የእለት ዜና

የእርስ በርስ ጦርነት ማስወገጃ መፍትሄ

ግጭት በተለያዩ ምክንያቶች የመከሰቱን ያህል መፍትሄውን ለማወቅ መንስዔውን ማወቁ አስፈላጊ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተስፋፋ የመጣው የርስበርስ ግጭት መንስዔ በዋናነት ያልተመጣጠነ እና ኢ-ፍትሃዊ የሆነ የሃብት ክፍፍል ነው የሚሉት ሳምሶን ኃይሉ፣ መፍትሔ ነው ስላሉት ገለልተኛና አካታች ተቋማትን መገንባት ላይ ትኩረት አድርገው የፅሁፋቸውን ኹለተኛውን ክፍል እንዲህ አሰናድተውታል።

ግጭት በተለያዩ ምክንያቶች የመከሰቱን ያህል መፍትሄውን ለማወቅ መንስዔውን ማወቁ አስፈላጊ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተስፋፋ የመጣው የርስበርስ ግጭት መንስዔ በዋናነት ያልተመጣጠነ እና ኢ-ፍትሃዊ የሆነ የሃብት ክፍፍል ነው የሚሉት ሳምሶን ኃይሉ፣ መፍትሔ ነው ስላሉት ገለልተኛና አካታች ተቋማትን መገንባት ላይ ትኩረት አድርገው የፅሁፋቸውን ኹለተኛውን ክፍል እንዲህ አሰናድተውታል።

ባለፈው ሳምንት ባስነበብኩት ፅሁፌ በኢትዮጵያ ከቅርብ ግዜ ጀምሮ በስፋት እየተስተዋለ ላለው የርስ በርስ ግጭት ዋና መንሰዔ የብሔር ፖለቲካ ብቻ ሳይሆን ያልተመጣጠነ እና ኢ-ፍትሃዊ የሆነ የሃብት ክፍፍል ያስከተለው ኢኮኖሚያዊ ሰበብ መሆኑን ለማስረዳት ሞክሬያለው። በዚህ ፅሁፌ ደግሞ ያልተመጣጠነ እና ኢ-ፍትሃዊ የሆነ የሃብት ክፍፍል ምንጭ ይሆናሉ ያልኳቸውን ምክንያቶች ከማስቀመጥ ባሻገር የመፍትሄ ሃሳቦችን ለመሰንዘር እሞክራለሁ።

ጉዳዩን በጥልቀት ለመረዳት ግን አስቀድመን የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ መዋቅር ማየት ያስፈልጋል። የሰው ልጆች የተለያዩ ፍላጎቶች ቢኖሯቸውም በጋራ የሚኖሩ ፍጡሮች ናቸው። አብረው ሲኖሩ ደግሞ እራሳችውን የሚያስተዳድሩበት፣ ጥቅማቸውን የሚያስጠብቁበት እና የርስ በርስ ግንኙነታቸውን የሚያጠናክሩበት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ አደረጃጀቶች ይፈጥራሉ። ኢትዮጵያም የሯሷ የሆነ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ መዋቅሮች አሏት።

ፖለቲካ ማለት አንድ ሃገር ውስጥ የሚኖሩ ህዝቦች እራሳቸውን የሚያስተዳድሩባቸውን ህጎችን፣ ወደ ስልጣን ማማ መውጫ መንገድን እና የሚከተሉትን የስርዐት አይነት የሚመርጡበት ሂደት ማለት ነው። ይህን ሂደት የሚያሳልጡት ደግሞ የፖለቲካ ተቋማት ናቸው። እነዚህ የፖለቲካ ተቋሟት በአብዛኛው በመንግስት ተፅእኖ ስር ይገኛሉ። ኢትዮጵያን እንደማሳያ ብንወስድ የተወካዮች ምክር ቤት፣ የፌደሪሽን ምክር ቤት፣ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እና እንደ ፍርድ ቤት የመሳሰሉ ተቋማት በዋነኛነት ሊጠቀሱ የሚችሉ የፖለቲካ ተቋማት ናቸው። ጥቂትም ቢሆኑ በመንግስት ቁጥጥር ስር ያልሆኑ የፖለቲካ ተቋሞች ግን አሉ። ለምሳሌ፣ በፖለቲካ ጉዳዮች ላይ የሚሰሩ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎችን ልንጠቅስ እንችላለን።

