የእለት ዜና

የነጻነት ትግል፤ የደካሞች ዕርግማን?

የነጻነት ትግል እየተባለ ሕዝቦች እርስበርስ መጠፋፋት ከጀመሩ ቆይተዋል፡፡ ያልተሳካላቸው የመኖራቸውን ያህል ሕዝብን ለያይተው ለጉስቁልና እንዲሁም ለኃያላን መፈንጫ ያደረጉ የየዘመኑ ልኂቃን መኖራቸውን አዲሱ ደረሰ በጽሑፋቸው ያትታሉ፡፡ የፓናማ እንደአገር መመስረትን ታሪክ እያጣቀሱ የሱዳን ልኂቃንም ሆኑ የትግራዮቹ ራሳቸውን አኮስሰው ጉልበተኛ የውጭ አገራን ከሚያገዝፉበት የዕርግማን ትግል እንዲወጡ የሚያስችላቸውን ነጥቦች እንዲህ ያነሳሉ፡፡

ሱዳን ወደነጻነት የማምራት አዝማሚያ ያለው ትግልን ማስጀመር በሚፈልጉ ኃይሎችና በወታደራዊው ክንፍ ሥልጣን የማስረዘም ፍላጎት እየተናጠች ነው። የቤጃ ጎሳ አባላት በእኛ ስም የተፈረመው የሠላም ሥምምነት አይመለከተንም በሚል የሱዳንን ምስራቃዊት የባለ ባህር በር ከተማ የሆነችውን ፖርት ሱዳንን ከካርቱም ጋር የሚያገናኘውን መንገድና የነዳጅ ማስተላለፊያ ከዘጉ ዋል አደር ብለዋል። “ጉዳያችን በፍጥነት የማይታይ ከሆነም ይህ የነጻነት ትግል ማስጀመሪያችን አድርጋችሁ ውሰዱት፤ የራሳችንንም አገር መመስረት እንችላለን!” ሲሉም አስፈራርተዋል።

በእኛም አገር እንዲሁ በፌደራል መንግሥትና በህወሓት መካከል የፌደራል የጦር ካምፕን ህወሓት በማጥቃቱ ምክንያት የተጀመረው ወታደራዊ ግብግብ ከተፈጠረ ዓመት ሊሞላው ነው። ሰቆቃውን ወደጎረቤት ክልሎች ጭምር አጋብቶ የቀጠለው ግብግብ፣ በቆየባቸው ወራት ከሰማናቸው ድሞጾች መካከል የራሳችንን አገር እንመሰርታለን፤ ትግሉም የነጻነት ሆኗል የሚሉት ይገኙበታል።

ለዛሬ በትግራይም ሆነ በምስራቅ ሱዳን ስለሚደረጉት እንቅስቃሴዎች ልጽፍላቸሁ አይደለም ሐሳቤ። ለመሆኑ የነጻነት ትግል እውን የነጻነት ነው? ምክንያቶቹስ ስለእውነት የሕዝብ ዘለቄታዊ ጥቅሞችን ያነገቡ ናቸው? ወይንስ የልኂቃን ጊዚያዊ ሀንጎቨር የሚፈጥሯቸው በራሪ ሐሳቦች ናቸው? የሚለውን ለመመለስ ነው የዚህ ጽሑፍ ዓላማ።

ከነዚህ የነጻነት ትግሎች ጀርባ ያለው ትልቅና ሕዝብ በጋራ የገነባው ሕልም ሳይሆን፣ የአንድ ግለሰብ ቀቢጸ ተስፋ ሊሆን ይችላል ቢባል ማን ያምናል። ትግል ተደርጎባቸው ተሳክተዋል ከሚባሉት ነጻነቶች መካከል እጅጉን የሚያዝናናውም የሚያስገርመውም የፓናማ ስለሆነ ለዛሬ በምናብ ወደፓናማ ይዣችሁ እንድጓዝ ፍቀዱልኝ።

