የእለት ዜና

የኹለተኛው ዙር ምርጫ ትዝብት

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ ለማካሄድ በያዘው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት አጠቃላይ ምርጫውን በአንድ ዙር ማካሄድ ባለመቻሉ የመጀመሪያውን ዙር ምርጫ ሰኔ 14/2014 ካካሄደ በኋላ ኹለተኛውን ዙር ምርጫ ባሳለፍነው መስከረም 20/2014 አካሂዷል። ቦርዱ ምርጫውን በአንድ ዙር ማካሄድ ያልቻለው በጸጥታ ችግር፣ በሕግ የተያዙ ጉዳዮች ዕልባት ባለማግኘታቸው እና የድምፅመስጫ ወረቀት ኅትመት ችግር በማጋጠሙ መሆኑ የሚታወስ ነው።

ኹለተኛው ዙር ምርጫ የተካሄደው በሱማሌ እና ሐረሪ ክልል ሙሉ በሙሉ ሲሆን፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል ደግሞ የደቡብ ምዕራብ ሕዝበ ውሳኔና በመጀመሪያው ዙር ምርጫ ባልተካሄደባቸው አከባቢዎች ነው። ይሁን እንጂ፣ በኹለተኛው ዙር ምርጫ ይካተታሉ ተብለው የነበሩ የቤኒሻንጉል ጉምዝ፣ የአማራ እና የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች በኹለተኛው ዙር ምርጫ አልተካተቱም።

ምርጫ ቦርድ ኹለተኛውን ዙር ምርጫ መስከረም 20/214 ሲያካሂድ፣ 11 ተቋማት ምርጫውን እንደታዘቡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኮሚዩኒኬሽን አማካሪ ገልጸዋል። ምርጫውን ከታዘቡት አገር በቀል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች መካከል የኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ኅብረት ለምርጫ እና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ(ኢሰመጉ) ይገኙበታል።

የኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ኅብረት ለምርጫ፣ በኹለተኛው ዙር ምርጫ ላይ በተሰማራባቸው ምርጫ ጣቢያዎች ላይ የታዘበውን የምርጫ ሒደት የመጀመሪያ ዙር ሪፖርት ይፋ አድርጓል።
የኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ኅብረት ለምርጫ በአገሪቱ የሚከናወኑ ምርጫዎች ነፃ እና ገለልተኛ እንዲሁም እንደ አካታችነት፣ ግልፅነት እና ተጠያቂነት የመሳሰሉትን ዓለም አቀፍ መርሆዎችን መሠረት አድርገው መከናወናቸውን መታዘብ አንዱ ዓላማው አድርጐ የተቋቋመ ድርጅት ነው።

ኅብረቱ ሰኔ 14/2013 የተደረገውን አገራዊ እና ክልላዊ ምርጫ 2050 ተቀማጭ፣ እንዲሁም ከ100 በላይ ተንቀሳቃሽ ታዛቢዎችን በማሰማራት መታዘቡ የሚታወስ ሲሆን፣ መስከረም 20/2014 በሐረሪ እና ሶማሌ ክልሎች የተደረጉ ምርጫዎች፣ እንዲሁም በደቡብ ክልል ውስጥ በሚገኙ አንዳንድ ሥፍራዎች የተደረገውን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የክልል ምክር ቤት ምርጫዎች፣ እንዲሁም በዚሁ ክልል የተደረገውን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝበ ውሳኔ ታዝቧል።

በተጨማሪም፣ ለሐረሪ ብሔራዊ ጉባኤ መቀመጫዎች በአዲስ አበባ እና በድሬዳዋ ከተማ በተመሠረቱ የምርጫ ጣቢያዎች እንዲሁም በሱማሌ ክልል፣ ፋፈን ዞን ደንዳማ ወረዳ በሚገኘው የቆሎጂ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ የተደረገውን የድምፅአሰጣጥ ሒደት መታዘቡን ገልጿል።

ኅብረቱ በታዛቢነት በተሰማራባቸው ምርጫ ጣቢያዎች፣ 956 ቋሚ እንዲሁም 37 ተንቀሳቃሽ ታዛቢዎችን ማሳተፉን የገለጸ ሲሆን፣ የመጀመሪያ ዙር ሪፖርቱም ይህንኑ መሠረት ያደረገ ነው ተብሏል። ኅብረቱ በመደበኛ የድምፅመስጫ ጣቢያዎች ካሰማራቸው ከ37 ተንቀሳቃሽ ታዛቢዎች መካከል ሰባቱን በልዩ ሁኔታ በማዘጋጀት በሱማሌ ፋፈን ዞን ደንዳማ ወረዳ ውስጥ በሚገኘው ቆሎጂ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ ውስጥ አሰማርቶ የምርጫ ሒደቱን ታዝቧል። ይህ የምርጫ ትዝብት ሪፖርት ከኅብረቱ ታዛቢዎች በተሰበሰቡ 944 የምርጫ ቀን ሪፖርቶች እና 26 የአሳሳቢ ኹነት ሪፖርቶች ላይ የተመሰረተ ነው። ኅብረቱ ትኩረቱን በድምጽ መስጫ ጣቢያዎች አከፋፈት እና አደረጃጀት፣ እንዲሁም የድምፅአሰጣጥ እና ቆጠራ ሒደት ላይ አድርጌ የምርጫ ትዝብቱን አከናውኛለሁ ብሏል።

