የእለት ዜና

በጦርነቱ ምክንያት ያልታረሱ ማሳዎች የሚያስከትሉት የምርት ማሽቆልቆል

በኢትዮጵያ አብዛኛው የማኅበረሰብ ክፍል የሚተዳደረው በግብርና ሥራ እንደሆነ ይታወቃል። ግብርና ከምግብነት አልፎ ለውጭ ምንዛሬ፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራ እንዲሁም ለኢንቨስትመንት መስፋፋት ከፍተኛውን ሚና እንደሚጫወት ስለሚታመን፣ በተለይም በክረምት ወራት ትምህርት ቤቶች፣ ኮሌጆች፣ ዩኒቨርሲቲዎች ሲዘጉ የአርሶ አደር ልጆች ወላጆቻቸውን የሚያግዙበት መስክ ነው።

በግብርናው ዘርፍ የተሻለ የምርት አቅርቦት ለማግኘት ደግሞ በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ በግብርና ሥራ የተሠማሩ አርሶ አደሮች ወቅቱን ጠብቀው ማረስ ይጠበቅባቸዋል።
ማንኛውም የሥራ መስክ የራሱ የሆነ የአሠራር ሒደት እንዳለው ሁሉ በግብርናው ዘርፍ የተሰማሩ አርሶ አደሮች የሚያከናውኑት እያንዳንዱ ተግባር በወቅቶች የተከፋፈለ እንደሆነ ይናገራሉ።

እንደሚሉትና እንደሚስተዋለውም በግብርናው ዘርፍ የዓመቱ ወቅቶች በሥራ የተከፋፈሉ ናቸው። አርሶ አደሮች የበጋው ወቅት ማሳቸውን የሚያለሰልሱበት፣ የክረምቱ ወቀት የሚዘሩበት፣ የዘሩትን የሚያርሙበት፣ የሚኮተኩቱበት ሲሆን፣ የመኸር ወቅት ደግሞ ሰብሉን ሰብስበው፣ ፍሬውን ከገለባው ለይተው ዓመቱን ሙሉ የደከሙበትን ምርት የሚያገኙበት ነው።

አሁን አሁን በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች በግብርናው ዘርፍ የተሰማሩ አርሶ አደሮች ወቅቱን ጠብቀው የእርሻ ስራቸውን ማከናወን እንዳልቻሉና የ2013 የምርት ዘመን ውጤቱ አጥጋቢ ሊሆን እንደማይችል ሲያወሱ ይደመጣሉ።
ለችግሩ መፈጠር የሚመዟቸው ምክንያቶችም አሉ። ከእነዚህም መካከል የክረምት ዘግይቶ መግባት አንዱ ሲሆን፣ አገራችን ላይ የተጋረጠው የእርስ በርስ ጦርነት ደግሞ ለችግሩ ቀንደኛ ምክንያ ነው።

አርሶ አደሮች የተጣለባቸው ኃላፊነት ማሳቸውን አለስልሰው የተሻለ ምርት ማቅረብ ነው። ምንም እንኳን ጦርነት ሲከሰት ማንኛውም ሰው መረባረብ ቢያሻም፣ በአሁኑ ጦርነት ግን አርሶ አደሮች ላይ ሚዛኑ የደፋ ይመስላል።
በመሆኑም፣ ጦርነቱ ባለባቸው አካባቢዎች ያሉ አርሶ አደሮች ቡቃያዎችን መዝራትም ሆነ መንከባከብ በሚገባቸው ሰዓት ከጦር ሜዳ ውለው ማደራቸውና መሞታቸው በግብርናው ዘርፍ የምርት ዕጥረትን ሳያስከትል አይቀርም።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጁት የህወሓትና ኦነግ ሸኔ ታጣቂ ኃይሎች በተለያዩ የአገሪቱ ቦታዎች ማለትም በቤኒሻንጉል ጉምዝ፣ በአፋር እና በአማራ ክልል አካባቢዎች ጥቃት መሰንዘር መጀመራቸው በተለያዩ የሚዲያ ተቋማት አማካይነት ከተሰማ ሰንበትበት ብሏል።

በመሆኑም፣ በየትኛውም የሥራ መስክ ለመሠማራት በመጀመሪያ ደረጃ ሠላምና መረጋጋት ከፍተኛውን ሚና እንደሚጫወት ቢታወቅም፣ አሁን ላይ በአገራችን ላይ የሚስተዋለው ጦርነት የብዙዎችን ሕይወት ስለመቀማቱ ያለው ነባራዊ ሁኔታ ምስክር ነው። በ2013 የክረምት ወራት ግጭት በተስፋፋባቸው አካባቢዎች በተለይም በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወላጋ ዞንና በአማራ ክልል ከሚገደሉትና ከሚፈናቀሉት አብዛኞቹ የምርት ምንጭ የሆኑት ገበሬዎች እንደሆኑ ይነገራል።

