የእለት ዜና

የብዙዎችን ሕይወት ያመሰቃቀለው ስደት

ድሮ በተለይ በጃንሆይ ዘመን አዲስ አበባ ውስጥ ዝናብ ሲያካፋ፣ ‹ዝናቡ እስከሚያባራ ለምን ፓስፓርት አናወጣም› በማለት እንደመዝናኛም በማድረግ የአዲስ አበባ ሰዎች ፓስፓርት ያወጡ እንደነበር ይነገራል። በዚያን ዘመን ኢትዮጵያውያን ወደ ሌላ አገር የሚሄዱት አንድም ለትምህርት፣ ለጉብኝት ወይም ለመንግሥታዊ ሥራ እንደነበር ይነገራል። በዚህም አንድ ኢትዮጵያዊ በሄደበት አገር ሁሉ ክብር ነበረው። ተፈሪ መኮንን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ እንግሊዝ ባቀኑ ወቅት የለንደን ሕዝብ እርሳቸውን ለማየት ሲጠብቅ እንደዋለ፣ እንዲሁም በአገረ አሜሪካ ከጆን ኦፍ ኬኔዲ ጋር ለራት ተቀምጠውና በአውራ መንገዶች ፎቷቸው ተሰቀሎ መታየቱ በወቅቱ ኢትዮጵያውያን በዓለም ሕዝብ ዘንድ የነበራቸውን ክብር ያሳያል። ከዚያ በፊትም ቢሆን ዳግማዊ አጼ ምኒልክ የነጮችን ምድር ይረግጣሉ የሚል መረጃ ተሰራጭቶ በነጮች ዘንድ እርሳቸውን የማየት ከፍተኛ ጉጉት አድሮ እንደነበር የታሪክ ምንጮች ያስረዳሉ።

በደርግም ዘመን ቢሆን በወቅቱ በነበረው ሥርዓት የተነሳ ካልሆነ በስተቀር ኢትዮጵያ አገሩን ጥሎ ለመሰደድ የሚፈልግ ዜጋ አልነበረም።

በአንድ ወቅት ለብዙ ዓመት ውጭ አገር የኖሩ በዕድሜ ገፋ ያሉ ኢትዮጵያዊ ለወጣቶች ንግግር ሲያደረጉ እንዲህ ብለው ነበር፣ ‹‹በደርግ ዘመን ለትምህርት ውጭ አገር ሔጄ ነበር። ሆኖም እዚያ እያለሁ ሁሌ የሚያጓጓኝ ነገር ትምህርቱን አጠናቅቄ ወደ አገሬ የምመለሰበት ቀን ነበር። ትምህርቴን ጨርሼ ወደ አገሬ ለመመለስ ወደ ኤምባሲ ስሄድ ግን፣ “ፀረ አብዮት ነህ” ተብዬ ወደ ኢትዮጵያ መመለስ እንደማልችል ተነገረኝ። በዚያ ምክንያት በኑሮዬ ከደረሰበኝ ሐዘን ይበልጥ በዕለቱ ያለቀስኩትን ለቅሶ አልረሳውም። አውሮፓ በምቾት መኖር እችል ነበር፣ ነገር ግን በዚያ ጊዜ በሰው አገር መኖር የማይታሰብ ነበር።››

ሰውዬው እንዳሉትም በዚያን ዘመን አትዮጵያውያን በሄዱበት አገር ሁሉ በክብር ተስተናግደው የሚመለሱበት እንጅ፣ በረሃ አቋርጠውና የሰው አገር ናፍቀው የሚሄዱበት አልነበረም። በዚያው ዘመን ኹለት በካናዳ አገር ትምህርት ላይ የነበሩ የኢትዮጵያ ዜጎች እንዲሁ፣ ትምህርታቸውን ጨርሰው ወደ አገራቸው ለመመለስ በተዘጋጁበት ወቅት የካናዳ መንግሥት ለኑሯቸው አስፈላጊውን ሁሉ አሟልቶላቸው ለካናዳ እንዲሠሩና እዚያው እንዲኖሩ ጥያቄ ያቀርብላቸዋል። ኢትዮጵያውያኑም የተከበረች አገር እንዳለችን እያወቀ የካናዳ መንግሥት እንዴት እንዲህ አይነት ርካሽ የሆነ ግብዣ ያቀርብልናል በማለት ክስ መስርተውበት እንደነበር በወቅቱ ነገሩን የተመለከቱ ሰዎች ይናገራሉ።

