የእለት ዜና

ስለ ጣና ሐይቅና አካባቢው የጥናት፣ ምርምር እና የዕውቀት ማዕከል ተቋቋመ

የጣና ሐይቅና ሌሎች የውኃ አካላት ጥበቃና ልማት ኤጀንሲ፣ የጣና ሐይቅና አካባቢውን የጥናት ምርምር መረጃና ማስረጃዎች ለተጠቃሚዎች ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል የዕውቀት ማዕከል ማቋቋሙን ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።
ኤጀንሲው መሠረቱን ጀርመን አገር በማድረግ በተፈጥሮ እና በብዝኃ ሕይዎት ላይ ከሚሠራ ‹ናቡ› ከተሰኘ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ጋር በጋራ በመተባበር ስለጣና ሐይቅ እና ተፋሰሱ በተለየ መልኩ ትክክለኛ መረጃ ከምንጩና ከባለቤቱ ለማግኘት ከኹለት ወር በፊት በኤጀንሲው ግቢ ውስጥ የዕውቀት ማዕከል ማቋቋሙ ነው የተገለጸው።

የዕውቀት ማዕከሉ መቋቋሙ ለተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች እና የምርምር ተቋማት የጥናትና ምርምር ውጤቶችን፣ እንዲሁም የማኅበረሰቡ ዕሴቶችን ለተመራማሪዎች፣ ለፖሊሲ አውጭዎች እና ለሕብረተሰቡ ተደራሽ በማድረግ፣ የሥራና የመረጃ ድግግሞሽን ብሎም ተጨማሪ የጊዜና የገንዘብ ወጪን በመቀነስ አዳዲስ የጥበቃና ልማት እንቅስቃሴዎችን ለማጎልበት ይረዳል ሲሉ የጣና ሐይቅና ሌሎች የውኃ አካላት ጥበቃና ልማት ኤጀንሲ ዋና ሥራ አስኪያጅ አያሌው ወልዴ(ዶ/ር) ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ዋና ሥራ አስኪያጁ አክለውም፣ የጣና ሐይቅና ሌሎች የውኃ አካላት ጥበቃና ልማት ኤጀንሲ መጀመሪያም ሲቋቋም በክልሉ የሚገኙ ሐይቆችን፣ ወንዞችን እና ውኃ ያዘሉ መሬቶችን ለመጠበቅ፣ ለመንከባከብና ለማልማት መሆኑን አብራርተዋል። አሁን ላይ የውኃ አካላትን ከመራቆት ከመጠበቅ በተጨማሪ፣ በጣና ሐይቅና በሌሎች የውኃ አካላት ዙሪያ ትክክለኛ ጥናት በማድረግ እንደ ምንጭነትና ማጣቀሻ የሚያገለግሉ ጥናታዊ ጽሑፎች እና የድርሰት ሥራዎች የሚገኙበት ማዕከል ማቋቋም አስፈላጊ መሆኑ በመወሰኑ ነው ማዕከሉ የተቋቋመ ተብሏል።

በመሆኑም፣ ስለ ጣና ማንኛውም ጉዳይ በማዕከሉ ውስጥ እንዲገኝ እና መረጃዎችን በተደራጀ መልኩ በማስቀመጥ ለአጥኝዎች፣ ለተመራማሪዎች እና ለተማሪዎች ክፍት ማድረግ እንደሚቻል ነው የገለጹት። ይህም ላሉት የውኃ አካላት ጥበቃና ልማት ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪ፣ ማዕከሉ ተማሪዎችና ጀማሪ ተመራማሪዎች ስለጣና ሐይቅ ስለዓባይ ወንዝ ፣ ስለሕዳሴው ግድብ፣ ስለገዳማት፣ ስለቱሪዝም መዳረሻዎች፣ ስለብዝኃ ሕይወትና እና ስለልማት ፕሮጀክቶች እንቅስቃሴ መረጃ የሚያገኙበት በመሆን ያገለግላል ተብሏል። በአማራ ክልል የተጀመረው ይህ ፕሮጀክት ውጤታማ ከሆነ በሌሎች ክልሎች የሚገኙ የውኃ አካላትን ለመጠበቅ ተመሳሳይ ሥራ እንደሚሠራም ተጠቁሟል።

የዕውቀት ማዕከሉ አሁን ላይ በጥቂት ባለሙያዎች የተደራጀና የመሥሪያ ቁሳቁሶች የተሟሉለት ሲሆን፣ ከኹለት ሳምንት በኋላ ሥራ እንደሚጀምር ነው የተጠቆመው።

በሌላ በኩል፣ በክረምቱ ምክንያት ወደ ጣና ሐይቅ የሚገባው የውኃ መጠን መጨመሩን ተከትሎ፣ ቀንሶ የነበረው እንቦጭ አረም በተወሰነ መልኩ መስፋፋቱ ተገልጿል። አሁን ላይ በአገሪቱ ያለው ወቅታዊ ሁኔታ ቅድሚያ የሚሰጠው በመሆኑ የሐይቁ ጉዳይ የተዘነጋ ቢመስልም፣ በቀጣይ በመንግሥት እና በማኅበረሰቡ እንቅስቃሴ እንደሚጀመር አያሌው ጨምረው ተናግረዋል።

ጣና ሐይቅ እና የጣና ሐይቅ መልክዓ-ምድር በ2008 በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የተመዘገበ በኢትዮጵያ ብቸኛው የውኃ አካል መሆኑ ይታወቃል።


ቅጽ 3 ቁጥር 153 መስከረም 29 2014
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com