የኢኮኖሚ ተቋሞች ደግሞ የአንድን ሃገር የምርት፣ የንግድና የፍጆታ ሂደትን የሚመሩና የሚቆጣጠሩ መዋቅሮች ናቸው። ለምሳሌ፣ የግብርናን ዘርፍ ብንመለከት እንደ ግብርና ሚኒስተር የመሳሰሉት ተቋማት የምርጥ ዘር፣ ማዳበሪያና ብድርን ለገበሬው የሚያሰራጩ ወይም ስርጭት የሚቆጣጠሩ አካላት ናቸው። እንደ ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስተር ያሉ ተቋማት ደግሞ የኢንዱስትሪ ምርትና የንግድ እንቅስቃሴን ይቆጣጠራሉ። በሌላ በኩል ደግሞ እንደ ገቢዎች ሚኒስተር ያሉ የኢኮኖሚ ተቋማት ግብርን የሚሰበስቡና የሃብት ስርጭትንና ክፍፍልን የሚያሳልጡ ተቋማት ናቸው። ምንም እንኳን አብዛኞቹ የኢኮኖሚ ተቋሞች በመንግስት ተዖእኖ ስር ቢሆኑም ከዚህ ውጭ ሊጠቀሱ የሚችሉ አሉ። የግል አምራችና የንግድ ድርጅቶ፣ ባንኮች እና የመድህን ሰጪዎች ከግል የገንዘብ ተቋማት ሊጠቀሱ ይችላሉ።

ማህበራዊ መዋቅር ደግሞ በአብዛኛው ከመንግስት ተዖእኖ ውጭ ሆነው ባህልን የሚያዳብሩ እና የጋራ እሴቶችን የሚቀርዑ የሃይማኖት ተቋማትን በዋነኛነት ያካትታል። በፊውዳሉ ስርዐት ጊዜ ማህበራዊ መዋቀር በተለይም የሃይማኖት ተቋማት በኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ ተፅእኖ ፈጣሪዎች የነበሩ ቢሆኑም ሃይማኖትና መንግስት በይፋ ከተለያዩ በኋላ ተፅእኗቸው ቀስ በቀስ እየቀነሰ መጥቷል። በተቃራኒው ደግሞ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ተቋሞች ሚና በኢትዮጵያን እያደገ መቷል።

አሁን ሃገሪቷ ያለችበትን ሁኔታ ለመረዳት የእነዚህን የፖለቲካና ኢኮኖሚ ተቋማት አደረጃጀት በጥልቀት መመልከትን ይጠይቃል። የፖለቲካና ኢኮኖሚ ተቋሞች በሁለት መንገድ ሊደራጁ ይችላሉ። የመጀመሪያው አሳታፊ ያልሆነና ኢ-ፍትሃዊ የሆነ የስልጣን ክፍፍልን ማእከል ያደረገ አደረጃጀት ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ አሳታፊ፣ ፍትሃዊ እና ብዝሃነት የተላበሰ የስልጣን ክፍፍል የሚንፀባረቅበት አወቃቀር ነው።

ኢትዮጵያም በውስጧ ብዙ እና የተለያየ ፍላጎቶች ያሏቸው ህዝቦች የሚኖሩባት ሰፊ ሃገር ብትሆንም፣ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ተቋሞች አደረጃጀት ብዝሃነት የተላበሰ፣ አሳታፊና ገለልተኛ አይደለም። በኢትዮጵያ ወደ ስልጣን መውጫው መንገድ የዲሞክራሲ አንዱ መገለጫ በሆነው ነፃ ምርጫ በኩል ቢመስልም፣ እስከ ቅርብ ድረስ ሃገሪቷ ያደረገቻቸው ምርጫዎች ብዙ ጥያቄ ተነስቶባቸዋል። ከ1983 ወዲህ በተደረጉት ምርጫዎች ኢሕአዴግ በሰፊ ለዩነት በማሸነፍ እንደ ህግ ኣውጭ፣ ህግ ኣስፈጻሚና ህግ ተርጓሚውን የመሳሰሉ ተቋማትን ያለአንዳች ተቀናቃኝ ሊቆጣጠር ችሏል።

በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ያለ ከሰማኒያ በላይ ብሔሮች ባሉበት አገር ነፃ ምርጫ የማካሄድ ዋና ግቡ የፖለቲካ ተቋሞችን በተለይም ሶስቱ የመንግስት አካላት ማለትም ህግ ኣውጭው፣ ህግ ኣስፈጻሚውና ህግ ተርጓሚው አሳታፊና ሚዛናዊ በሆነ መልኩ ለማዋቀር ነው። እነዚህ ሶስት የፖለቲካና ተቋሞች ብዝሃነት የተላበሰና አሳታፊ በሆነ መልኩ ከተደራጁ ተጠያቂነት የሰፈነበት ስርዓት ይፈጠራል። ያለበለዚያ ግን፣ በተለያየ አጋጣሚ ስልጣን የሚይዙ ባለስልጣናት እነዚህን ኣካላት መሳሪያ ኣድርገው የግል ጥቅማቸውን ሊያሳድዱ ይችላሉ ። በተለይም እነዚህ ሶስቱ የመንግስት መዋቅሮች ከአንድ ፓርቲ በመጡ ሰዎች ከተደራጁና ከተፈጠሩ፣ ተጠያቂነት ስለሚጠፋ ስልጣን ከህዝብ እጅ ይወጣና የጥቂቶችን ፍላጎት መስፈጸሚያ ሆነው ይቀራሉ። ህግ ኣውጭው፣ ህግ ኣስፈጻሚውና ፍርድ ቤት የጥቂቶች ፍላጎት አስፈፃሚ ሲሆኑ፣ ትክክለኛ ፖሊሲ መቅረፅም ሆነ ሃገሪቷ የሚያጋጥሟትን ችግሮች በሚገባ መመርመርና አማራጭ መፍትሄ መፈለግ አዳጋች ይሆናል።

የኢኮኖሚ ተቋሞችና ፖሊሲዎች የፖለቲካ መዋቅሩ ነፀብራቅ ናቸው። ምክንያቱም በአንድ ፓርቲ የተደራጀው የፖለቲካ መዋቅር በተመሳሳይ መልክ የኢኮኖሚ ተቋሞችን አቃፊና አሳታፊ ባልሆነ መንገድ ሊገነባ ስለሚችል ነው። በዚህ ሁኔታ ውስጥ እንደ መሬት ያሉ የተፈጥሮ እና ሌሎች ሃብቶችን አጠቃቀምና ክፍፍል ላይ ግልጽነት ስለሚጠፋ ብዙ ጥያቄዎች እየተመዘዙ ይወጣሉ። በኢትዮጵያ እንዳየነው እነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ ሳያገኙ ሲቀሩ ሁኔታው ወደ እርስ በርስ ግጭት ያመራል።

አካታችና ገለልተኛ ያልሆኑ ተቋሞች ሲኖሩ፣ የአንድ ሃገር መዋዕለ ንዋይ ተወዳዳሪና ይበልጥ ምርታማ በሚያደርጓት ዘርፎች ላይ ሳይሆን የፖለቲካና ኢኮኖሚ መዋቅሩ በተቆጣጠሩት ጥቂት ሰዎች ፍላጎት መሰረት ይሆናል። ይህንን ሀቅ ከአስር አመት በፊት ተግባራዊ የተደረገውን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ እንደማሳያ በመጠቀም ማሳየት ይቻላል። ከ2002 እስከ 2008 ከዛም እስከ 2013 በሁለት ምእራፍ ተከፍሎ ተግባራዊ የሆነው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ የተቀረፀው አሳታፊነተ በጎደለው መንገድ በጣም በጥቂት የመንግስት ባለስልጣኖች ነበረ። ምንም እንኳን ይህ እቅድ የተለጠጠና የሃገሪቷን አቅም ያላገናዘበ ነው ብለው አንዳንድ ምሁራንና እንደ የአለም ባንክ ያሉ ድርጅቶች ቢሟገቱም፣ የፖለቲካ መዋቅሩ አሳታፊ ስላልነበረ እቅዱ ያለምንም ተቋውሞ ሊፀድቅ በቅቷል። የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዐቅዱን የሚያስፈዖሙት የኢኮኖሚ ተቋሞች በተመሳሳይ መንገድ ስለተደራጁ፣ ውጤቱ ለተንሰራፋ ሙስና ሃገሪቷን ማጋለጥና ለአንድ ቡድን ሃብት ያለልክ መሰብሰቢያ መሳሪያ ከመሆን አልዘለለም።