ፓናማ 1914…
የባህር ላይ ንግድም ሆነ የባህር ላይ ውንብድና የሚያስቀኑበት ዘመን! ከኹሉም ይልቅ የባህር ኃይል ትልቁ እና ብቸኛው የአገራት ወታደራዊ አቋም ግዝፈት ማሳያ በሆነበት ዘመን ነው ታሪኩ። በሰሜንና በደቡብ አሜሪካ መካከል፤ የአትላንቲክንና የፓሲፊክ ውቂያኖሶችን አላገናኝ ብለው በመካከል ከተሰነቀሩት የየብስ መሬቶች መካከል በአንደኛው ላይ ነው የታሪኩ ቦታ። አነዚህን ኹለት የውኃ አካላትን አገናኝቶ ንግድና ግዛት ማስፋፋትን እንዴት ማሳለጥ ይቻላል የሚለው ሐሳብ የአውሮፓውያኑን እና የአሜሪካውያኑን አእምሮ ሰቅዞ ከያዘ ዋል አደር ብሏል።
እነዚህን ኹለት የውኃ አካላት ከሚያገናኙ መሬቶች መካከል ያሁኗ እራሷን የቻለች አገር፣ የያኔዋ ደግሞ አንዲት የኮሎምቢያ ግዛት ፓናማ አንዷ ነበረች። በዚህች ግዛት ውስጥ ፈረንሳውያን ኢንጂነሮች እና ባሀብቶች ፓሲፊክና አትላንቲክን ለማገናኘት ሲለፉ ነበር የከረሙት። ከኢንጂነሮቹ መካከል የግብጹን የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ምርኩዝ የሆነውን የስዊዝ ካናልን እንዲሠራ ያስቻለውን ጽንሰ ሐሳብ የነደፈው ፈረንሳዊው ፈርዲናንድ ዲሌሴፕ ይገኝበታል።

የፈርዲናንድ ንድፈ ሐሳብ ብዙ ገንዘብ ተበጅቶለት ቢተገበርም፣ በብዙ አስር ሺሕዎች የሚቆጠሩ ባሪያዎችን ጉልበት ከመበዝበዝ እና በቁፋሮ በተፈጠሩ ጉድጓዶች ውስጥ በተጠራቀሙ ኮሬዎች አማካኝነት የተስፋፋው ወባ ከአምስት ሺህ በላይ የቀን ሰራተኞችን ሕይወት ከመቅጠፍ አላለፈም። ሐሳቡ አይሠራም በሚል ገንዘባቸውን የሰጡ ባለሀብቶች ድጋፋቸውን አቁመው ወደአገራቸው ቢመለሱም፣ ፈርዲናንድን የመሰለ የካናሎች ጌታ ተስፋ ቢቆርጥም፣ ሌላ ፈረንሳዊ ኢንጂነር ግን ይህንን ካናል ለመፍጠር የማይገመት እርቀትን ለመጓዝ ቆርጦ ይነሳል- አዶልፍ ጎዲን ፊሊፕ።

በወቅቱ አሜሪካውያኑ ፓናማ ላይ ሳይሆን ኒካራጉዋ ላይ የራሳቸውን ካናል ለመገንበት እየተንደፋደፉ ነበር። ይህንን የተገነዘበው ፊሊፕ ወደ አሜረካ ኮንግረስ አምርቶ፣ “ሰዎች የኒኩዋራጋው ፕሮጀክታችሁ ብዙም አዋጭ አይደለም፤ ኒኩዋራግዋ በእሳተ ገሞራ (ቮልካኖ) ፍንዳታ የሚናጥ አካበቢ ነው” በማለት የቮልካኖ ፍንዳታ ምስል ያለበት የኒኩዋራግዋ ቴምብር ለሴኔተሮች እየዞረ ያድል ጀመር፤ ሐሳባቸው እንደማያስኬድ ወተወተ።

አሜሪካውያኑም ፍርሀት ገባቸው፤ ፕሮጀክታቸውንም አቋረጡ። ፊሊፕ ያን ጊዜ እኔ የተሻለ ሐሳብ አለኝ ብሎ ብቅ አለ፡- ካናሉን ፓናማ ላይ ለመገንባት። አሜሪካውያኑ ትንሽ ካቅማሙ በኋላ፣ “ግን ፓናማ እኮ የኮሎምቢያ አካል ናት። ኮሎምቢያውያኑ ከፈቀዱ ብቻ ነው ያንተ ሐሳብ ላይ ገንዘብ የምናወጣው!” ይሉታል። ፊሊፕ፤ “እርሱን ለኔ ጣሉት!” ብሎ የኮሎምቢያ ግዛት ወደነበረችው ፓናማ ይጓዛል።

ፓናማ ያሉ ጥቂት ልኂቃንን ሰብስቦ፤ “ጎበዝ ምን ትጠብቃላችሁ። ቦጎታ ያለው መንግሥት እኮ ስለናንተ ደንታ የለውም። እናንተ እኮ የራሷ ባህር በር ያላት ምርጥ እራሷን የቻለች አገር መሆን ትችላላችሁ። እናንተ ወስኑ እንጂ ጉዳዩን ያለምንም ደም መቃባት አኔ አስፈጽመዋለው” ይላቸዋል።

