የእለት ዜና

የሴት መብት ተከራካሪ ወንዶች

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

ጾታዊ መድሎን ለማስቀረትም ሆነ የሴቶችን መብት ለማስከበር በተለምዶ ሲከራከሩና ሲሟገቱ የምንሰማቸው ሴቶችን ነው። “ፌሚኒስት” በመባል የሚታወቁት እነዚህ የመብት ጠያቂዎች አብዛኞቹ እንስቶች ቢሆኑም፣ ጥቂት ወንዶችም ቢሆኑ እንቅስቃሴያቸውን ሲደግፉ ይሰማሉ። ዋና የእኩልነት ቀስቃሽም ሆነ የመብት አስከባሪ ሆነው የምንሰማቸው ሴቶች ናቸው ቢባልም፣ እንቅስቃሴውን የሚደግፉ ታዋቂ ወንዶችም አሉ።

እንደ ካናዳው መሪ ጀስቲን ቱሩዶ አይነት ለሴቶች መብት በመታገል የሚታወቁ ዝነኛም ሆኑ ባለሥልጣናት በርካታ ቢሆኑም፣ ያን ያህል ግን በሁሉም ሲመሰገኑበት አይሰማም። ስለ ሥርዓተ-ጾታ እኩልነት ማሳወቅም ሆነ መከራከር ያለበት የተበደለው ወገን ማለትም ሴት ብቻ ናት ብለው የሚያምኑ ብዙዎች ናቸው። ወንዶች ድጋፍ መስጠትና መስማማት እንጂ ዋና የመብት አቀንቃኝ ሊሆኑ እንደማይችሉ የሚናገሩ አሉ።

በሌላ በኩል፣ ሁሉም እንስቶች ለሴቶች መብት መታገል አለባቸው ብለው የሚምኑ ቢኖሩም፣ ጥቂት የማይባሉ ሴቶች ይባስ ብለው የሚሟገቱትን ሲተቹ ይሰማል። ሴት ስለሆንኩ ብቻ ጎጠኛ ሆኜ ሴቶች ያሉትንና የደገፉትን ፅንሰ ሐሳብ መደገፍ የለብኝም ብለው የሚናገሩት እነዚህ ሴቶች፣ እንዲህ ብለን ካሰብን አብዛኞቹ መብት ነፋጊ ናቸው የምንላቸውን ወንዶች በተቃራኒው በአንድ ጎራ ማሰለፍ ይሆናል ብለው ያስባሉ። የተቃራኒ አስተሳሰብ ደጋፊዎችን እየሸረሸሩ ወደ ራስ እንዲመጡ ማድረግ ነው እንጂ፣ ከራስ ወገን የነበረንም ወደሌላኛው ወገን ማድረጉ ዓላማን ከማክሸፉ በላይ ስምምነት እንዳይኖር ያደርጋል በማለት ያስረዳሉ።

ሰው በሰውነቱና በአስተሳሰቡ አይለይ እየተባለ፣ ሴቶች በጾታቸው ብቻ ተለይተው ጎራ እንዲፈጥሩ ማድረጉ ተገቢ እንዳልሆነ የሚናገሩት የሴት መብት ተከራካሪዎች፣ ወንዶችም በእኩል እንዲቀላቀሉዋቸው በስራቸው ጥሩ ስም ያተረፉ ታዋቂ ወንዶችን እንደምሳሌ በማንሳት ለመቀስቀሻነት ይጠቀሙበታል።

የወንድ ተሟጋቾችን በይበልጥ ማሳተፉ የበለጠ ጥቅም አለው የሚሉት እነዚህ ሴቶች፣ ከብዙ ዓመታት ልፋት በኋላ ወንዶች ሲሳተፉበት የመጣን ለውጥ በማስረጃነት ያቀርባሉ። ዓለም በወንዶች ቁጥጥር ስር መሆኗ ስላላበቃ ያለወንዶች ይሁንታ ሴቶች ብቻቸውን ማስገደድ እንደማይችሉ የሚናገሩት እነኚህ ሴቶች፣ ወንድ ብቻውን ውጤታማ ሆኖ መኖር እንደማይቻለው ሁሉ ሴቶችም ለውጥ ማምጣት ከፈለጉ ሁሉንም ማሳተፍ አለባቸው ይላሉ።

በአንፃሩ፣ የሴት መብት እየተባለ የሚደነገጉ ሕጎችን ጭምር በማንሳት የወንድ መብት እየተጣሰ ነው ብለው የሚከራከሩም አሉ። ለአብነት ያህል፣ ጥንዶች ግንኙነት ፈጽመው ልጅ ቢረገዝ ወንዱ ጽንሱ አድጎ ይወለድ አይወለድ ብሎ እንደሴቷ ብቻውን የመወሰን መብት ባይኖረውም፣ አይወለድ ብሎ የነበረው ሕፃንን በእናት ፍላጎት ብቻ ሲወለድ ቀለብ ከመቁረጥና ከማሳደግ ራሱን ነጻ ማድረግ አይቻለውም ብለው የሚከራከሩ አሉ።

መብት ከሆነ ዘር ጾታና ኃይማኖት የመድሎ መንስዔዎች መሆን ስለሌለባቸው ለሁሉም ሚዛኑ እኩል መሆን አለበት። ፍትሕ ማለት ግን በተፈጥሮ ተበላልጠውም ሆነ ተለያይተው የተፈጠሩትን አመጣጥኖ ሚዛናዊ ባይሆንም እኩል የሚያደርጋቸውን፣ የተበላለጠም ቢሆን የሚያቀራርባቸውን ዕድል መስጠት እንደሆነ የሚያምኑ አሉ።
አለቃ ዮሐንስ


ቅጽ 3 ቁጥር 153 መስከረም 29 2014
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com