ደርግን አስወግዶ የአገሪቱን የሥልጣን መንበር የተቆናጠጠው ኢህአዴግ ሥልጣን ከያዘ በኋላ ግን ብዙ ኢትዮጵያውያን ለአገራቸውና ለሰው አገር ያላቸው እሳቤ በእጅጉ ሲቀየር ተስተውሏል። ከአገር መውጣትን እንደመታደል ከመቁጠር ጀምሮ ብዙዎች በአገራችን ሠርተን አንቀየርም፣ ኑረንም አያምርብንም የሚል ውሳኔ ላይ ደርሰው፣ የቻሉ በሕጋዊ መንገድ ያልቻሉ በሕገ-ወጥ መንገድ ከአገራቸው ርቀው ተሰደዋል።

‹ኢትዮጵያ ታበጽሕ እደዊሃ ኀበ እግዚአብሔር› ብለው የሚዘምሩ እና ኢትዮጵያ አገረ እግዚአብሔር ቅድስት አገር ናት ብለው የሚናገሩ ሰዎች ሳይቀር ውጭ አገር የመውጣት ሐሳቤን አሳካልኝ ብለው ብርቱ ጸሎት የሚያደርጉ እልፍ ዜጎች መኖራቸውን ብዙ ሰው ያውቀዋል። ከወጡ በኋላ ጸሎታችንን ለሰማ ለኢትዮጵያ አምላክ እያሉ ስለት የሚልኩም ብዙዎች ናቸው።

ይህ ብቻ አይደለም፣ ብዙ ሴቶች ትምህርታቸውን አቋርጠው ወደ አረብ አገራት ለሥራ ሲሄዱ ወዳጅ ዘመድ እና ጎረቤት ተስብስቦ፣ ድግስ ተደግሶ፣ ተዘፍኖ እና ተጨፍሮ ይላኩ እንደነበር የሚዘነጋም አይደለም።
ብዙ ነገር በአገር ሠርቶ ከመለወጥ ይልቅ ከአገር መውጣትን ያበረታታል። ማንም ቤቱ ቁጭ ብሎ ቴሌቪዥን ሲክፍት ‹ውጭ አገር ከሚገኙ ወዳጅ ዘመድዎ የሚላክልዎትን ገንዘብ በባንካችን ሲመነዝሩ የተለያዩ አጓጊ ሽልማቶችን ያገኛሉ› የሚል ማስታዎቂያ ሊያይ እና ሊሰማ ይችላል። በዚህ ጊዜ ወደ ውጭ የመውጣት ሐሳብ ሊያድርበት ይችላል ወይም ውጭ ዘመድ ባላቸው ሰዎች ሊቀና ይችላል።

ሆኖም ዜጎቸ ከተወለዱበት ቀዬ እርቀው መሄዳቸው ወይም ከአገራቸው ይልቅ ጉልበትና ዕውቀታቸውን ለሰው አገር መገበራቸው አይደለም የሚያስቆጨው። አገራቸውን ጥለው የወጡ ዜጎች አብዛኞቹ በስቃይ ውስጥ የሚኖሩ መሆናቸው ነው ስደታቸውን አሳዛኝ የሚያደርገው። ገና ለስደት ከቤታቸው ሲወጡ ጀምሮ እጅግ ብርቱ ስቃይ ይሰቃያሉ። ገንዘባቸውን በደላላ ይዘረፋሉ። በበረሀ በውኃ ጥምና በረሃብ ሞተው ይቀራሉ። ይታሰራሉ፤ ለአካል ጉዳት ይዳረጋሉ። ወደ ተለያዩ የባህር ዳርቻዎች ሲቀዝፉ በጭካኔ ወደ ባህር የተወረወሩት በርካታ ናቸው። የሟች ቤተሰቦች ሐዘናቸውን ሳይጨርሱ ከጎርቤት ደግሞ ሌሎች ለስደት ይነሳሉ።

