የእለት ዜና

አዲሱ ምዕራፍ የአዲስ መጽሐፍ እንዳይሆን ይታሰብበት!

ኢትዮጵያ እንደአገር ከተመሰረተች ከ4 ሺሕ ዓመት በላይ እንዳስቆጠረች ስሟ የተጠቀሰባቸው ጥንታዊ የታሪክ መዛግብት ይመሰክራሉ። ኹሉም ዘግይተው የተመሠረቱትም ይሁን በተመሳሳይ ወቅት የተቆረቆሩት አገራት ከዕድሜያቸው የተወሰነውን ክፍል በቅኝ ገዢዎች ሲተዳደሩ ቆይተዋል። የአውሮፓና አካባቢው የረጅም ዘመን ገዢ የነበረችው ሮም ሳትቀር ከገናናነቷ በፊት በግሪካውያኑ ሥር እንደነበረች ይነገራል። ኢትዮጵያ ግን እስካሁን ሳይቋረጥ በዘለቀው ታሪኳ ከመወረር በስተቀር ሳትገዛ ቆይታለች።

ለኢትዮጵያ አኩሪ ታሪክ ዋና ተመስጋኙ ኹሉን የፈጠረ አምላክ መሆኑን ማንም ኢትዮጵያዊ ባይክድም፣ አሁን ያለን ትውልዶች እንዳለን እንድንቆይ ያደረጉ አያት ቅድመ-አያቶቻችን በቀጣይነት መመስገን እንዳለባቸው የአዲስ ማለዳ ዕምነት ነው። “የኋላው ከሌለ የለም የፊቱ” እንደተባለው፣ የመጣንበትን የማናውቅ ከሆነ የምንሄድበትን አቅጣጫ ለመለየት ይቸግረናል።

ኢትዮጵያ በረጅም ዘመኗ መንግሥታት ሲቀያየሩባት የነበረ ቢሆንም፣ በዋናነት የሚጠቀሱት ጥቂቶች ናቸው። ከኩሽ በመልከፄዴቅ በኩል ሲወርድ ሲወራረድ የመጣውና ንግስተ ሳባ ጋር የደረሰው ሥርወ- መንግሥት በሰለሞን ልጅ ቀዳማዊ ምኒልክ ከተተካ ጀምሮ፣ የዛጉዌው ሥርወ-መንግሥት በመሃል ከመግባቱ ውጭ እስከዘመነ መሳፍንት መነሻ ድረስ ሳይቋረጥ ቆይቷል። አፄ ቴዎድሮስ የማዕከላዊውን መንግሥት ጉልበት ወደነበረበት ከመለሱ ወዲህ ግን ሥርወ-መንግሥት ለመዘርጋት የበቃ መንግሥት አልነበረም።

አፄ ቴዎድሮስ ለፍተው ዳግመኛ የመሠረቱትን ማዕከላዊ መንግሥትና ያሰባሰቡትን ሀብት ለፈለጉት ማስረከብ ባለመቻላቸው መንግሥታቸው ለውስጥ ጠላታቸው፣ አሰባስበው በመቅደላና ሌላም ግምጃ ቤት ያከማቹት የአገር ሀብት ለውጭ ወራሪዎች ሲሳይ ሊሆን በቅቷል። እሳቸውን ለአጭር ጊዜ የተኩት የላስታው አፄ ተክለጊዮርጊስም በተመሳሳይ ከባዶ የገነቡት በያለበት ባክኖ ቀጣዩ መንግሥት ሳይወርሰው ቀርቷል። የእሳቸውን ሥልጣን በጉልበት የነጠቁት አፄ ዮሐንስ አራተኛም በተራቸው ማስነው የሰበሰቡትን ሀብት፣ እንዲሁም ይሳሱለት የነበረውን ሥልጣናቸውን ለልጆቻቸውም ሆነ ለፈቀዱት ማስረከብ ሳይችሉ አልፈዋል።

