የእለት ዜና

ከሞት ያመለጡ ተፈናቃዮች

ዓመት ሊሞላው የተወሰኑ ቀናት የቀሩት በሰሜኑ የአገሪቱ አካባቢ የተነሳው ጦርነት እስካሁን የበርካቶችን ሕይወት አሳጥቷል። የሞት ጥላ አንዣቦባቸው የኖሩበትን ቀዬ ጥለው የተሰደዱና ተፈናቃይ ተብለው በየመጠለያ ጣቢያውና በየዘመድ አዝማዱ፣ እንዲሁም በየዱሩ ኬንዳ ወይም ሸራ ወጥረው ለመኖር የተገደዱ በጣም በርካታ ዜጎች አሉ።

ጦርነቱ ከአስከተለው ሰብዓዊ ጉዳት በተጨማሪ በርካታ የአገርና የሕዝብ ሀብት በመውደሙም እንደአገር ወደ ነበርንበት አቋም ለመመለስ ረጅም ጊዜ እንደሚወስድ ይታወቃል። በጦርነቱ የተሰዉ ቤተሰቦችን ለማቋቋም ከሚደረገው ጥረት በላይ፣ በየቦታው ተፈናቅለው የሚገኙ እንዳይርባቸውና እንዳይታረዙ፣ በበሽታም እንዳይልቁ የተቻለው እየተደረገ ቢሆንም፣ ከአሳሳቢነት አንፃር እንዲሁም መንስዔው ዘላቂ መፍትሔ ስላልተበጀለት ችግሩ እንደሚቀጥል ይነገራል። ችግሩ በአጭር ጊዜ የማይቀረፍ ከሆነና መልሶ በዘላቂነት ማቋቋም ካልተቻለ የተረጂው ቁጥር እያደር እንደሚጨምር የሚናገሩ አሉ።

ለዕለት ጉርስ የሚሆናቸውን ዕርዳታ በርብርብ እያገኙ ቢሆንም፣ ችግሩ እስኪቀረፍ ድጋፉ በቋሚነትና በተመሳሳይ መጠን የሚዘልቅ ባለመሆኑ ትኩረት ሊደረግበት እንደሚገባ የሚናገሩ ብዙዎች ናቸው። ከቄየውና ሥራው ተፈናቅሎ የነበረ ሕዝብን ወደቦታው መመለስ ቢቻል እንኳን፣ ራሱን ችሎ ወደነበረበት የኑሮ ደረጃ ለመመለስ ጊዜና ሀብት እንደሚፈልግ ይታወቃል። በተለይ በግብርና ከሚተዳደሩ የተወሰኑት እህል ዘርተው ቡቃያው ቢደርስላቸውም፣ ስላልታረመ ምርቱ አነስተኛ መሆኑ አይቀሬ ነው። ያልታረሱ ጦም ያደሩ መሬቶች በስፋት የመኖራቸውን ያህልም፣ ትርፍ አምራችና ለሌላው ይበቁ የነበሩ አካባቢዎች በቀጣይ ዓመት ድጋፍ ፈላጊ ይሆናሉ። ጦርነቱን ሸሽተው ያልተፈናቀሉ በእርሻ ሥራቸው ላይ ቢገኙም፣ የምርታቸውን እኩሌታ እንዲሰጡ የሚገደዱ እንዲሁም ሙሉ በሙሉ የሚዘረፍባቸው እንዳሉም እየተነገረ ይገኛል።

ጦርነቱ ከበረታባቸው ከሰሜን ወሎ ግዛቶች በርካታ ተፈናቃዮችን ያስተናገዱ የደቡብ ወሎ ከተማ የሆኑት ደሴና ኮምቦልቻ በርካታ ቁጥር ያለው ሕዝብ ከመቀበላቸው ባሻገር በከተሞቹ ከፍተኛ የሆነ የኑሮ ውድነት እየተስተዋለ ይገኛል።
አዲስ ማለዳ በከተሞቹ ባደረገችው ቅኝት ተፈናቃዮች ይዘዋቸው በመጡ ባጃጅን በመሳሰሉ ተሸከርካሪዎች ከተሞቹ ተጣበዋል። በአዘቦት ጭር ይሉ የነበሩ ጎዳናዎች በሥራ አጦች ተጥለቅልቀዋል። በየመንገድ ዳር የሚቀመጡ ወጣቶችም ብዙ ናቸው። የከተማው ሕዝብ ለይቶ የሚያውቃቸው ቢሆንም፣ መጀመሪያ ሲመጡ ከነበረው ሁኔታ እያደር እየተለወጠ ይገኛል። ጥሪት ኖሯቸው ተከራይተው የሚኖሩ፣ እየከፈሉ የሚበሉና የሚዝናኑ ጭምር ቀደም ባሉት ቀናቶች በርካቶች ነበሩ። አሁን አሁን ገንዘባቸውን እየጨረሱ በመምጣታቸው አብዛኞቹ የዕርዳታ ሰጪዎችን ፊት ለማየት ተገደዋል።