ምንም እንኳን በአንዳንድ አካባቢዎች ገና ሠላም ባለመስፈኑ ምክንያት ምን ያክል ሔክታር መሬት እንዳልተዘራና አጥጋቢ ቡቃያ እንደሌለ በውል ማውቅ ቢያስቸግርም፣ በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ ዞን ጊዳ አያና አንገር ጉትን ሊሙ ወረዳ የሚገኙ ከመንደር አንድ እስከ መንደር አራት፣ እንዲሁም መንደር ሰባትና ስምንት አካባቢዎች ግማሾቹ ማሳዎች በፖለቲካ አለመረጋጋቱ እንዳልታረሱ ነዋሪዎቹ ይናገራሉ።

የአካባቢው ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት ከሆነ፣ በሊሙ ወረዳ የሚገኙ ግማሾቹ የእርሻ መሬቶች ደግሞ በቡቃያ የተሸፈኑ ሲሆን፣ አርሶ አደሮች ሰብሉን ለመንከባከብ ወደ ማሳው በተሰማሩበት ወቅት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጀው የኦነግ ሸኔ ታጣቂ ባደረሰባቸው ያልታሰበ ጥቃት የተሳቀቀው የአካባቢው ኗሪ፣ ዳግም ወደ ማሳዎች ሔዶ ሰብሎችን ለመንከባከብ ስጋት ስላደረበት ሰብሎቹ አረም በልቷቸው ቀርተዋል በማለት ገልጸዋል።

ነዋሪዎቹ አክለውም፣ በእርሻ ቦታዎች ሰብሎቹን ሊንከባከቡ አቅንተው በነበረበት ወቅት በኦነግ ሸኔ ኃይሎች ኹለት ወንዶችና አንዲት ሴት እንደተገደሉ፣ እንዲሁም ባሳለፍነው መስከረም 16 እንኳን ሦስት ገበሬዎች እንደተገደሉ የገለጹ ሲሆን፣ ይህም በሕይወት ባሉት ሰዎች የተዘሩት ሰብሎች አንኳን ለመሰብሰብ ከፍተኛ ስጋትና መሰናክል እንደፈጠረባቸው አብራርተዋል።

በርግጥ በ2013 የክረምት ወቅት በአገራችን ላይ የሚስተዋለው ጦርነት በኢትዮጵያ ውስጥ የተከሰተ የመጀመሪያ ጦርነት እንዳልሆነ ታሪክን ዘወር ብሎ መመልከት ይቻላል። የታሪክ ምሁራን ሲያወሱ እንደሚደመጠው፣ ኢትዮጵያ ባለፉት በርካታ ዘመናት ውስጥ ከውስጥም ከውጭም አያሌ የሚባሉ ጦርነቶችንና ግጭቶችን ያሳለፈች መሆኑን ነው።

ቢሆንም ግን ጦርነቱ ለውጊያ የተመረጡ ታጣቂዎች ተፋልመው የሚሸናነፉበት እንጅ በዚህ ወቅት ከሚስተዋለው በተቃራኒ ጦርነት ከታጣቂዎች አልፎ ንጹኃን ላይ የማያነጣጥር፤ እንዲሁም ተፋላሚዎቹ ነጋቸውን በማሰብ ሰብሎችና እንስሳት እንዳይጎዱ አካባቢዎችን መርጠው ስለሚፋለሙ በማሳዎች ላይ ይደርስ የነበረው ክስረት እምብዛም እንዳልነበረም ይወሳል።

በዚህ ወቅት የሚካሄደው ጦርነት ግን፣ “የመሸናነፍ ወሰን ያልተቀመጠለት”፣ እንስሳትን እንዲሁም ሰብሎች ላይም ያነጣጠረ በመሆኑ የሚያስከትለው ኢኮኖሚያዊ ማሽቆልቆል ለአንድ አካባቢ ይቅርና ለአገሪቱ እንኳን ቀላል የማይባል እንደሆነ ጦርነቱ በተካሄደባቸው አካባቢዎች ያሉ ነዋሪዎች በተደጋጋሚ ይገልጻሉ።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጀው የኦነግ ሸኔ ታጣቂ ኃይል በሚንቀሳቀስባቸው አካባቢዎች በሚሰነዝረው ጥቃት ከ75 በመቶ በላይ የሚሆነው እርሻ እንዳልተዘራ፣ በአንዳንድ አካባቢ የተዘሩ እህሎችም እንክብካቤ እንዳላገኙና የምርት ውጤታቸው አጥጋቢ እንደማይሆን ነው ነዋሪዎቹ ለአዲስ ማለዳ የገለጹት።