በፓናማ ያሉት ልኂቃን ፈራ ተባ ብለው፣ “ግን አንተ እኮ አንድ ተራ የፈረንሳይ ኢንጂነር ነህ፤ አንዴት ነው አገር መፍጠር የምትችለው?!” ይሉታል። “እርሱን ለኔ ጣሉት። በጉዳዩ ላይ አምባሳደር እንደሆንኩ የሚገልጽ የሆነ ወረቀት ብቻ ስጡኝ፤ አኔ እጨርሰዋለው።”
ፓናማውያኑም “በል እንግዲህ ካልክ፤ ከተሳካልህ ምልክት ስጠንና እኛም ከዚህ እናንቀሳቅሰዋለን!” ይሉታል።

ፊሊፕ ያቺን ወረቀት ይዞ ሲበር ወደ አሜሪካውያኑ ጋር ይመለሳል። ነገሩ ያላማራቸው የኮንግረስ አባላት ነገሩን አጣጥለው መልሰውትም ነበር። ከየት መጡ ሳይባሉ ኢምፔሪያሊዝም አፍቃሪ ናቸው የሚባሉት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ቴዲ ሩዝቬልት ብቅ አሉ።
“የነጻነት ትግል አቀጣጥሎ ተጨማሪ ግዛት ማግኘትማ የተካንኩበት ሥራ አይደል እንዴ። በል እስቲ ሐሳብህን አስረዳኝ!” ይሉታል።

ፊሊፕ በደስታ፤ “አኔ ወደፓናማ ተመልሼ ፓናማውያን ለነጻነታቸው የሚያደርጉትን አመጽ አቀጣጥላለሁ። እርሶ የሚጠበቅቦት የኮሎምብያ መንግሥት ከቦጎታ ጦር ልኮ የነጻነት ትግሉን እንዳያስተጓጉለው ወደፓናማ የባህር በር ሐይሎትን አስጠግተው ብቻ ይጠብቁኝ” ይላቸውና ወደፓናማ ሲበር ይመለሳል።

ፊሊፕ እንዳለው የአሜሪካውያኑ የባህር ኃይል ወደፓናማ ይጠጋል፤ በፓናማም የነጻነት አመጽ ይቀጣጠላል። ቦጎታ የተቀመጠው የኮሎምቢያ መንግሥት ለፓናማ ብሎ ኮሎምቢያን ማጣት ይኖራል በሚል ፍራቻ ለፓናማ ሳይደርስ ይቀራል። ፓናማም አገር ትሆናለች።
ፓናማ አገር በሆነች በንጋታው፤ አሜካውያኑና ፊሊፕ ዶማ ይዘው የፓናማን ካናል ሲቆፍሩ ይታያሉ። ያንን ያስተዋሉት ፓናማውያኑ፤ “ምን እየሰራችሁ ነው፤ ማንስ ፈቀደላችሁ?!” ሲሉ ይጠይቃሉ።

“ምነካችሁ፤ ለፊሊፕ የአምባሳደርነት ወረቀት ሰጥታችሁትስ የለ፤ እኛ ደግሞ ከርሱ ጋር ተፈራርመናል!” ይላሉ። አሜሪካውያኑ በነጻነት ትግል ስም ፓናማን መሥርተው፣ የፓናማን የንግድ መተላለፊያ አስገንበተው፣ ፓሲፊክ እና አትላንቲክ ውቂያኖስን አጋጥመው የዓለም ንግድን ሲያሳልጡት ከረሙ።

በደጉ ዘመን፤ ተጠቅመው አንደ ቆሻሻ ከጣሏት በኋላ፤ ፓናማ በአሁኑ ወቅት አገር አይሏት ወይ የኮሎምቢያ ግዛት፣ እንዳው ዝም ብላ ማንም የሚወጣ የሚገባባት በተለይ የአሜሪካውያኑና እና የአውሮፓውያኑ የግብር መሰወሪያ ከተማ ሆና ቀርታለች።

ነጻነት ለነሱና ለኛ…
ከላይ ባነበብነው ታሪክ ውስጥ የነ ፊሊፕ ታሪክ እውነት ሳይሆን የሆነ የሆሊዉድ ታሪክ ውስጥ ያለ ገጸ ባህሪ ታሪክ የመሰለው ቢኖር ፍጹም ይሳሳታል። ደቡብ አፍሪካዊው ማርቲን ፕላውት የዕርዳታ ገንዘብን ለመሣሪያ መግዣነት አውሎታል ብሎ ለወቀሰው ድርጅት ለራሱ የነጻነት ትግል የዓለም አቀፍ አታሼ ሆኖ ሲያገለግል ላየ፣ አሊያም የሆሊውድ ተዋናዩ ጆርጅ ክሉኒ እና አባቱ በደቡብ ሱዳኑ የነጻነት ትግል ማጠቃለያ የነበራቸው ድርሻ መርምሮ ላነበበ፣ የነጻነት ትግል ለነጭ ግለሰቦች የሀብት ማካበቻ ከመሆን የዘለለ ትርጉም አልባ እንቅስቃሴ መሆኑን ይገነዘባል።