በደሴ ከተማ በሚገኘው ዳውዶ ትምህርት ቤት አዲስ ማለዳ ተገኝታ እንደተመለከተችው ምግብ ከሚሰጥበት ሰዓት ውጭ ግቢው ውስጥ በአብዛኛው የሚገኙት ሕፃናትና ወላጅ እናቶች ናቸው። ታመው ወይም አልፎ አልፎ ከሚታዩ አዲስ መጪዎች በስተቀር ወጣቱ ግቢው ውስጥ አይውልም።

በቦታው ተገኝተን ካነጋገርናቸው መካከል ከሀብሩ የተፈናቀለች ስሟን መናገር ያልፈለገች ወጣት እንደነገረችን፣ ለወላጆችና ለሕፃናት ቅድሚያ እየተባለ እነሱ እንደሚዘነጉ አንስታለች። ደሴ ከገባች 22 ቀናት ቢሆናትም ከለበሰችው ውጭ መቀየሪያ ልብስ አላገኘችም። የኪስ ገንዘብ ምንም እንዳልደረሳት የምትናገረው ይህች ተፈናቃይ፣ የደሴ ሕዝብና ባለሀብቶች እስካሁን ላደረጉት ዕገዛ ሊመሰገኑ ይገባል ትላለች። የኪስ ተብሎ የሚሰጥ በግል ባለሀብቶችም ሆነ በእርዳታ ድርጅቶች የሚከፋፈል ገንዘብ ወጣትና ቤተሰብ የሌላት በመሆኗ እየደረሳት እንዳልሆነ ነው ቅሬታዋን የምትናገረው።

ሌላ እዛው መጠለያ ጣቢያ ያገኘናቸው ተፈናቃይ፣ ምግብ በቀን ሦስት ጊዜ የነበረው ተቀንሶ ቁርስና ምሳ ብቻ ሆኖ እራት በመቅረቱ ከውጭ ለመብላት መገደዳቸውን ይናገራሉ። ምንም አይነት ገንዘብ ስለሌላቸው ከመጠለያው ተነሱ ቢባሉ መሄጃ እንደሌላቸው ያስረዳሉ። እስካሁን የሚደረገው ድጋፍ በቂ እንደነበረ የሚያወሱት እኚህ ተፈናቃይ፣ ሕዝቡ እንዳይሰላችና ድጋፉ እንዳይቀንስ ሥጋት እንዳላቸው አሳውቀውናል።

በዛው መጠለያ ጣቢያ ያገኘናቸው አዳነች ሲሳይ የተባሉ የ3 ልጆች እናት እንደነገሩን፣ ቦታውን ተማሪዎች ከዛሬ ነገ ይገቡበታል እየተባለ ጭንቅ ላይ እንደሆኑ ነው። አንድ ቀን መጥተው ውጡ ቢሏቸው መድረሻም ሆነ ወደመጡበት መመለሻ ምንም እንደሌላቸው ይናገራሉ። በእንዲህ አይነት ሆኔታ መቆየት ተገቢ ስላልሆነ በቶሎ ወደቀያቸው የሚመለሱበትን መንገድ መንግሥት እንዲያመቻች ጠይቀዋል። ወደአገራችን የመግባት ጉጉቱ ችግር ላይ ጥሎናል የሚሉት እኚህ እናት፣ በአጭር ጊዜ እንመለሳለን የሚል ተስፋ እንደነበራቸው ያስታውሳሉ።