ከዚህ ኹሉ መከራ አምልጠው ቢወጡ እንኳን አገራቸው ሳሉ የጎመዡለትን ነገር አያገኙም። የራሳቸው ባልሆነ አገር ውስጥ ሰው በመሆንና በዜግነት የሚገኙ የሰው ልጅ መብቶችን ለመጠቀም ዕድል የላቸውም።
በተለይ በዐረብ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የሚደርስባቸው መከራ ከኹሉም የከፋ ነው። ከፎቅ ላይ ይወረወራሉ። ይደበደባሉ፤ ይታሰራሉ፤ የሰሩበትን ደሞዘ ይቀማሉ፤ ያጠራቀሙትን ንብረታቸውንም ይዘረፋሉ።
ዐረብ አገር ቆይተው የመጡ ሰዎች እንደሚናገሩት ብዙ ኢትዮጵያውያን የሚሠሩት ሥራ ደስታ የሚሰጥ አይደለም።

በዚህ ላይ ሥሟ እንዳይጠቀስ የፈለገች አንዲት ሴት በዐረብ አገር ቆይታዋ ያየችውን ለአዲስ ማለዳ ተናግራለች። ‹‹ደጋማ ሥፍራዎች ላይ ለወራት ብቻቸውን ከብቶችን እና በጎችን የሚጠብቁ ብዙ ኢትዮጵያውያን ወንድ እረኞች አሉ። እኛ ወተት ልናመጣ ስንሄድ ከእነሱ ጋር መገናኘት አይፈቀድልንም። ወተቱን የሆነ ቦታ ላይ ያስቀምጡልንና ሔደን እንወስደዋለን። በምንም ሁኔታ አንዲት ሴት ከአንድ ኢትዮጵያዊ ወንድ ጋር እንድትገናኝ አይፈልጉም። ከቤት እንዳይወጡና ስልክ እንኳን እንዳይደውሉ ተከልክለው የሚኖሩ እህቶቻችን በጣም ብዙ ናቸው።
የኢትዮጵያ ሴቶች ሥራ እና ሙያ ጎበዞች ነን፤ የሚከፈለን ክፍያ ግን ሙያና ሥራ ከማይችሉ ደካማ የእስያ ሴቶች በጣም የወረደ ነው። ለምሳሌ፣ የፊሊፒንስ ሴቶች በጣም ከፍተኛ ብር ነው የሚከፈላቸው። ሥራ ግን የእኛን ሩብ ያህል እንኳን የመሥራት አቅም የላቸውም። እንደዚያም ሆኖ እነሱ ላይ ምንም አይነት ፆታዊም ይሁን አካላዊ ጥቃት አይደርስባቸውም። ክብራቸው አይነካም፣ መብታቸው አይጣስም።

ይህ የሆነው የአገራቸው መንግሥት ውጭ ለሚኖሩ ዜጎቹ ከፍተኛ ክትትልና ጥበቃ እንዲደረግላቸው ስለሚያደርግ ነው። እንደ ኢትዮጵያ መንግሥት የወደቁበትን የማያውቅ ግዴለሽ መንግሥት ስላልሆነ ተከብረው ይኖራሉ። ለምሳሌ፣ በዐረብ ወንድ ተደፍራ ልጅ በመውለዷ ልጁን ይዛ መውጣት ስለማትችል ሳትፈልግ እዚያ የምትኖር ኢትዮጵያዊት ሴት አለች። ብዙ ሴቶችም ሴተኛ አዳሪ ናቸው። ኢትዮጵያዊ ከአገሩም ውጭ የሚደርስበት ግፍ የከፋ ነው።››

