የእለት ዜና

በአዲሱ የአስፈጻሚ አካላት ሥልጣንና ተግባር መወሰኛ ዐዋጅ 39 ሕጎች ተሽረዋል

40 የፌዴራል አስፈጻሚ ተቋማት ሥያሜያቸው ተቀይሯል

ባሳለፍነው መስከረም 26/2014 ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ የጸደቀው የአስፈጻሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር መወሰኛ ዐዋጅ ቁጥር 1263/2014፣ 39 ሕጎች እንዲሻሩ አድርጓል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባለፈው ሳምንት ባካሄደው 6ኛ ዙር 1ኛ ዓመት 1ኛ ልዩ ስብሠባ የአስፈጻሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን የቀረበውን ዐዋጅ በአንድ ድምጸ ተአቅቦ በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል። በአዲሱ ዐዋጅ መሠረት የመንግሥት ተቋማት እንደ አዲስ መዋቀራቸውን ተከትሎ ስድስት ዐዋጆች እና 33 ደንቦች ተሽረዋል። በመሆኑም ዐዋጁ ሥራ ላይ መዋሉን ተከትሎ ሕጎቹ ተፈጻሚነት አይኖራቸውም።

በአዲሱ ዐዋጅ የተሻሩት ዐዋጆች የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የፌዴራል አስፈጻሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን የወጣው ዐዋጅ ቁጥር 1097/2011፣ የነዳጅና የነዳጅ ውጤቶች አቅርቦትና ሥርጭት ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን ማቋቋሚያ ዐዋጅ ቁጥር 1145/2011፣ የጨረራ መከላከያ ዐዋጅ ቁጥር 571/200፣ የፌደራል የተቀናጀ መሠረተ ልማት ማስተባበሪያ ኤጀንሲ ማቋቋሚያ ዐዋጅ ቁጥር 587/2000 እና የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ ማቋቋሚያ ዐዋጅ ቁጥር 194/1992 መሆናቸው በዐዋጁ ላይ ተደንግጓል።

በአዲሱ ዐዋጅ ቁጥር 1263/2014 መሠረት ከተሻሩት 33 ደንቦች መካከል፣ የቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ማቋቋሚያ ደንብ ቁጥር 180/2002፣ የቴክኖሎጂ ኢንፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ሥልጣን፣ ተግባርና አደረጃጀት ለመወሰን የወጣ ደንብ ቁጥር 440/2011፣ የፌደራል ከተሞች ሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ማቋቋሚያ ደንብ ቁጥር 347/2008፣ የመስኖ ልማት ኮሚሽን ሥልጣን፣ ተግባርና አደረጃጀት ለመወሰን የወጣ ደንብ ቁጥር 444/2011፣ የኢትዮጵያ ኢነርጂ ባለሥልጣን ማቋቋሚ ድንብ ቁጥር 308/2006 እና የትምህርት ስትራቴጂ ማዕከል ማቋቋሚያ ደንብ ቁጥር 276/2005 ይገኙበታል።

እንዲሁም የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ ማቋቋሚያ ደንብ ቁጥር 261/2004፣ የስፖርት ኮሚሽን ሥልጣን፣ ተግባርና አደረጃጃት ለመወሰን የወጣ ደንብ ቁጥር 446/2011፣ የፌደራል ከተሞች መሬትና መሬት ነክ ንብረት ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ ማቋቋሚያ ደንብ ቁጥር 251/2003፣ የፌደራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ልማት ኤጀንሲ ማቋቋሚያ ደንብ ቁጥር 373/2008፣ የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ማቋቋሚያ ደንብ ቁጥር 180/2002፣ የኢትዮጵያ ሥጋና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ማቋቋሚያ ደንብ ቁጥር 295/2005 እና የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ተግባር፣ ኃላፊነትና አደረጃጀት ለመወሰን የወጣ ማቋቋሚያ ደንብ ቁጥር 435/2011 ይገኙበታል። በአጠቃላይ ከላይ የተጠቀሱትና ያልተጠቀሱትንም ደንቦች ጨምሮ 39 ሕጎች በአዲሱ ዐዋጅ ተሽረዋል።

በአዲሱ የአስፈጻሚ አካላት ሥልጣንና ተግባር መወሰኛ ዐዋጅ መሠረት ከተሻሩ ሕጎች በተጨማሪ 40 የፌደራል አስፈጻሚ ተቋማት የሥያሜ ለውጥ ተደርጎባቸዋል። የሥያሜ ለውጥ ከተደረገባቸው ተቋማት መካከል፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ ስያሜው የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር፣ የኢንፎርሜሽን መረብ ድኅንነት ኤጀንሲ ወደ የኢንፎርሜሽን መረብ ድኅንነት አስተዳደር፣ የፋይናንስ መረጃ ደኅንነት ማዕከል ወደ የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት፣ ብሔራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ወደ የአደጋ ሥራ አመራር ኮሚሽን እና የቡናና ሻይ ልማትና ግብይት ባለሥልጣን ወደ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን የሥያሜ ለውጥ ተደርጎባቸዋል።

ሌሎች ያልተጠቀሱ የፌደራል ተቋማት የሥያሜ ለውጥ የተደረገባቸው ሲሆን፣ ከዚህ በኋላ በአዲሱ ሥያሜያቸው የሚጠሩ ይሆናል። በአዲሱ ዐዋጅ የታጠፉ ተቋማትና የሥያሜ ለውጥ የተደረገው፣ መንግሥት ለስምንት ወራት የተቋማት አደረጃጃት ላይ ጥናት ማድረጉን ተከትሎ መሆኑ ተገልጿል።


ቅጽ 3 ቁጥር 153 መስከረም 29 2014
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!