ተሾመ ኃይሉ የተባሉ ከመርሳ የተፈናቀሉ አባት ደግሞ እንዳያሰቃዩኝ ፈርቼ ተሰደድኩኝ ይላሉ። ገና መጠለያው ከገቡ አንድ ቀናቸው ሲሆን፣ ስለነበሩበት ሁኔታ በሀዘኔታ ይናገራሉ። ሕዝቡ የሚያስፈጭበት አጥቶ በረሃብ እየተቆላ ነው የሚሉት እኚህ ተፈናቃይ፣ ነዋሪው በአገሩ ከገዛ ቤቱ እንዳይወጣ እየታዘዘ በስቃይ ላይ መሆኑን ጠቁመዋል። ቤተሰቤ ተበታትኖ ይገኛል ያሉን ሲሆን፣ በየመጠለያ ጣቢያው ካሉ ብዬ ፍለጋ ልጀምር ነው ብለውናል።

ሌላው ያነጋገርናቸው ከቆቦ አራት ልጆቻቸውን ይዘውና አራስ ሚስታቸውን ትተው የተፈናቀሉን ነው። የብልጽግና አባል መሆኔ ስለሚታወቅ ፈርቼ ተሰደድኩ የሚሉት አባት፣ 22 ሆነው ደሴ ከገቡ 3 ቀናት ቢሆናቸውም ምንም አይነት አመራር መጥቶ እንዳላያቸው ይናገራሉ። ለቀናት የሚነጠፍ ፍራሽና ብርድልብስ ሳያገኙ እንደቆዩ ሌሎች ተፈናቃዮች የሚመሰክሩላቸው እኚህ አባት፣ የቀጥታው መንገድ ስለተዘጋባቸውና ብራቸውን በመጨረሳቸው እየለመኑ በባህር ዳር ዞረው ዓባይ በረሀን አቋርጠው ከኹለት ወር በላይ ተጉዘው ደሴ ለመግባት የተገደዱ ናቸው። የቀሩትን ቤተሰቦቻቸውን ሁኔታ አለማወቃቸው ጭንቀት ውስጥ እንደከተታቸው የሚናገሩት እኚህ ተፈናቃይ፣ ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ደሴ ቢገቡም የጠበቁትን ድጋፍ ማግኘት አልቻሉም። አዲስ ገቢ እንደመሆናቸው ስላልተመዘገቡ ሌላው የሚያገኘውን ለመቀበል አልቻሉም። በቆርቆሮ በተሠራ አነስተኛ ክፍል ውስጥ የሚነጠፍ ሳይኖራቸው ከአንድ በሕመም ምክንያት ሙሉ ቀን ተኝቶ ከሚውል ሰው ጋር ሆነው እሳቸው ከልጆቻቸውና ሌሎች እንደእሳቸው በቅርብ ከገቡ ሰዎች ጋር ለመኖር ተገደዋል።

በደሴም ይሁን በኮምቦልቻ የምግብ አቅርቦቱ ጥሩ እንደሆነ አብዛኞቹ የሚናገሩ ሲሆን፣ ከመኪና ያልወረደ ጭምር እንደተጫነ በመንገድ ዳር ተደርድሮ ያታያል። ይህ ቢሆንም ግን ልገሳው የወረት እንዳይሆንና እንዳይቋረጥ፣ “በቂ አላቸው” ተብሎም እንዳይቀዛቀዝ የብዙዎች ስጋት ነው። ክምችቱ ለምን ያህል ጊዜ እንደሚበቃ ባይታወቅም፣ ካለው ተፈናቃይ ቁጥር አንፃር ብዙ እንደማይቆይ የሚገምቱ በርካቶች ናቸው።

አብዛኛው ረጂ ለአየር ትራንስፖርት ቅርብ ለሆኑት፣ ከተማ ላሉና በቀላሉ ሊደረስባቸው ወደሚችሉ መጠለያ ጣቢያዎች በማምራት ልገሳውን ስለሚያከማች፣ ከከተማ ርቀው ያሉ እንዲሁም በየዱርና ጢሻው ውስጥ ተደብቀው የተጠለሉት በበቂ ሁኔታ ዕርዳታ እያገኙ እንዳልሆነ ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉና የሚያስተባብሩ የማኅበረሰብ አንቂዎች ይናገራሉ። በተለይ ድሃ የሆነውና ከከተማ ያልተፈናቀለው ሕዝብ በቅርብ ወዳለ ዱር እየገባ ወደገጠር ቀበሌዎችም እያመራ ለመቆየት ተገዷል። ተቀባዩ ማኅበረሰብ እስከቻለ እየተንከባከበ ቢያቆይም ከጊዜው መርዘም አኳያ ሁሉም ለችግር ተዳርጓል።