የሚያሳዝነው አብዛኛውን ጊዜ የሐሳቡ ጠንሳሾች እራሳቸው የነፊሊፕ አይነት ግለሰቦች እንጂ የአገሬው ባለቤቶች ያለመሆናቸው ብቻ አይደለም። ሐሳቡ ከባህር ወዲያም ይሁን ከባህር መለስ የነጻነት ትግል በነጻነት ቢያበቃ በዚህ ጽሑፍ ባልሞገትነውም ነበር። ደቡብ ሱዳን ከነጻነት በኋላ፣ ሰርቢያ ከነጻነት በኋላ፣ ኤርትራ ከነጻነት በኋላ ምን መስለው እንደኖሩ ላነበበ ፓናማ እንደውም እጅግ የተሻለ ቦታ ናት ማለቱ አይቀርም።

ከጠንካራ እና ግዙፍ ግዛት ተገንጥሎ እራስንበራስ የማስተዳደር ጽንሰ ሐሳብ እና ለሱ የሚደረገው ትግል የነጻነት ሳይሆን የደካሞች እርግማን እንደሆነ ማሳያው ደግሞ ነጻነት ለኛና ለነሱ የተለያየ ትርጉም ስላለውም ጭምር ነው።
ነጻነት ለነሱ መግዘፍ ነው፤ ግዛት ማስፋፋት! ከፓናማ መፈጠር በፊት በነበሩት መቶ ዓመታት ውስጥ የኢምፔሪያሊዝም/ የግዛት ማስፋፋት ዓለም አቀፍ ቢዘነስ ለአሜሪካውያኑ የጦፈበት ዘመን ነበር። ከስፔን ጋር የፈበረኩት ጦርነት ፊሊፒንሶችን ጉዋምና ፖርተሪኮን እንዲይዙ አድርጓቸዋል። የሁዋይን መንግሥት ገልብጠው የዌክ ደሴትን ወደግዛታቸው አስገብተዋል፤ የአላስካን ግዛት ወደአገረ አሜሪካነት ቀይረዋል።

በቅርቡ አንኳን የግዛት ማስፋፋት አጀንዳ እየተተገበረ ሰንብቷል። ራሽያውያኑ የሶቪየት ኅብረትን ያክል መግዘፍ ባይቻላቸውም የክራይሜን ግዛት ጠቅልለዋል። ቻይኖቹ በአካል ብቻ የጠቀለሏትን ሆንግ ኮንግ በሕግም ጠቅልለዋል። ታይዋን ላይ ያላቸው ፍላጎት የሦስተኛውን የዓለም ጦርነት እንዳያስነሳ ያስፈራል። አውሮፓውያኑም ቢሆኑ በባለፉት 70 አመታት በአምሳል ባይጣመሩም፣ በአካል አንድ ሆነው ጠላትህ ጠላቴ፤ ኪስህ ኪሴ ተባብለው ኖረዋል።

እንደ ኢትዮጵያ እና ሱዳን አይነት የገዛ አገራቸውን ለማድከም ጠንክረው የሰሩ የፖለቲካ ልኂቃን በበዙባቸው አገራት አንዲት አስቂኝ ግን ውስጠ መርዝ አበባል አለች። “ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ስለድንበርና የአገሪቱ ቅርጽ እንጂ በውስጡ ስላሉት ዜጎች ግድ የለውም” የምትል። እውነት ነው ለዜጎች ሕይወት ግድ ያለው መንግሥት እንዲኖር መታገል አይጠላም። መግዘፍ፤ ግዛት ማስፋት ግን ወደዜጎች ተጠቃሚነት እንደሚቀየር ከነጮቹ ልንማር ይገባል።

በሱዳንም ሆነ በትግራይ የሚገኙ ወንድሞቻችን ከማዕከላዊ መንግሥታቸው ጋር ያላቸውን ልዩነት በአንድ አገርነት ማዕቀፍ ውስጥ እንዲፈልጉ እንመክራለን። ለኛ ማነስ ነጻነት፤ ለነጮቹ ግን ነጻነት ማለት መግዘፍ ሆኖ ተተርጉሞ እስከመቼ እንኖራለን?!


ቅጽ 3 ቁጥር 153 መስከረም 29 2014
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

Comments: 1

Leave a Reply to Alferd Gideon Cancel Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com