የእለት ዜና

በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ንግድ ከውጭ ገበያ ከ32 ሚሊዮን ዶላር በላይ መገኘቱ ተገለጸ

የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨረቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ባለፉት ሐምሌና ነሐሴ ወራት የተለያዩ የጨርቃ ጨርቅ እና አልባሳት ምርት ውጤቶችን ለውጭ ገበያ በማቅረብ ከ32 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ማግኘት መቻሉን ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።
ተቋሙ 29.9 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ዕቅድ አስቅምጦ፣ 32.5 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘት ችሏል ሲሉ የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር ባንቲሁን ገሰሰ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ይህም ከዕቅድ አንጻር ሲለካ 107.7 በመቶ መሆኑን ነው ያስረዱት።

ዳይሬክተሩ አክለውም ያለቀላቸው እንደ ክር፣ ጨርቅ፣ ልብስ እና ባህላዊ አልባሳት የመሳሰሉ ምርቶችን ወደ ተለያዩ የዓለም አገራት እንልካለን ብለዋል። በዚህም በዋናነት ወደ ቻይና፣ ጣሊያን፣ ጀርመን፣ አሜሪካ፣ የተለያዩ የአፍሪካ እና የእስያ አገራት ምርቶች እንደሚላኩ ነው የጠቆሙት።

የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨረቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት በኹለት ወር ብቻ የተሻለ ገቢ እና አፈጻጸም ማስመዝገብ የቻለው፣ የተቋሙ ሠራተኞች እና ባለሙያዎች በኹሉም አምራች ኢንዱስትሪዎች እየተገኙ ድጋፍ እና ክትትል ስለሚያደርጉ ነው ተብሏል። በዚህም በአገሪቱ ጨርቃ ጨርቅ እና አልባሳት በሚያመርቱ የተለያዩ ኢንዱስትሪዎች ውስጥ የአሠራር ብክነት እንዳይኖር፣ በማምረት ሒደት ላይ የቴክኒክ ችግር እንዳያጋጥም እና የሥራ ጊዜ እንዳይባክን የሚረዱ ተከታታይ ሥልጠናዎች ይሰጣሉ ነው የተባለው። የምርት ጥራትን ለማስጠበቅ እና አዳዲስ ምርቶችን ለማምረት በባለሙያዎቹ ጥናት እና ምርምሮች እንዲሚከናወኑ፣ ብሎም አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችም በየጊዜው ተግባራዊ እንደሚደረጉ የተቋሙ ዳይሬክተር ጨምረው ገልጸዋል።

ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪውን መንግሥት ከማኑፋክቸሪንጉ ዘርፍ ቅድሚያ የሠጠው መሆኑን እና ኢትዮጵያንም መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለማሰለፍ ዋና የኢኮኖሚ ምንጭ እንደሚሆን ተነግሮለታል።

በአሁኑ ጊዜ በዓለም ገበያ ቀርበው ተወዳዳሪ የሆኑ ዘመናዊ ሹራቦችን ከሚያመርተው የደብረ ብርሃን ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ፓርክ በተጨማሪ በአዳማ፣ ሐዋሳ፣ ቦሌ ለሚ፣ ኮምቦልቻ እና ዱከም ሰፋፊ እና ትላልቅ የጨርቃ ጨርቅ እና አልባሳት አምራች ኢንዱስትሪዎች ያሉ ሲሆን፣ ወደፊትም አገሪቱ በዚህ ዘርፍ ትኩረት ሰጥታ ከሠራች የተሻለና ከፍተኛ ዕድገት ማግኘት የምትችልበት ሠፊ ዕድል አለ ተብሏል። በዚህም ለዘርፉ የሚሆን በቂ የተማረ የሰው ኃይል እንዳለ እና ዘርፉ በአነስተኛ ወጭ ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኝ እንደሆነ ተገልጿል።

በተጨማሪም፣ የአገሪቱ ቆላማ አካባቢዎች የአየር ንብረት ለጥጥ ምርት ምቹ በመሆኑ፣ ሠፋፊ የጥጥ እርሻዎችን በማዘጋጀት ያለውን የጥሬ ዕቃ አቅርቦት ችግር በመፍታት ዘርፉን ለማሳደግ መልካም ዕድል እንደሚፈጥር ነው የተገለጸው።
ከጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪዎች አንዱ ብቻ ከ 7 ሺሕ እስከ 20 ሺሕ ለሚደርሱ ዜጎች የሥራ ዕድል ስለሚፈጥር ዘርፉ በኢትዮጵያ ማደግና መስፋፋት እንዳለበት ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

ዳይሬክትሩ አክለው ኢትዮጵያ ለጨርቃ ጨርቅና አልባሳት እንዲሁም ለጥጥ ምርት ምቹ ስለሆነች እና ብዙ መልካም አጋጣሚዎች ስላሏት ወደፊትም ባለሀብቶች እዚህ ላይ ቢሰማሩ ራሳቸውን እና አገራቸውን ተጠቃሚ ማድረግ ይችላሉ ሲሉ ተናግረዋል።
በመጨረሻም፣ ዳይሬክተሩ በአገሪቱ ከኢንዱስትሪዎች መስፋፋት ጋር ተያይዞ የኃይል መቆራረጥ፣ የጥሬ ዕቃ አቅርቦት፣ የአስተዳደር ክፍተት፣ እንዲሁም ዕድሎችን ያለመጠቀም ችግሮች መኖራቸውን ጠቁመው፣ ተቋሙ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ዕጥረት ላለባት አገር በቀጣይ ወራት ከአሁኑ የላቀ የውጭ ምንዛሪ ለማስገኘት ዕቅድ ይዞ እየሠራ ይገኛል ብለዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 153 መስከረም 29 2014
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com