እንዲሁ ሥማቸው እንዲጠቀስ የማይፈልጉ አንድ የውጭ አገር ሥራ እና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲ ባለቤት የሆኑ ግለሰብ በስደተኞች ጉዳይ ሐሳቸውን እንዲህ ሲሉ ሰጥተዋል፣ ‹‹በዚህ ሰዓት ኢትዮጵያዊ የማይኖርበት አገር አለ ብሎ ማመን አይቻልም። አገራችን ውስጥ ያለው ውስብስብ ቢሮክራሲና ሙስና ወጣቶች በአገራቸው ሠርቶ የመለወጥ ሐሳብ እንዳይኖራቸው አድርጓል። ማንም ቢመቸው ከአገሩ ውጭ መኖርን ይፈልጋል ብዬ አላስብም። እኔ አሁን በዚህ ወር ብቻ ወደ ኢራቅ ባግዳድ አስራ አራት ሴቶችን ልኬያለሁ። ባግዳድ ለብዙ ሰው ሩቅና የማትመች ሠላም የሌላት ትመስላለች። ኢትዮጵያውያን ግን ይህ ጉዳያቸው አይደለም። ወደ ጆርዳን፣ ኳታር፣ ኢራቅ፣ ቤሩት እና ሊባኖስ ብዙ ሰው ነው የምንልከው። አሁንም ወረፋ የሚጠብቁ ብዙ ናቸው። ሰዉ ውጭ የወጡት የሚደርባቸውን ስቃይ ማሰብ አይፈልግም።››
የኤጀንሲው ባለቤት በመጨረሻም፣ ‹‹በዚህ ሰዓት ከኢትዮጵያ የማይሻል አገር አለ ብዬ አላምንም። ሠላም ብትሆን እንኳን አንድ ሠራተኛ በብዙ ተቋማት በወር የሚከፈለውን ክፍያ ማየት በቂ ነው። ስለዚህ ሰው ወዶ አይሰደድም። ወደፊት ግን አገራችን የተሻለች ሆና ኹሉም በአገሩ ተከብሮ የሚኖርበትና ስደት የሚያበቃበት ግዜ ይመጣል ብዬ አስባለሁ›› ብለዋል።

አንድ ጸሐፊ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን አስመልክቶ በመጽሐፉ ላይ ‹‹ኢትዮጵያውያን አፍጋኒስታንም ይኖራሉ። የአሜሪካ ጦር ከአፍጋኒስታን ምድር ለቆ መውጣት ከአፍጋናውያን በላይ የሚያሳስባቸው ኢትዮጵያውያንን ነው። ምክንያቱም፣ የአሜሪካ ወታደሮች ከቦታው ከወጡ እነሱ ሥራ ያጣሉ። ለእነሱ ምግብ አብሳይ ሆነው ነው የሚኖሩት።›› ሲል አስፍሯል።

ባለፈው ዓመት 2013 ከወትሮ በተለየ ሁኔታ በተለያዩ የዐረብ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ያለምንም ምክንያት ከመታሰርና ንብረታቸውን ከመዘረፍ ጀምሮ ብዙ ስቃይ እንደደረሰባቸው አይዘነጋም።
ይህን ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግሥት ዜጎችን ወደ አገራቸው እመልሳለሁ በማለት በየሳምንቱ በርካታ በረራዎችን በማድረግ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎቸን ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ አድርጓል።
ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በዚህ ወር አጋማሽ ላይ ባወጣው መግለጫ ‹በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ረገድ ዜጎችን ከተለያዩ አገራት የማስመለስ ሥራ እየተከናወነ ሲሆን፣ ከሪያድ 794 ፣ ከጅዳ 892 ፣ ከየመን 357 ዜጎችን ማስመለስ ተችሏል› በማለት መግለጹ ይታወሳል። በሳዑዲ የሚገኙ ስደተኞችንም በማስመለስ ላይ እንዳለ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጨምሮ ገልጾ ነበር።