በአንገር ጉትንና በዙሪያዋ የሚኖሩ ገበሬዎች የበቆሎ፣ የአኩሪ አተር፣ የቦለቄ፣ የሰሊጥ፣ የማሽላ፣ የለውዝና የኑግ ምርትን በማምረት ይታወቃሉ የሚሉት ነዋሪዎቹ፣ በዘንድሮው ዓመት 75 በመቶ ከሚሆነው እርሻ ምርት አለማግኘት ከባድ ጉዳት ያስከትላል ይላሉ።
በሌላ በኩል፣ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ጳጉሜ አንድ 2013 ባወጣው መረጃ መሰረት በሽብርተኝነት የተፈረጀው ህወሓት በሚሰነዝረው ጥቃት የእርሻ ማሳዎች በዘር ሳይሸፈኑ እንደቀሩና፤ ቀድመው የተዘሩት ሰብሎችም በወቅቱ እንክብካቤ ባለማግኘታቸው በአረም፣ ተባይና በእንሰሳት መውደማቸውን ያመላከተ ሲሆን፣ የመልሶ ማሻሻያ ዕቅድ ዝግጀት ላይ መሆኑንም ገልጾ እንደነበረ የሚታወስ ነው።

በግብርና ልማት ዘርፍ የሚተዳደረው ብዙኅኑ አርሶ አደር እጅግ አስከፊ በሆነ ችግር ወስጥ ይገኛል። ቀድመው የተዘሩት ሰብሎች በጦርነት፣ በአረም፣ በተባይና በእንሰሳት ወድመዋል የሚለው የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ነው።
ጦርነቱ በተለይም በሰሜንና በደቡብ ጎንደር፣ በሰሜን ወሎ፣ በዋግኸምራ ዞኖች በግብርና ልማት ላይ ከፍተኛ ውድመትን አስከትሏል የሚሉት የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ተስፋሁን መንግስቴ፣ በሰብል ያልተሸፈኑ ማሳዎች እንዳሉ ሆነው፣ ጦርነቱ ከመፈጠሩ በፊት የተዘሩት ቡቃያዎች በተባይና በእንሰሳት መጥፋታቸውንም ጠቁመዋል።

ይህን ተከትሎ የመጣውን ችግር ለመቅረፍ እንቅስቃሴ እየተደረገ ቢሆንም፣ የዳግም ማሻሻያውን ተግባር ለማከናዎን የዘርና የግብርና መሠረተ ልማት አውታሮች ውድመት መሰናክል እንደሆነም ነው የተገለጸው።
የሰብል ውድመት በደረሰባቸው ከጦርነቱ ነጻ በወጡ አካባቢዎች መስኖ በመጠቀም በትንሽ ዝናብ በአጭር ጊዜ ውስጥ መድረስ የሚችሉ እህሎችን ለመዝራት ዕቅድ ላይ እንደሆነ ያመላከተው ግብርና ቢሮው፣ ለመስኖ ልማት በግንባታ የተዘጋጁ የውኃ አውታሮች ላይ ጉዳት እንደደረሰና በኅብረት ሥራ ማኅበራት የተከማቹ የተለያዩ የግብርና ምርጥ ዘሮች እንደተዘረፉም አመላክቷል።

የግብርና ቢሮው ገለጻ እንደሚያመላከተው ከሆነ፣ የአማራ ክልል የአገሪቱን የሰብል ምርት 35 በመቶ በመሸፈን ትልቅ ሚና የሚጫወት መሆኑን ነው። በተፈጠረው ጦርነት ያልተዘሩና እንክብካቤ ሳያገኙ የከሰሩ ሰብሎች ምንም እንኳን ገና በሽብርተኝነት በተፈረጀው ህወሓት ቁጥጥር ስር ያሉ አካባቢዎች ሰብል የክስረት መጠኑ ባለመታወቁ ምርቱ እስካሁን ሲሸፍነው ከነበረው መጠን በስንት እንደሚቀንስ በውል ባይታወቅም፣ እንደስከዛሬው ግን በምርቱ የነበረው ሽፋን እንደሚቀንስ ይታመናል ነው የተባለው።
በምስራቅ ወለጋ ዞን አንገር ጉትን ዙሪያ በሚገኙ ማሳዎች በተለይም የበቆሎ ምርት በሰፊው እንደሚመረት የሚገልጹት ኗሪዎቹ፣ በሽብርተኝነት የተፈረጀው ኦነግ ሸኔ በተለይም ከሐምሌ ማገባደጃ ወር ጀምሮ በሚሰነዝረው ጥቃት ኗሪዎቹ ስለተፈናቀሉ አንዳንድ ቀድመው የደረሱ ሰብሎችን እንኳን መሰብሰብ እንዳልተቻለ ነው።