ቀጥሎ የነገሱት አፄ ምኒልክ በሸዋ ከአያት ቅድመ አያቶቻቸው ነገሥታት የወረሱት ሥልጣንና ሀብትን አስፍተው አገርን አንድ አድርገው እስከ እለተሞታቸው ቢቆዩም፣ የፈለጉት ኑዛዜያቸው ተፈፃሚ አልሆነላቸውም። አልጋ ወራሻቸው የነበሩት ልጅ እያሱ የወረሱትን ይዘው ለመቀጠል የምዕራባውያኑ ተጽዕኖና የውስጥ ተቀናቃኞች ሴራ ስላላስቻላቸው ፍላጎታቸው በአጭር ነበር የተቀጨው። እሳቸውን ተክተው የነገሱት ንግስት ዘውዲቱ፣ እንዲሁም እንደራሴያቸው የነበሩትና በኋላም ራሳቸው የነገሱት አፄ ኃይለሥላሴም ቢሆኑ አመጣጣቸው መፈንቅለ መንግሥት ሊባል በሚችል ውጊያ ስለነበር ከባዶ ለመጀመር ተገደው ነበር።

ነገሥታቱ አንዱ ያንዱን ሥልጣን እየነጠቁ የአገር ሀብትንም ሆነ ሥልጣንን ባግባቡ ሳይረከቡ 200 ዓመታት ቢያልፉም፣ የመንግሥት አወቃቀሩም ሆነ ሥርዓቱና መተዳደሪያ ሕጉም ሳይቀየር በነበረበት ላይ እየተጨመረ ቆይቷል። ሕገ-መንግሥትንና ሌሎች ሕጎችን በተመለከተ ግን በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመን የምዕራባውያኑን የመሰለ ከፈረንሳይና ጃፓን የተቀዳ ሕግ ለሕዝብ እንደተበረከተ ተነግሮ ነበር። ይህ የሆነው ሕዝብ ጠይቆ ሳይሆን ምዕራባውያኑ ባቀረቡት ሐሳብ ምክንያት እንደሆነ ይነገራል። የሊግ ኦፍ ኔሽን አባል ለመሆን ያመለከቱት ንጉሠ ነገሥቱ እንደመስፈርት የተቀመጠላቸው የውጭ ዜጎችን የምትዳኙበት የእኛን የመሰለ ሕግ ስታወጡና ተግባራዊ ስታደርጉ ነው ስለተባሉ እንደሆነ የሕግ ታሪክ ትምህርት ያስረዳል።

ያም ሆነ ይህ፣ ለረጅም ዘመናት የቆየውን ሥርዓት መቀየሩን እሳቸው ሀ ብለው ቢጀምሩትም በቀጥታ ሕዝቡ ላይ ተፈፃሚ የሚሆን ሳይሆን ለይስሙላ ምዕራባውያኑን ለማስደሰት የተደረገ ነበር። ይህ ለውጥ የማምጣት ውጥናቸው፣ ተማሪዎች ብለው በዘመናዊ መልክ የውጩን ብቻ ለይተው እንዲማሩ በተንከባከቧቸው ተማሪዎቻቸው ላይም መልካም ፍሬን አላፈራም። የነበረውን ሥርዓት የገረሰሰ ጥሩውንም መጥፎውንም አብሮ ያቋረጠ አብዮት በተማሪዎች እንቅስቃሴ ፈንድቶ አገሪቷን እንዳልነበረች እንዳደረገ አዲስ ማለዳ ታምናለች።

ለሺሕ ዘመናት ተከብሮ የቆየን ሥርዓት ያስወገደው አብዮት ባዶ እጁን በመቅረቱ ሀብት ብቻ ሳይሆን ሥርዓትንም ከውጭ ለመዋስ ተገድዷል። የበፊቱን በመውቀስና በማንቋሸሽ ራሱን ከፍ ለማድረግ በማለምም፣ የቀደመው ሥርዓት ተሳታፊዎች ርዝራዥና ናፋቂ እየተባሉ የተወሰደው ዕርምጃ ባለቤቱን እየቀየረ አድማሱን አስፍቶ እስካሁን እንደቀጠለ ነው።