ሆኖም እስካሁን ባለው ጊዜ በመንግሥት ድጋፍ ከ50 ሺሕ የማያንሱ ስደተኛ ዜጎች ከተለያዩ አገራት የተመለሱ ቢሆንም፣ ‹እዚህ ከመጣን በኋላ የተደረገልን ነገር የለም። በስደት ላይ እያለን ከሚደርስብን ስቃይ ያላነሰ እዚህም በሥራ እጦት እየተሰቃየን ነው› የሚሉ ከስደት ተመላሾች ብዙ ናቸው።

የፌደራል የከተሞች የሥራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቡድን መሪ የሆኑት አቦዘነች ነጋሽ አሁን ላይ ከስደት ተመላሾችን በተመለከተ ምን እየተሠራ እንደሆነ ለአዲስ ማለዳ በሰጡት ቃል፣ ‹‹ተቋማችን ለስደተኞች ቅድሚያ ሰጥቶ ይሠራል። በመደራጀት፣ ብድር ሥልጠናና የገበያ ትስስር እንዲሁም መሥሪያና መሸጫ ቦታ ቅድሚያ እንዲያኙ ይደረጋል። በዚህም በአገራቸው ሠርተው እንዲቀየሩ ከማድረግ በተጨማሪ ስለ ስደት ያለውን አመለካከት መቀየር ይቻላል›› ብለዋል።

አቦዘነች ነጋሽ ከሥራ ዕድል ፈጠራ ዳይሬክቶሬት አገኘሁት ያሉትን መረጃ ጨምረው ለአዲስ ማለዳ በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪ፣ ‹‹አሁን ከስደት ከሚመለሱ ዜጎች ጋር በተያያዘ የሚሠራ አዲስ ነገር የለም፣ ሆኖም የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን በኮሚቴ እየሠራ ነው የሚል መረጃ አለ›› ሲሉ ገልጸዋል።

በዚህ ጉዳይ ላይ አዲስ ማለዳ ከሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን መረጃ ለማግኘት ያደረገችው ጥረት ኮሚሽኑ ፈቃደኛ ባለመሆኑ ሳይሳካ ቀርቷል። ሆኖም በማኅበራዊ ገጹ ስደተኞችንና ከስደት ተመላሽ ዜጎችን በሥራ ገበያ ውስጥ ለማካተት የሚያስችል ስምምነት ከስደተኞችና ስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ ጋር መፈራረሙን ኮሚሽኑ ገልጿል።

በሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ሚኒስቴር የሕፃናት ድጋፍ እና ኢንስፔክሽን ባለሙያ የሆኑት ሙሉዓለም ታደሰ በበኩላቸው፣ ለስደተኞች ሥራ ከመፍጠር አንጻር ከሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ጋር በጋራ እየሠሩ መሆኑን ገልጸው፣ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በዋናነት የሚመለከተው ከስደት ስለተመለሱ ሕፃናትና ሴቶች ነው ብለዋል። በዚህም አሁን ላይ ቀን በቀን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ዜጎች ከስደት ስለሚመለሱ እንደመጡ ሥራ መፍጠር አይቻልም፣ መጀመሪያ ተቀብለን ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲቀላቀሉ ነው የምናደርገው ሲሉ ተናግረዋል። በስደት ላይ ያሉ ብዙ ሴቶች ስለሚደፈሩ ልጅ ይዘው እንደሚመለሱ ገልጸው፣ ወላጅ የሌላቸውን ሕፃናት ደግሞ ወደ ማሳደጊያ ገብተው እንዲቆዩ እንደሚደረግ ጨምረው አመላክተዋል።

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ በ26 መጠለያዎች ከ900 ሺሕ በላይ ስደተኞች እና በሕገ-ወጥ መንገድ ከአገር ወጥተው የተመለሱ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያዊያን ዜጎች እንዳሉ መረጃዎች ያመለክታሉ።


ቅጽ 3 ቁጥር 153 መስከረም 29 2014
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com