የኅብረቱ ታዛቢዎች በድምጽ አሰጣጥ ወይም ቆጠራ ወቅት ያጋጠሙ እንዲሁም የምርጫውን ተዓማኒነት ጥያቄ ውስጥ የሚጥሉ ወይም የመራጮችን፣ የምርጫ አስፈጻሚዎችን፣ የዕጩዎችን ወይም ሌሎች ከምርጫው ጋር ግንኙነት ያላቸውን አካላት ደህንነት አደጋ ላይ ሊጥሉ የሚችሉ “አሳሳቢ ኹነቶችን” መኖራቸውን ጠቁሟል።

የድምፅአሰጣጥ ሒደቱን ከጠዋቱ 12 ሰዓት ለመጀመር እንዲያስችል፣ የምርጫ አስፈፃሚዎች ቀድመው በድምጽ መስጫ ጣቢያዎች መገኘት ያለባቸው ሲሆን፣ በተመደቡበት የድምፅ መስጫ ጣቢያ ከማለዳው 11 ሰዓት ጀምሮ በመድረስ ሪፖርቶቻቸውን ከላኩ የኅብረቱ 944 ታዛቢዎች መካከል 97 በመቶዎቹ የምርጫ አስፈፃሚዎች በድምጽ መስጫ ጣቢያዎች ቀድመው መገኘታቸውን ታዛቢዎቹ አረጋግጠዋል ተብሏል።

98 በመቶ የኅብረቱ ታዛቢዎች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሰጠውን የታዛቢነትን ማረጋገጫ ባጆችን በማሳየት ወደ ምርጫ ጣቢያ በመግባት እንዲታዘቡ የተፈቀደላቸው ቢሆንም፣ በአንዳንድ የምርጫ አስፈፃሚዎች ዘንድ በሚታየው የመረጃ ክፍተት ጥቂት ታዛቢዎቻች ወደ ድምጽ መስጫ ጣቢያ እንዳይገቡ እንቅፋት መፍጠሩን ኅብረቱ ገልጿል። በዚህም በደቡብ ክልል ዳውሮ ልዩ ዞን፣ በሐረሪ ክልል በባቢሌ፣ በአዲስ አበባ የሐረሪ ብሔራዊ ጉባኤ የድምፅመስጫ ጣቢያ የተመደቡ የተወሰኑ የኅብረቱ ታዛቢዎች በምርጫ አስፈፃሚዎች እንዳይታዘቡ መከልከላቸው ተጠቁሟል።

መራጮች በቀላሉ ድምጻቸውን ለመስጠት እንዲችሉ የድምፅመስጫ ጣቢያዎች ለሁሉም በቀላሉ ተደራሽ በሆኑ አካባቢዎች ሊቋቋሙ እንደሚገባቸው የጠቆመው ኅብረቱ፣ በታዛቢዎቹ ሪፖርት መሰረት 96 በመቶ የድምፅመስጫ ጣቢያዎች ለአካል ጉዳተኞች እና የመንቀሳቀስ ችግር ላለባቸው መራጮች (በዕድሜ ለገፉ፣ ለነፍሰ-ጡሮች እና ሕፃናትን ለያዙ) ምቹ በሆኑ ቦታዎች ላይ ተቋቁመዋል ብሏል። በተመሳሳይ 97 በመቶ የድምፅመስጫ ጣቢያዎች ለሴቶችም ሆነ ለወንዶች በእኩል መጠን ተደራሽ መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን፣ ይህ ግኝት በድምጽ መስጫ ጣቢያዎች ተደራሽነት ረገድ በሰኔ ወር ከተካሄደው ምርጫ ከነበረው የ87 በመቶ ግኝት አንፃር የተሻለ ነው ተብሏል።

መስከረም 20/2014 የተካሄደው ኹለተኛው ዙር ምርጫ በሰኔ 14/2013 ከተካሄደው የድምፅመስጠት ሒደት አንፃር የተሻሻሉ አሠራሮች መኖራቸውን ገልጿል። ከተሻሻሉት አሠራሮች መካከል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫውን ለማካሄድ ያደረገው ቅድመ-ዝግጅት፣ በተለይም በቂ የድምፅመስጫ ቁሳቁስ አቅርቦትን ከሟሟላት አንፃር፣ እንዲሁም ለምርጫ ታዛቢዎች ቀደም ብሎ የታዛቢነት ባጅ መስጠት መቻሉ፣ የአገር-ውስጥ ተፈናቃዬች በድምጽ መስጠት ሒደቱ ውስጥ እንዲሳተፉ በማድረግ የፖለቲካ ተሳትፎ መብታቸውን በተለይም የመምረጥ መብታቸውን እንዲጠቀሙ ለማስቻል መሞከሩ፣ ምርጫ በተካሄደባቸው በአብዛኛው አካባቢዎች ምርጫው በተያዘለት ሰዓት ተጀምሮ መጠናቀቁ፣ ተጨማሪ የድምፅመስጫ ሰዓት ባስፈለገባቸው የሐረሪ ክልል ምርጫ እና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የክልልነት ሕዝበ ውሳኔ ተጨማሪ ኹለት ሰዓታት በመስጠት ዜጐችን የመምረጥ መብቶቻቸውን እንዲጠቀሙ መደረጉ፣ የኅብረቱ ታዛቢዎች የምርጫ ትዝብታቸውን በሚያከናውኑበት ወቅት ያጋጥሟቸው እና ለቦርዱ በወቅቱ የቀረቡ ችግሮችን በፍጥነት በመፍታት ከኅብረቱ ጋር በትብብር መንፈስ መሥራት መቻሉ፣ በዋነኛነት የሚጠቀሱ መሆናቸውን ገልጿል።