አብዛኛውን በእቅዱ ላይ የተካተቱትን ፕሮጀክቶች ለማስፈፀም ስራውን የተረከበው የብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን በመባል ይታወቅ የነበረው የመንግስት ድርጅት፣ በመቶ ቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ በሙስና ሲያባክንም ሆነ የግንባታ ሂደቱን ሲያጓትት ጠያቂ አልነበረውም። ይህን አውዳሚ አካሄድ በጊዜው ማረም የሚገባው የህግ ኣውጭው አካልም ሆነ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባሎች እንደ ሌላው ህዝብ ከመታዘብ በቀር አስፈላጊውን እርምጃ ሲወስዱ አላየንም። እንዲያውም ሙስናን ለማጋለጥ እነዚህ የፖለቲካ ተቋሞች አቅምም ሆነ ፍላጎት አልነበራቸውም። ስለሆነም፣ ሙስና የስርዓቱ ዋና መገለጫና ህልውናው ሊሆን በቅቷል። በተመሳሳይ መንገድ የተቀረፁና ስራ ላይ የዋሉ እንደ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንዱስትሪ ልማት እና የሰፋፊ እርሻዎች ማስፋፊያ የመሳሰሉ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎችን መጥቀስ ይቻላል።

እዚህ ላይ መገንዘብ የሚገባን አሳታፊና ገለልተኛ ያልሆኑ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ተቋሞች መኖር አንድን ሃገር ከአድገት ላይገቱ ይችላሉ። ለምሳሌ፣ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ተቋሞች በአንድ የፖለቲካ ፓርቲ አምሳያ በተደራጁባት የቀድሞዋ ሶቪየት ህብረት ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚ አድገት ተመዝግቦ ያውቃል። ኢትዮጵያም ባለፉት አስራ አምስት ዓመታት ከፍተኛ የሆነና ባለ ሁለት አሃዝ አመታዊ እድገት አስመዝግባለች። በታሪክም ሆነ በቅርቡ እንዳየነው ግን እንደዚህ አይነት እድገት ቀጣይነት ያለው አይደለም።

ሌላው ትኩረት የሚሻው ሃቅ ደግሞ ያልተመጣነ እድገት (unbalanced growth strategy) ተገን አድርጎ ኢኮኖሚን ማስፈንጠር የተለመደ አካሄድ መሆኑ ነው። በተለይ ድሃ ሃገሮች ኢኮኖሚያቸውን ለማስፈንጠር ለአጭር ጊዜ ሃብት በአንድ ቦታ እንዲጠራቀም ወይንም በተወሰነ ቡድን እንዲያዝ ማድረጋቸው ያልተለመደ አሰራር አይደለም። እንደ ኢትዮጵያ ልማታዊ መንግስትን ተከትለው የነበሩ እንደ ደቡብ ኮርያና ቻይና የመሳሰሉ ኣገሮች ኢኮኖሚያቸውን ለማስፈንጠር ሃብት ወደ አንድ አቅጣጫ እንዲፈስ አድርገው ያውቃሉ። ለምሳሌ፣ ደቡብ ኮርያ 1979ዎቹ እንደነ ሂወንዴ በመሳሰሉ ግዙፍ የንግድ ተቋማት እና የመንግስት የልማት ድርጅቶች ላይ ከፍተኛ ሃብት አፍስሳ የሚያስደንቅ እድገት ለማስመዝገብ ችላለች። ነገር ግን በደቡብ ኮርያ እንዳየነው ይህ በአንድ ቦታ የተከማቸ ሃብት በአጭር ጊዜ ውስጥ ምርታማነትንና ተወዳዳሪነትን እንዲጨምር አድርጎ ፍትሃዊ እና ተመጣጣኝ የሃብት ስርጭት እንዲሰፍን ማስቻል አለበት።

