠራዊት እና በጦርነቱ ለተፈናቀሉ እንዲሰጥ ነሐሴ 20/2013 በሁሉም ደረጃ የሚገኙ ሠራተኞች ተስማምተው ተወስኗል ብለዋል።

የኮርፖሬሽኑ የቀድሞው ዋና ሥራ አስፈጻሚ በነበሩት ንጉሴ ምትኩ ገላው (ዶ/ር) አማካይነት የተፈረመ ደብዳቤ ለኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን በማስገባት አዲስ ማለዳ ተቋሙን በተመለከተ በሠራችው ዘገባ ላይ ማስተባበያ እንዲፃፍ ጠይቀዋል።
አዲስ ማለዳ በመስከረም 8/2014 ቁጥር 150 ላይ ያቀረበችው ዘገባ፣ ተቋሙ የ25 ሚሊዮን ብር ተሸከርካሪዎች እየገዛ በሌላ በኩል 40 ሚሊየን ብር ከዝቅተኛ ደሞዝ ተከፋይ ሠራተኞች መጠየቁን እና ማዋጣት የማይችል ከሥራ እንደሚሰናበት በማስፈራራት ያለሠራተኛው ፈቃድ ደሞዝ መቁረጡን ሠራተኞቹ ገለጹ በሚል የተሠራ ሲሆን፣ ተቋሙ ዘገባው የተሳሳተ ነው ሲል አስታውቋል። ዘገባው የመንግሥት እና የሕዝብ ተቋማት ሠራተኞቻቸውን በማስተባበር ለመከላከያ የሚያደርጉትን ድጋፍ ያደናቀፈ ነው ያለው ተቋሙ፣ አክሎም ህወሓት አገርን ለማፍረስ የያዘውን ዕቅድ የሚደግፍ እንቅስቃሴ ነው ሲል ዘገባውን ተችቷል።

የኮርፖሬሽኑ ቅሬታ አቅራቢዎች በበኩላቸው፣ ቅሬታችን የአንድ ወር ሙሉ ደሞዝ መቆረጡ ሲሆን ደሞዝ መቁረጡን ደግሞ ተቋሙ አምኗል ብለዋል።
የኮርፖሬሽኑ የፋይናንስ አስተዳደር ዲቪዥን ሥራ አስፈጻሚ ተፈራ ቶሌራ በበኩላቸው፣ ተቋሙ በወር ያልተጣራ 23 ሚሊዮን ብር እና ከነጥቅማ ጥቅሙ 32 ሚሊዮን ብር ለሠራተኞች ደሞዝ እንደሚከፈል ገልጸዋል። በተጨማሪም፣ በከተማ እና በክልሎች የሚገኙ የተቋሙ ሠራተኞች በአጠቃላይ 2100 መሆናቸው የጠቀሱት ተፈራ፣ ለኹሉም ሠራተኞች የተጣራ የአንድ ወር ደሞዝ 15 ሚሊየን ብር እንደሚከፍሉ ገልጸዋል።

ለመከላከያ ሠራዊት፣ እንዲሁም በጦርነቱ ለተፈናቀሉ የተደረገው ድጋፍ ከኮርፖሬሽኑ በጀት በተሰብሳቢ ሒሳብ ወጪ የተደረገ ሲሆን፣ ሠራተኞች ተቋሙን ለቀው የሚወጡ ከሆነ የሚጠበቅባቸውን ከፍለው እንደሚወጡ እና በሞት የሚለዩ ከሆነ ደግሞ ተቋሙ እንደሚሸፍን ተፈራ ገልጸዋል።

ኮርፖሬሽኑ ያለበትን የተሸከርካሪ ችግር ለመቅረፍ ሲባል በመጋቢት ወር 2013 ለአምስት የመንግስት ኃላፊዎች ቀረጥ እና ታክስ ጨምሮ ለእያንዳንዳቸው 3.9 ሚሊዮን ብር በአጠቃላይ 19 .9 ሚሊየን ብር ማውጣቱን ያስታወቁት ሞላልኝ፣ ለበላይ ኃላፊዎቹ ተሽከርካሪዎችን የገዛበት ዋጋ ሌሎች የመንግሥት ኃላፊዎች ከሚገዟቸው ተሽከርካሪዎች በዋጋ ከ70 በመቶ ያነሰ ነው ብለዋል። ይሁን እንጂ ግዢ ተፈጸመበት የተባለው ደረሰኝ የተቆረጠበት ቀን በዘንድሮው በጀት ዓመት ማለትም ሐምሌ 1/ 2014 መሆኑን ለአዲስ ማለዳ የተላከው ሠነድ ያሳያል።
ከዚህ በተጨማሪ ዘጠኝ የመስክ ተሽከርካሪዎች ግዢ ተፈጽሞ ጅቡቲ ወደብ ከደረሱ ኹለት ወር ማስቆጠራቸውንም ገልጸዋል።

ኮርፖሬሽኑ ለመከላከያ ሠራዊት ያደረገው ድጋፍ 10.8 ሚሊዮን ብር መሆኑን የጠቀሱት ሞላልኝ፣ በአማራ እና አፋር ክልል ለተፈናቀሉ ደግሞ 6.6 ሚሊዮን ብር ብቻ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል። እክለውም ከሠራተኞች የሚቆርጠው የአንድ ወር ደሞዝ ላይ ከተቋሙ ትርፍ 2 ሚሊዮን ተጨምሮ በድምሩ ድጋፍ የተደረገው 17.4 ሚሊዮን ብር መሆኑን ገልጸዋል።

የመከላከያ ሠራዊት እና የክልል ኃይሎች እየወሰዱት ያለውን የሕልውና ዘመቻ መደገፉን፣ እንዲሁም በጦርነቱ ምክንያት ከአማራና አፋር ክልሎች ለተፈናቀሉ ዜጎች ዕርዳታ ማድረጉን የገለጹት ሞላልኝ፣ ከሌላው የመንግሥት መሥሪያ ቤት ሠራተኞች ጋር ሲነጻጸር የተቋሙ ሠራተኞች የተሻለ የወር ገቢ ያላቸው መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ ፌደራላዊ መንግሥት የ2013 የፌደራል በጀት ዓመት የኮርፖሬሽኑ የካፒታል ወጪ 196 ሚሊዮን ብር የጸደቀለት ሲሆን፣ መደበኛ ወጪ ደግሞ 300 ሚሊዮን ብር ነበር። በ2013 በጀት ዓመት የመደበኛ ወጪ መሠረት ተቋሙ በአንድ ወር 25 ሚሊዮን ብር የመከፈል አቅም እንዳለው ያመለክታል።

በአዋጅ ቁጥር 858/2006 የተቋቋመው ኮርፖሬሽኑ ባለው የግዢ መመሪያ መሠረት በ2013 በጀት ዓመት በርካታ ዕቃዎች ለመግዛት ዕቅድ ነበረው።


ቅጽ 3 ቁጥር 153 መስከረም 29 2014
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!