ከከተማ ርቀው የተጠለሉት አሉበት ከተባሉ አካባቢዎች መካካል በመገኘት አዲስ ማለዳ በአፋሯ ጭፍራ ከተማ አድርጋ ከሐራ ወደ ሚሌ በሚወስደው መንገድ የሚገኙ ተፈናቃዮችን ተመልክታለች። ከድሬ ሮቃ ከተማ አቅራቢያ በሚገኝ ጃራ በተባለ አካባቢ ዱር ውስጥ የጨርቅ ዳስ እየሰሩ ወይም ዛፍ ስር የተጠለሉ በርካታ ተፈናቃዮች ይታያሉ። ከተማ ከሚታዩ ተፈናቃዮች የሚለዩና ከፍተኛ ችግር እንዳለባቸው በግልጽ የሚታይ ሕፃናትና ወጣቶች የሚበዙበት ስብስብ ነው።

ከነዚህ ተፈናቃዮች መካካል ቤተቦቻቸውን በየመንደሩና በየጫካው ጥለው ሁኔታውን ሊያጣሩ የመጡ በርካቶች ናቸው። ዕርዳታ መምጣቱን ካወቁ ተመልሰው ቤተሰቦቻቸውን ከያሉበት ሰብስበው የመከራ ጊዜያቸውን ሊያሳጥሩ የጓጉ ናቸው።
ሶዶማ የተባለው ይህ አካባቢ የጦር ግንባር እንደመሆኑ በርካታ ጦር በማንነግራችሁ አካባቢ በመስፈሩ ለተፈናቀሉት ወታደሮቹ ከስንቃቸው ላይ እየቀነሱ ኮሾሮ የመሳሰሉ ድጋፎችን ያደርጉ ነበር። ከመከላከያ ቀደም ብሎም በአካባቢው የሚኖሩ ማኅበረሰቦች ተፈናቃዮቹን እየመገቡ ከአቅማቸው በላይ እስኪሆንባቸው ድረስ አቆይተዋል።

ተደጋጋሚ የወረራ ጥቃት ተፈጽሞባቸው በከፍተኛ ገድል ሚሌ እንዳትያዝ እንዳደረጉ የሚነገርላቸው እነዚህ የሕብረተሰብ ክፍሎች፣ ለድል ላበቋቸው ለጦር መሪያቸው የጀነራልነት ማዕረግ ሰጥተዋል። “ባለሽርጡ ጀነራል” በመባል የሚታወቁት ሀሠን ከረሙ ማኅበረሰባቸውን ከማስተዳደር በተጨማሪ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተፈናቃይን በማስተናገድ የራሳቸውንም ሆነ የማኅበረሰባቸውን አቅም እስኪፈታተን ማቆየታቸው ለዝናቸው ሌላው ምክንያት ሆኗል።

ጃራ በሚገኘውና መጠለያ ለማለት በሚያስቸግረው የተፈናቃዮቹ ማረፊያ፣ በዕርዳታ አስተባባሪዎች አማካይነት የተተከለ አንድ ድንኳን ቢኖርም ገና ሰው አልገባበትም ነበር። አዲስ ማለዳ በተገኘችበት ወቅት ገና የተፋናቃዮች ስም መመዝገብ እየተጀመረ ነበር። በበነጋታው የነፍሰጡሮች ስም ዝርዝር፣ የወላድ እመጫቶችና ብዙ ሕፃናት ያሏቸው ተፈናቃዮች መለየታቸውን ራሳቸው ተፈናቃይ የሆኑ አስተባባሪ ነግረውናል። ከተፈናቀሉበት የገጠር ቀበሌ አብሯቸው የመጣ የመንግሥት አመራርም እገዛ እያደረገ መሆኑንም ሰምተናል። አዲስ ማለዳ ከቦታው በምትመለስበት ወቅት ሊረሸኑ ሲሉ ሲያመልጡ ጉዳት ደርሶባቸው ለሕክምና ወደ ኮምቦልቻ ሲያመሩ የነበሩን ተፈናቃይ አግኝታ አነጋግራለች።

