የእለት ዜና

ኤድና ኮንስትራክሽን የስምንት ወር ደሞዝ ሳይከፍል ሠራተኞቹን መበተኑ ተሰማ

የተክለ ብርሃን አምባዬ/ታኮን ኮንስትራክሽን እህት ኩባንያ የሆነው ኤድና ኮንስትራከሽን የስምንት ወር ደሞዝ ሳይከፍል የኮንስትራክሽን ሠራተኞቹ ሲሳተፉበት ከነበረ ሥራቸው አትሰማሩም ብሎ በማገድ እንደበተናቸው ምንጮቻችን ገለጹ።
በአዲስ አበባ ሲኤምሲ አካባቢ ተክለ ብርሃን አምባዬ በሚባለው የኮንስትራክሽን ተቋራጭ ድርጅት ግቢ አራተኛ ፎቅ ላይ የሚገኘው ኤድና ኮንስትራክሽን፣ ሠራተኞቹን ከሥራ እንዳገደና የስምንት ወር ደሞዝ እንዳልከፈላቸው ነው ከሠራተኞቹ መረዳት የተቻለው።
ድርጅቱ የሰራተኞቹን ደሞዝ ካለመክፈሉም ባሻገር፣ ያሉትን ንብረቶችም እንደደበቀ ነው የአዲስ ማለዳ ምንጮች ያመላከቱት።

የኤድና ኮንስትራክሽን ለድፍን ስምንት ወር ደሞዛችንን ሳይከፍል ከሥራ ገበታችን አፈናቅሎናል የሚሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፣ ድርጅቱ የምከፍለው ደሞዝ የለኝም ለማለት ኹለት የፒካፕ መኪናዎችን ታኮን በሚባለው እህት ኩባንያው እንደደበቀም ነው ቅሬታ አቅራቢ ለአዲስ ማለዳ የገለጹት።

ሠራተኞቹ አክለውም፤ ኤድና ኮንስትራክሽን የተክለ ብርሃን አምባዬ ወይም የታኮንን የዲዛይን ሥራ በመሥራት ሲሳተፍ የቆየ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

የኮንስትራክሽን ድርጅቱ ሠራተኞች ለአዲስ ማለዳ የተናገሩት፤ እንኳን የስምንት ወር ቀርቶ የአንድ ቀን ደሞዝም በምንም አይነት ሕገ-ወጥ በሆነ መንገድ መቆረጥ እንደሌለበትና ደሞዙን አለማግኘታቸው በዕለት ተዕለት ኑሯቸው ላይ ተጽዕኖ እንዳሳደረባቸው ነው።
በመሆኑም፣ የተደበቁት የኤድና ኮንስትራክሽ ንብረቶች ተሸጠውም ቢሆን ደመዛችን ሊከፈለን ይገባል የሚሉት ሠራተኞቹ፣ ጉዳዩን ይዘው ወደ ፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት እንዳቀኑ እና በኮንስትራክሽን ድርጅቱ ደርሶብናል ያሉትን በደል አቅርበው ክስ እንደመሰረቱም ነው የተናገሩት።

ኤድና ኮንስትራክሽንን በፍርድ ቤት እንደከሰሱ የተናገሩት ሠራተኞቹ፣ ባቀረቡት አቤቱታ መሠረትም ፍርድ ቤቱ ደረሰብን ያሉትን በደል አድምጦ ምላሽ እንደሰጣቸው ነው ያመላከቱት።

አዲስ ማለዳ ክስ ከመሰረቱት የኮንስትራክሽን ሠራተኞቹ የተረዳችው፣ የፌደራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን በመመልከት የኤድና ኮንስትራክሽን ዕቃዎች በሐራጅ ተሸጠው ደሞዛቸው እንዲከፈላቸው ትዕዛዝ የሰጠ መሆኑን ነው።
ለሠራተኞቹ ደሞዝ እንዲከፈል ትዕዛዝ የሰጠው ፍርድ ቤቱ፣ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13 የሚገኙ በዕዳ የተያዙ የኤድና ኮንስትራክሽን ዕቃዎች የፊታችን ጥቅምት ኹለት 2014 መግዛት ለሚፈልጉ ተጫራቾች በሐራጅ እንዲሸጡ ወስኗል።

ቅሬታ አቅራቢዎቹ ባቀረቡት ክስ መሰረት፣ የፌደራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤቱ በሐራጅ ጨረታ እንዲሸጡ ትዕዛዝ የሰጠባቸው ዕቃዎች የጨረታ መነሻ ዋጋ ስንት መሆን እንዳለበት፣ ጨረታው የት ቦታና በምን ሰዓትን እንደሚካሔድ መወሰኑም ተነግሯል።
የሐራጅ ጨረታው በስንት አንደሚጀምር ዋጋ የተተመነለት መሆኑን ለአዲስ ማለዳ የገለጹት በደል ደርሶብናል ባዮቹ፣ መገልገያ ዕቃዎቹ ለጨረታ የሚቀርቡት ተጠቃለው በአንድ መቶ አምስት ሺሕ ዘጠኝ ስልሳ ብር (105.960.00) መነሻ ዋጋ እንደሆነም አመላክተዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 153 መስከረም 29 2014
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!