የእለት ዜና

የቱሉ ሞዬ ጂኦተርማል ኃይል ለማመንጨት የሚረዳ ግንባታ ሊጀመር ነው ተባለ

የቱሉ ሞዬ ጂኦተርማል ኢነርጂ ከመሬት ውስጥ እንፋሎት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት የሚችል ፕሮጀክት ሲሆን፣ የሀይል ማመንጫ ግንባታውን ለማካሄድ መታቀዱን በቱሉ ሞዬ ጂኦተርማል ኢነርጂ ድርጅት የኮሚኒኬሽን ኃላፊ ነዚፍ ጀማል ገልጸዋል።
ነዚፍ ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቁት ይህንን ግንባታ ለማካሄድ ጨረታ የወጣ ሲሆን፣ በአሁኑ ሰዓት የሀይል ማመንጫው ቁፋሮ ላይ የሚገኝ የግንባታ ሂደት ነው ብለዋል።

በፈረንጆች 2020 የወጣው የመጀመሪያ ጨረታ ሰባት ትልልቅ አለም አቀፍ የተርባይን አምራች ድርጅቶች መወዳደራቸውንና በአሁኑ ሰዓት ኹለት ድርጅቶች ስራውን ተቀብለው ለመስራት እየተጠባበቁ መሆናቸውን ነዚፍ ጠቁመዋል።
በአሁኑ ሰዓት ጨረታው ላይ በቀረበው የቴክኒክ ብቃት መሰረት ከሰባት ድርጅቶች ውስጥ ኹለት ብቻ የቀሩ ሲሆን፣ በዋናነት ግንባታውን የሚያካሂደው እና በተጠባባቂነት ያለው ድርጅት ናቸው ሲሉ ተናግረዋል።

ከእነዚህ ኹለቱ ድርጅቶች ጋር ለመፈራረም በድርድር ላይ መሆናቸውን የጠቆሙት ነዚፍ በቅርቡ አሸናፊውን ድርጅት ተለይቶ የሚታወቅ ይሆናል ብለዋል።
በፈረንጆቹ 2022 ስራውን ለመጀመር ያቀደው የሀይል ማመንጫው ግንባታ የስራውን ኮንትራት ውል በ2021 ለመጨረስ እቅድ መያዙን አስታውቀዋል።

የቱሉ ሞዬ ጂኦተርማል ሃይል ለማመንጨት ይረዳል የተባለው ይህ ግንባታ፣ ከመሬት ውስጥ የሚገኘውን የእንፋሎት ሃይል ወደ ኤሌክትሪክ ሃይል በመቀየር ወደ ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል መስመር ማስገባት የሚችል ነው።
ቱሉ ሞዬ በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን ጦሳ ወረዳ ኢተያ አካባቢ የሚገነባ ፕሮጀክት ሲሆን፣ በሀገሪቷ ያለ ኤሌክትሪክ ለማመንጨት ከሚገነቡ ትልልቅ ግንባታዎች ውስጥ አንዱ ነው።

የጂኦተርማል ኢነርጂ ወደ ስራ ለማስገባት ከ10 ዓመት በላይ ጥናት የተካሄደበት ሲሆን፣ ከኹለት ዓመት በፊት ቁፋሮ በመጀመር ወደ ስራ የገባ የሀይል ማመንጫ ነው።
በፈረንጆች 2020 የተጀመረው የሀይል ማመንጫው የጉድጓድ ቁፋሮ በአሁኑ ሰዓት ኹለት ቁፋሮዎችን በማጠናቀቅ ሶስተኛው ጉድጓድ ቁፋሮ ተጀምሮ ኹለት ሺሕ ሜትር በላይ መሰራቱን ነዚፍ ጠቁመዋል።

የመጀመሪያው ቁፋሮ የተደረገበት እንፋሎት እየወጣ መሆኑንም ነዚፍ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ይህን እንፋሎት ምን ያህል ማመንጨት እንደሚችል በውጭ ሀገራት ባለሙያዎች ተጠንቶ፣ መረጃዎች ተሰብስበው ውጤት እየተጠበቀ ይገኛል ብለዋል። ይህ ጉድጓድ ያመነጨው እንፋሎት ላይ ኤሌክትሪክ ለማመንጨት የሚረዳ ጥናት ሲሆን፣ ጥናቱ ላይ እንፋሎቱ ሳይቋረጥ ለምን ያህል ጊዜ እንደሚቀጥል፣ ስንት ሜጋዋት ኤሌክትሪክ ሊያመነጭ ይችላል የሚል ነው። ለመጀመሪያው የሚጠናው ጥናት አጠቃላይ ለሚቆፈሩት ማመንጫ ሀይል መረጃ ለማግኘት ያስችላልም ተብሏል።

ቱሉ ሞዬ ጂኦተርማል የመንገድ ግንባታ፣ የውሃ ቁፋሮ እና ሌሎች የድጋፍ ስራዎችን እያከናወነ ሲሆን ከ150 በላይ የስራ እድል የፈጠረ ድርጅት ነው።
ተቋሙ እንደ ድርጅት የተቋቋመው በፈረንጆቹ ታህሳስ 2017 ሲሆን፣ ሳይንሳዊው ጥናት መካሄድ ከጀመረ አስር ዓመታት አስቆጥሯል።

የቱሉ ሞዬ ሃይል ማመንጫ ለመገንባት 850 ሚሊየን ዶላር የሚፈጅ ሲሆን፣ በእንፋሎት ሃይል ማመንጨት የሚያስችሉ 12 ቁፋሮዎች የሚያካሄድበት ነው።

ቱሉ ሞዬ ጂኦተርማል የሃይል ማመንጫ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የግል የከርሰ ምድርን እንፋሎት በመጠቀም ሀይል የሚያመነጭ ድርጅት ሲሆን፣ በ2017 ሀይል ለማመንጨት እና ለሀገር ወስጥ ጥቅም ለማዋል እቅድ ይዞ በመስራት ላይ ይገኛል።

የቱሉ ሞዬ ጂኦተርማል ኃይል ጣቢያ ፣ በኢትዮጵያ እየተገነባ ያለ 150 ሜጋ ዋት ማመንጨት የሚችል ሲሆን፣ ሙሉ በሙሉ ተገንብቶ ወደ ስራ ሲገባ በሚቀጥሉት አራት ዓመታት ውስጥ በታቀደው በሁለተኛው ምዕራፍ ወደ 150 ሜጋ ዋት እንዲያመነጭ አቅሙን ለማስፋፋት ያስችላል ተብሏል።


ቅጽ 3 ቁጥር 153 መስከረም 29 2014
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com