መሻሻል የታየባቸው በጎ ጎኖች የሚበረታቱ መሆናቸውን የገለጸው ኅብረቱ፣ በአንፃሩ ቦርዱ ትኩረት ሊያደርግባቸው የሚገቡ ክፍተቶችም መታየታቸውን በሪፖርቱ ጠቅሷል። ከታዩ ችግሮች መካከል ኅብረቱ በታዘበባቸው አንዳንድ የድምፅ መስጫ ጣቢያዎች ላይ የምርጫ አስፈፃሚዎች አቅም ማነስ በመታየቱ፣ ታዛቢዎችን መከልከል፣ እንዲሁም በምርጫ ማስፈጸሙ ሥራ ላይም በኹለት አጋጣሚዎች የኅብረቱ ታዛቢዎች ሙያዊ ትብብር እንዲያደርጉ መጠየቃቸው፣ ኅብረቱ በታዘባቸው አንዳንድ የድምፅ መስጫ ጣቢያዎች ላይ የምርጫ አስፈፃሚዎች በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ፍቃድ የተሰጣቸው ኅብረቱ ያሰማራቸውን ታዛቢዎች መከልከላቸው፣ ብሎም እስከማሰር የደረሱባቸው አጋጣሚዎች መኖራቸው፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በወላይታ ዞን፣ በሶዶ ከተማ አንድ የመራጮች መዝገብ የጠፋ ሲሆን፣ እንዲሁም በዚሁ ክልል አንዳንድ መራጮች በተደጋጋሚ ድምፅ ሲሰጡ ታይተዋል ብሏል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ተጨማሪ ምርመራ እንዲያደርግ ኅብረቱ ጠይቋል።

በጅግጅጋ ከተማ ከተሰማራ አንድ ታዛቢ ለኅብረቱ በደረሰው መረጃ መሠረት በአንድ የድምፅ መስጫ ጣቢያ ውስጥ አንዲት ግለሰብ አግባብ ባልሆነ መልኩ በሚስጥር የድምፅ ምልክት ማድረጊያ ክፍል ውስጥ ቀኑን ሙሉ የነበረች ሲሆን፣ የድምፅ መስጫ ሳጥኑም ለመራጮች፣ ለታዛቢዎች እና ለምርጫ-አስፈፃሚዎች በግልጽ በሚታይ ቦታ አለመቀመጡ ተስተውሏል። ምንም እንኳን ኅብረቱ ለምርጫ ትዝብት ባደረገው ቅድመ-ዝግጅት ወቅት ከቦርዱ ከፍተኛ የሥራ ትብብር የተደረገለት ቢሆንም፣ በአንዳንድ አጋጣሚዎች (ለምሳሌ፡ ኅብረቱ የአገር-ውስጥ ተፈናቃዮች ምርጫ የሚደረግባቸውን መጠለያዎች የሚገኙበትን ስፍራ እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች) ግን አስፈላጊ መረጃዎችን ለማግኘት አልቻልኩም ብሏል።

ኅብረቱ በተፈናቃዮች መጠለያ ባደረገው ትዝብት በመጠለያው ውስጥ የሚገኙ መራጮች ድምፃቸውን ለመስጠት ገደብ የሚያደርጉ የአቅም ውስንነቶችን መታዘቡን የገለጸ ሲሆን፣ በመሆኑም እነዚህን ክፍተቶች ለመሙላት የመራጮችን አቅም ለማጎልበት ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት በጋራ እንዲሠሩ አሳስቧል። ከላይ ከተጠቀሱ ቦርዱ ሊያሻሽላቸው ከሚገቡ ጉዳዬች በተጨማሪ ኅብረቱ በድምፅ መስጫ ጣቢያዎች የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዬች ብዛት ዝቅተኛ መሆኑን ተመልክቻለሁ ብሏል። በዚህም የፓለቲካ ፓርቲዎች በመስከረም 20/2014 በተካሄደው ኹለተኛ ዙር ምርጫ ያደረጉት ተሳትፎ አነስተኛ መሆኑን መገንዘቡን ኅብረቱ በሪፖርቱ ጠቅሷል።


ቅጽ 3 ቁጥር 153 መስከረም 29 2014
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com