የእለት ዜና

ብሔራዊ የሎጅስቲክስ ካውንስል አዲስ የ‹ፎብ› መመሪያ ማጽደቁ ተገለጸ

የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣን፣ ብሔራዊ የሎጀስቲክስ ካዉንስል በተያዘው መስከረም ወር ባካሄደው መደበኛ ስብሠባው ‹የፎብ› (Free-On-Board FOB) መመሪያ ማጽደቁን ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።
ካውንስሉ በባህር ተጓጉዘው ወደ ኢትዮጵያ ለሚገቡ ዕቃዎች ትራንስፖርት የሚከፈለውን የውጭ ምንዛሬ አጠቃቀም ለማሻሻል የተዘጋጀው የፎብ መመሪያ ላይ ተወያይቶ አጽድቋል ሲሉ፣ የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣን የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር የሆኑት የሺ ፈቃደ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

አዲሱ የፎብ መመሪያ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶችን በተመለከተ የማጓጓዣ ወጫቸውን ለመቀነስ፣ እንዲሁም ከውጭ ወደ አገር ውስጥ የሚገባው ጭነት በተበጣጠሰ መልኩ የሚገባ በመሆኑ፣ በአንድ የትራንስፖርት ሥርዓት እና የግዥ ሥርዓት በአንድ በኩል ተጠቃሎ አገሪቱ በየቦታው የምታወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ለመቀነስ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ሲሉ ዳይሬክተሯ ጨምረው ገልጸዋል።

መመሪያው የተዘጋጀው በዋናነት የአገሪቱን የሎጂሰቲክስ ዘርፍ አፈጻጸም ወደተሻለ ደረጃ ለማሳደግ፣ ጠንካራና ተወዳዳሪ የሎጂስቲከስ አግልግሎት ሰጪ ኩባንያዎች እንዲፈጠሩ፣ ዘርፉን ቀስ በቀስ ለግል ባለሀብቱ ክፍት በማድረግ በውድድር እንዲመራ ማስቻል አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ እና የውጭ አገር ኢንቨስተሮች፣ የኢንዱስትሪ ዕቃ አምራች እና ላኪዎች፤ ተጨማሪ የሎጅስቲክስ አገልግሎት ሰጪዎችን የመጠቀም ዕድል እንዲያገኙ ለማድረግ እንደሆነ ተገልጿል።

እንዲሁም አገሪቱ የብሔራዊ የመርከብ ባለቤት ሆና እንድትቀጥል ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ፣ ባለፉት አመታት በፎብ የግዢ ሥርዓት በኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት አጓጓዥነት የተገኘውን አገራዊ ጠቀሜታ ተሻሽሎ እንዲቀጥል በመወሰኑ የፎብ መመሪያ እንደተዘጋጀ ተገልጿል።

የፎብ አሰራር ገቢ ዕቃን በማሰባሰብ (Economy of Scale) ዝቅተኛ የባህር ትራንስፖርት ዋጋ ለማስገኘት እና የውጭ ምንዛሪ ብክነትን ለመከላከል የሚያስችል ሲሆን፣ በሒደቱም የአገር ውስጥ የሎጂስቲክስ ኩባንያዎችን አቅም አጠናክሮ አገራዊ ፖሊሲን ለመተግበር የተሻለ ዕድል ይሰጣል ተብሏል።

እንዲሁም የፎብ መመሪያ መጽደቅ ከላይ ከተጠቀሱት ጠቀሜታዎች በተጨማሪ፣ በመልቲ ሞዳል ሎጂስቲክስ ኦፕሬሽን ላይ የነበረውን ሞኖፖሊ በማስቀረት፣ ቀስ በቀስ ወደ ነጻ የገበያ ውድድር ለማሸጋገር እንዲቻል አምስት የመልቲሞዳል ኦፕሬተሮች በዘርፉ እንዲሳተፉ የሚፈቅደውን እና በሰኔ ወር 2013 የጸደቀውን የመልቲሞዳል ኦፕሬሽን መመሪያ ቁጥር 802/2013 ተግባራዊ እንዲሆን ያስችላል ነው የተባለው።

የመልቲ ሞዳል ኦፕሬሽን ለግሉ ዘርፍ ክፍት መሆን፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዕድገት የፈጠረውን ከፍተኛ የወጪ ገቢ ጭነት ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ፍላጎትን ለማስተናገድ ዕድል የሚፈጥር ሲሆን፣ በገበያ ውድድር ከሚገኝ የዝቅተኛ ዋጋ አማራጭ እና የአገልግሎት ውጤታማነት አገሪቱን ተጠቃሚ ያደርጋልም ተብሏል።

የፎብ መመሪያ መጽደቅን ጨምሮ በብሔራዊ ሎጂስቲክስ ስትራቴጂዎች ተለይተው በዘርፉ እየተከናወኑ የሚገኙ የለውጥ ሥራዎች መተግበር፣ የሎጂስቲክስ ሥርዓቱ ላይ ውጤታማነትን በመጨመር ከዓለም አቀፍ ሎጂስቲክስ አፈጻጸም ቀመር (Logistics Performance Index) አንጻር የኢትዮጵያን ደረጃ ከፍ ለማድረግ ጉልህ ሚና እንደሚኖራቸው ተጠቁሟል።

በመጨረሻም በብሔራዊ ሎጅስቲክስ ካውንስል በጸደቀው የፎብ መመሪያ ላይ በዘርፉ የሚመለከታቸው አካላት ውይይት ያደረጉበት ሲሆን፣ ወደፊት ሕግ ፊት ቀርቦ ሕጋዊ ሰውነት ሲያገኝ በሥራ ላይ ይውላል ተብሏል።
ፎብ ማለት በዓለም አቀፍ የግብይት ሒደት ገዥ እና ሻጭ በሚያደርጉት የግዥ እና የሽያጭ ውል ገዥው ጫኝ መርከብን የሚመርጥበት፣ ሻጭ ደግሞ አስፈላጊውን ፎርማሊቲ አሟልቶ ጭነቱን በተመረጠው መርከብ ላይ የሚጭንበት የግዢ ሥርዓት ነው።


ቅጽ 3 ቁጥር 153 መስከረም 29 2014
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com