አዲስ ማለዳ ጉዳዩን በማስመልከት የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲቱት ኢኮኖሚስት የሆኑት ክፍሉ ገደፈ (ዶ/ር) ጋር ቆይታ ያደረገች ሲሆን፣ የኢኮኖሚ ባለሙያው ሐሳባቸውን በሚከተለው መልኩ አካፍለውናል።
የኢኮኖሚ ባለሙያው እንደገለጡት ከሆነ፣ ጦርነት በአገር ላይ ከሚያስከትለው ማኅበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቀውሶች ባልተናነሰ ኢኮኖሚ ላይም ቀላሉ የማይገመት ውድመትን እንደሚያስከትል ነው።

አዲስ ማለዳ ከባለሙያው መረዳት የቻለቸው በጦርነት ወቅት ሰላማዊ እንቅስቃሴ በማድረግ ሥራዎችን ማከናወን ስለማይቻል፣ እንኳን የምርት አቅርቦት እጥረት ለጦርነቱ መከላከያ የሚሆኑ መሣሪያዎችን ለመግዛት የሚደረገው ወጭም በኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንደሚያስከትል ነው።

እንኳን በክልሎች ደረጃ በአንድ አካባቢ የሚፈጠር ችግር ራሱ የአገሪቱን ዕድገት ወደ ኋላ እንደሚጎትት ይታወቃል የሚሉት ክፍሉ፣ ጦርነት ወደን ሳይሆን ተገደን የምንገባበት የፍልሚያ አውድማ ነው። በመሆኑም እንኳን የሰብል መጎዳትን የሰው ልጅን ጉዳት እራሱ ለመታደግ የሚያዳግትበት ክስተት ስለሆነ ጦርነቱ አሁን ባሉት አጭር ጊዜ ውስጥ ካልተቋጨ ኢኖሚያዊ ማሽቆልቆሉ ላለመኖሩ በድፍረት መናገር አይቻልም።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ምንም እንኳን በከሰረው ሰብል ልክ የምርቱን አቅርቦት መሸፈን ባይቻልም፣ ዝም ብሎ ከማየት መሞከሩ ቀላል ማይባል መፍትሄ ይኖረዋልና ልክ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ እንደጀመረው አይነት የሰብል ልማት እንቅስቃሴ በሌሎች በጦርነቱ አካባቢዎችም ማከናወኑ የማያሻማ ተመራጭ ተግባር ነው ሲሉም ነው አስተያየታቸውን ያስቀመጡት።

የክረምት ወራቱም እያለቀ መሆኑን ተከትሎ፣ ተረጋግቶ የሚሠራና እንዲሁ በጥድፊያ የሚተገበር ሥራ ሠፊ ልዩነት ስላለው የሰብል ማሻሻያ ሥራ መሥራቱ ብዙም አመርቂ ውጤት አያመጣም የሚሉት የኢኮኖሚ ባለሙያው፣ ዘላቂ ውጤት ለማምጣት ግዴታ ጦርነቱ በመንግሥትም በሕዝብም ርብርብ መቆም እንዳለበት ነው።

መስኖዎችን ተጠቅሞ በሰብል ያልተሸፈነውንና በእንክብካቤ እጥረት የኮሰሰውን ምርት ለማማካካስ እንኳን ጦርነቱ ባለባቸው አካባቢዎች በሠላም መንቀሳቀስ፤ ከጦርነቱ ነጻ በወጡ አካባቢዎች ደግሞ የመንግሥትና የሕብረተሰብ መተጋገዝ ከፍተኛውን ሚና እንደሚጫዎት ነው ያመላከቱት።

በአጠቃላይ ችግሩን ለመቅረፍ ከመንግሥት፣ ከሕዝብ እንዲሁም ለግብርና ሥራው ቅርብ ከሆኑ የግብርና ባለሙያዎች የጠነከረ መደጋገፍ የአንበሳውን ድርሻ የሚይዝ መፍትሔ እንደሆነ ነው የጠቆሙት።


ቅጽ 3 ቁጥር 153 መስከረም 29 2014
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com