ከባዶ የተነሳው የወጣቶች አመፅ በአባቶቹ ላይ ጭምር በመነሳት ሥርዓተ-መንግሥቱን ብቻም ሳይሆን ባህልና ኃይማኖትን ለመቀየር ብዙ ጣረ። ፈጣሪ ለዘመናት ሲመለክባት በኖረች አገር ድንገት ፈጣሪ የለም በሚሉ ወጣቶች ኃይማኖት የሚባል ነገር ሲከለከል የአገርን ታሪክ ማስቀጠል ሳይሆን አዲስ አገር የመመስረት ያህል ሆኖ ነበር። ይህ ሥርዓት ዕድሜ ልኩን ሲዋጋና ሕዝብን ሲያዋጋ ቆይቶ በተራው ተገረሰሰ ሲባል የተኩት ተመሳሳዮቹ ነበሩ። ለአገር ባላቸው ፍቅር ቢለያዩም ለሺሕ ዘመናት ከቆየው ሥርዓት አንፃር የሚያመሳስላቸው ይበዛል።

ደርግ የዘውዳዊውን ሥርዓት ተቋማትም ሆነ ወታደሮችን ወርሶ የበላይ አዛዦችን ብቻ አስወግዶ ቢቀጥልም፣ ወያኔ ተብሎ በጦርነት ቤተመንግሥት የገባውና እስካሁን የቆየው ሥርዓት የአገሪቱ የታሪክ መጽሐፍ ላይ አዲስ ምዕራፍ እንደማስጀመር፣ አዲስ መጽሐፍ ይፃፍልኝ ብሎ ታሪኩ ጭራሹኑ ከመጽሐፉ ላይ ሊፋቅበት እስኪችል ድረስ አገርን የሚያወድም መንገድ እየተከተለ ነው።

የመንግሥት ለውጥ ተብሎ በቅርቡ የተፈጠረው ክስተት ከ1991ዱ የውስጥ ክፍፍላቸው የተለየ አይደለም የሚሉ፣ በተጨባጭ ከሰዎች መቀያየር በስተቀር አዲስ ምዕራፍ ሊያስብል የሚችል ለውጥ አለመምጣቱን ያነሳሉ። ከሕገ-መንግሥቱ አንስቶ የቀደሙት ፈላጭ ቆራጮች እንዲመቻቸው አድርገው የተከሉት ዘር ተኮር ሥርዓትም ሆኑ በርካታ መገለጫዎቹ ባሉበት ሆነው አዲስ የመጣ ለውጥ ስለሌለ ታግሰን እንጠብቅ የሚሉም አሉ።

አሁን አዲስ ምዕራፍ መባሉን የሚጠላ ባይኖርም፣ ለዘመናት የቆየው ታሪክ እንዲቀር ተደርጎ በተጀመረው አዲስ መጽሐፍ ላይ ምዕራፍ ኹለት እንዳይሆን ሥጋት አለን የሚሉትን ሐሳብ አዲስ ማለዳ ትጋራለች። ተወደደም ተጠላም የአገር ታሪክ የኹላችንም ነው። የአዛዥና ታዛዥ ልጆች ብንሆንም አሁን ያለንና ለወደፊት የሚኖረንን እኩል ተሳትፎ ያህል አባቶቻችን እንደነበራቸው መቀበል ግድ ይላል።