እንድሪስ ሰዒድ ይባላሉ። ሐብሩ ወረዳ ቁጥር/ቀበሌ 20 ውስጥ፣ ከነቤተሰባቸው ተደብቀው ከነበሩበት ቦታ ስንቅ በማለቁ ዱቄት ሊያመጡ ሲሄዱ አካባቢውን በወረሩ ታጣቂዎች ተይዘው ነበር። ከ9 ሰዓታት እንግልት በኋላ እንዲረሸኑ ተወስኖ የታዘዘው ታጣቂ መሣሪያውን ደግኖ ወደሰዋራ ቦታ ሲወስዳቸው ያዩ 40 የሚሆኑ ግብረ አበሮቹ እነሱ ፊት ጭንቅላታቸውን እንዲመታ ያዛሉ። ሁኔታውን የተረዱት እኚህ አባት አስከሬናቸው ወደገደል እንዲወድቅ ሲያስጠጓቸው ሁኔታውን በመረዳት፣ ራሳቸውን ወደ ገደል በመወርወር ያመልጣሉ።

እየተንከባለሉና እየተንፏቀቁ ሲወርዱ ከመገሸላለጥ በተጨማሪ በእግር በእጅና በወገባቸው ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል። 40 የሚሆኑት አሳዳጆች ጥይት እስኪጨርሱ ለመግደል ቢሞክሩም ትረፊ ያላት ነፍስ ነበረችና ሳይሳካላቸው ቀርቷል። በእንዲህ አይነት ሁኔታ ያመለጡት እኚህ ጉዳተኛ ከጥይት አረር እንደራቁ መሄድ አቅቷቸው የነበረ ሲሆን፣ በሰዎች እገዛ በሽርጥና በእንጨት ሸክም ቤተሰብ ጋር ተወስደው ሲረዱ ቆይተው ሕመሙ ስለጠናባቸው የጦር ግንባሩን ተሻግረው ወደ መጠለያው ለመቀላቀል ችለዋል።

ይህን ያህል የጥይት ውርጅብኝ ደርሶባቸው በመትረፋቸው የተናደዱት አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀው የህወሓት ቡድን ታጣቂዎች፣ አንድ የአካባቢው ሰው ይዘው መልዕክት አስልከው ነበር። ከዛ ሁሉ ጥይት የተረፉበትን መንገድ እንዲያስረዱና ያባከኑትን ጥይት እንዲከፍሉ አለበለዚያ ንብረት በማውደም ቤተሰቦቻቸውን እንደሚበቀሉ ቢነገራቸውም፣ ለእሳቸውም እንደማይመለሱ ስለተረዱ ከመልክተኛው ጋር በመሆን እየተደገፉ ጃራ የተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ ደርሰዋል። ቤተሰቦቻቸው ቦታ ቀይረው ወደሌላ ቦታ እንዲደበቁ ማድረግ ቢችሉም፣ ስማቸውን አስመዝግበው ዕርዳታ ማስላክም ሆነ ራሳቸው ሔደው ማምጣት አለመቻላቸውን በጉዟቸው ወቅት ነግረውናል።

እሳቸው የሚኖሩበት ቀበሌ እንዳይያዝ ነዋሪው ኹለት ቀን ሙሉ ተታኩሶ ስለነበረ፣ ለበቀል በትንሹ 45 ቤቶችን ወራሪዎቹ ላምባ(ነዳጅ) እየረጩ እንዳቃጠሉ ይመሰክራሉ። ሰባት ገበሬዎችን አርደዋል የሚሉት እኚህ አባት፣ የሸሹትም ተመልሰው እንዳይኖሩ እሸትና አገዳ በማበላሸት ላይ ናቸው ብለዋል። ታጣቂዎቹ ፍየልና ዶሮ የቀራቸው የለም ጨርሰዋቸዋል ያሉን ሲሆን፣ ቤታችንንም እያወላለቁ ማብሰያ በማድረጋቸው ስንመለስ ምንም አይኖረንም ሲሉ መንግሥት በቶሎ ከአካባቢው እንዲያባርራቸው ጠይቀዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 153 መስከረም 29 2014
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com