በኢትዮጵያ የነበረው ይህ ሂደት ግን ረዘም ያለ ጊዜ በመውሰድ ሃብት ወደ አንድ አቅጣጫ ረዘም ላለ ጊዜ እየፈሰሰ እንዲቆይ አድርጓል። ይህ የሃብት ዝውውር የመጣው በፖለቲካ ውሳኔ ብቻ በመሆኑ የሃገሪቱን የረጅም ጊዜ የኢኮኖሚ እድገት ሳያገናዝብ የተወሰነ ነበር። በውጤቱም ኢ ፍተሃዊ የሃብት ክፍፍል ከማስከተሉም በላይ በራሱ የግጭት መንስዔ ለመሆን በቅቷል።

ታሪክ እንደሚነግረን ዲሞክራሲያዊና ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ብቻ አይደለም አሳታፊና ገለልተኛ ያልሆኑ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ተቋሞች የሚፈጠሩት ። ለምሳሌ፣ በጀርመን የናዚ ፓርቲ ወደ ስልጣን ማማ የወጣው ህጋዊ በሆነ መንገድ ሲሆን፣ አንዴ ስልጣኑን ከተረከበ በኋላ ግን ገለልተኛ እና አሳታፊ የነበሩትን ተቋሞችን በሙሉ የጥቂት ግለሰቦች ፍላጎት ሟሟያ እንዲሆኑ አድርጎ አደራጅቷቸዋል። ሌሎች ተመሳሳይ ተሞክሮ ያላቸው ሃገሮችን መጥቀስ ይቻለል። ነገር ግን እዚህ ላይ በዋናነት መገንዘብ ያለብን ዲሞክራሲያዊና ነፃ ምርጫ ማካሄድ ብቻውን በቂ ላይሆን ይችላል።

በቅርቡ በኢትይጵያ በተደረገው ምርጫ የብልፅግና ፓርቲ በከፍተኛ ብልጫ አሸንፏል። ከበፊቶቹ ጋር ሲነፃፀር የተሻለ የነበረው በቅርቡ የተደረገው ምርጫ ለወደፊቱ የተሻለ ተስፋ እንድንሰንቅ ቢያደርገንም፣ በውስጡ ግን አውዳሚ መሳሪያ መሸሸጉን ልንረሳ አይገባም። ለዚህ ሙግቴ ማሳመኛ የሚሆነኝ ምክንያት የፖለቲካና ኢኮኖሚ ተቋሞች አሁንም በአንድ ፓርቲ አምሳያ የመገንባት እጣ ፈንታ ሊገጥማቸው ስለሚችል ነው። ኢትይጵያ አሸናፊ ሆና እንድትወጣ ከተፈለገ ግን የብልፅግና ፓርቲ መሪዎች ይህንን ሁለት ገፅታ ያለውን እውነታ ተገንዘበው የፖለቲካና ኢኮኖሚ ተቋሞች እንደገና ሲደራጁ አሳታፊና ገለልተኛ የሆነ መንገድ ሊከተሉ ይገባል። ይህም የፓርቲው አባል ይልሆኑ ግን በሙያቸውና በሀቀኝነታቸው የተመሰገኑ ግለሰቦችን ወደ ፖለቲካና ኢኮኖሚ ተቋሞች መጋበዝንና በነፃነት ሃገራቸውን እንዲያገለግሉ መፍቀድን ይጠይቃል።

ኢትዮጵያም በውስጧ ብዙ እና የተለያየ ፍላጎቶች ያሏቸው ህዝቦች የሚኖሩባት ሰፊ ሃገር ብትሆንም የፖለቲካና ኢኮኖሚ ተቋሞች አደረጃጀት ብዝሃነት የተላበሰ፣ አሳታፊና ገለልተኛ አይደለም።
በዋናነት መገንዘብ ያለብን ዲሞክራሲያዊና ነፃ ምርጫ ማካሄድ ብቻውን በቂ ላይሆን መቻሉን ነው።


ቅጽ 3 ቁጥር 153 መስከረም 29 2014
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com