አድዋ የዘመቱት የኹሉም ኢትዮጵያውያን ተወካዮች እንደመሆናቸው ይዘውት የዘመቱት ሠንደቅ ዓላማችንን የመሳሰሉ መገለጫዎቻችን የጋራ እንደሆኑ መልሰን ለመቀበል የምንችልበት የታሪክ አጋጣሚ ላይ እንገኛለን። የአገርን ምልክት የአንድ ኃይማኖት ነው በማለት፣ የዕምነቱ የረጅም ዘመናት ሿሚዎች የነበሩት ግብጻውያን የማይጠቀሙበትን ምልክት ታሪኩን አዛብቶ መግለጹ እንደማያዋጣ ልንረዳ ይገባናል። “አይወክለንም” ብለን አሁን የምናጥላላው ነገር እኛን ከባለቤትነት ማራቁ ብቻ ሳይሆን አባቶች የተዋደቁለትን ታሪክ በገዛ እጅ አሳልፎ መስጠትና እነሱን ማሳነስ መሆኑን ልንገነዘብ ያስፈልጋል።

ለሺሕ ዘመናት በአንድነት ከኖሩበት አገር፣ “ነጻነት እናግኝ” ብለው ላሉበት ክብር ያበቋቸውን አያት ቅድመ-አያቶቻቸውን ለሺሕ ዘመናት በባርነት ቆይተዋል ብለው የሚሰድቧቸውም፣ የታሪክ ምልከታቸውን ቢያስቡበት እንደሚሻላቸው አዲስ ማለዳ ታመክራለች።
ከአገራችን ስያሜ ጀምሮ ኢትዮጵያ መባሏ በቂ ሆኖ ሳለ፣ “ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ” ብሎ ማብራሪያ መስጠቱ ለማን ተብሎ እንደሆነ ሊታሰብብት ይገባል። የአገር አርማ የሆነውና የመላ አፍሪካውያን መለያ የሆነው አንበሳ ሳይቀር ወደነበረው ክብሩ ሊመለስ ይገባል። የቀደመው መጽሐፍ ላይ ይሁን ወይስ አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀው ህወሓት በጀመረው አዲስ መጽሐፍ ላይ አዲሱ ምዕራፍ የሚጀምረው ሕዝቡ በቶሎ እንዲያውቅ መደረግ እንዳለበት አዲስ ማለዳ ታሳስባለች።

ታሪክ ወደድነውም ጠላነውም እውነታ ስለሆነ ከእኛ ጋር ብቻ ሳይሆን ከቀጣይ ትውልድ ጋርም አብሮ የሚጓዝ ነው። ከአሁን በኋላ የሚጓዝበትን መንገድ መቀየስ ብንችልም፣ ከሰማይ ወርደን ከፈለግንበት ቦታ ወደፈለግንበት ማስመር አይቻለንም። አቅጣጫ ለማስተካከል ወደ ኋላ እያዩ ወደፊት ይሮጣል እንጂ፣ ፊቱን ብቻ እያዩ መገስገስ ያጋጫል። የኋሊት ተመልሶ እንዳዲስ ለመጀመር ከታሰበ ተከትለው የሚሮጡት ሊጨፈልቁ ስለሚችሉና ወድቆ መቅረትን ስለሚያስከትል፣ የመሮጫ መንገዱንም ሆነ አቅጣጫውን ቀድሞ ማወቅ ያስፈልጋል። የሚያባርርንም ሆነ የሚከተልን ሳይደርስ በፊት በመለየት የውድድሩ ማብቂያ ጋር መድረስ ግድ ይላል።

አዲስ ምዕራፍ የተባለው ሌላ የአዲስ መጽሐፍ አዲስ መቅድምም ሆነ መግቢያ እንዳይሆን ብቻ ሳይሆን፣ መስሎ እንዳይታይም ከወዲሁ ምዕራፉን እፅፋለሁም ሆነ አሳትሜ አሰራጫለሁ የሚለው ወገን ሊያስብበት ይገባል። የሚያነበውም ሆነ የሚገዛው እንዳይጠፋም በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ሊቋጭ ያልቻለው የጦርነት ምዕራፍ ትኩረት ተሰጥቶት በአፋጣኝ እልባት ሊያገኝ እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ታሳስባለች።


ቅጽ 3 ቁጥር 153 መስከረም 29 2014
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com