የእለት ዜና

ሰንደቅ ዓላማ ቀን “በአዲስ ምዕራፍ በተሟላ ሉዓላዊነት ለሰንደቅ ዓላማችን ከፍታ” በሚል መሪ ቃል የፊታችን ሰኞ ይከበራል

በአገራችን ለ14ኛ ጊዜ የሚከበረው የብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ ቀን በዓል የፊታችን ሰኞ ጥቅምት 1 ቀን 2014 “በአዲስ ምዕራፍ በተሟላ ሉዓላዊነት ለሰንደቅ ዓላማችን ከፍታ” በሚል መሪ ቃል ተከብሮ እንደሚውል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለአዲስ ማለዳ በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡

ምክር ቤቱ ሰንደቅ ዓላማ የብሔራዊ አንድነት መገለጫ፤ የአንድ አገር ዜጎች አገራዊ ፍቅርና ብሔራዊ ስሜትን የሚገልፁበት፤ ታሪካዊ ትስስርና ሥነ-ልቦናዊ አንድነት የሚንፀባረቁበት የአገራዊ አንድነትና ህብረት አርማና ምልክት እንደሆነ በመግለጫው ገልጿል፡፡

ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን በተሻሻለው የሰንደቅ ዓላማ አዋጅ ቁጥር 863/2006 አንቀጽ 2 መሰረት በየዓመቱ ጥቅምት ወር በገባ በመጀመሪያው ሳምንት ሰኞ እንደሚከበር ተደንግጎ የሚገኝ ሲሆን፤ በአገራችን በተለያየ መልኩ እየተከበረ 13 ዓመታትን ማስቆጠሩንም አስታውሷል።

ዘንድሮ 14ኛው የሰንደቅ ዓላማ ቀን በዓልም ወቅቱንና አገራዊ ነባራዊ ሁኔታዎችን ባገናዘበ መልኩ “በአዲስ ምዕራፍ በተሟላ ሉዓላዊነት ለሰንደቅ ዓላማችን ከፍታ” በሚል መሪ ቃል እና በሌሎች መልዕክቶች ታጅቦ የፊታችን ሰኞ ከረፋዱ 4፡30 ጀምሮ በፌዴራል፣ በክልሎችና በሁለቱ ከተማ አስተዳደር ም/ቤቶች ሰንደቅ ዓላማ በመስቀል እና በሰንደቅ ዓላማ ፊት ቃለ መሐላ በመፈፀም ሥነ ሥርዓት እንዲሁም በተለያዩ ዝግጅቶች በደማቅ ሁኔታ እንደሚከበርም አስታውቋል፡፡

በዓሉ በአገራችን አዲስ ፓርላማ እና የመንግስት ምስረታ በተካሄደበት እንዲሁም አዲስ ምዕራፍ በተጀመረበት ወቅት የሚከበር በመሆኑ ልዩ እንደሚያደርገውም ምክር ቤቱ ገልጿል፡፡

በሌላ መልኩ የውስጥና የውጭ ጠላቶቻችን ብሔራዊ አንድነታችንን እና ሉዓላዊነታችንን እየተፈታተኑ ባሉበት በዚህ ወቅት የሰንደቅ ዓላማ በዓሉን ማክበር፤ ተናበንና ተደራጅተን በተባበረ ክንድ የተጋረጠብንን የህልውና አደጋ ለመመከትና ለመቀልበስ ፤ ለብሔራዊ አንድነታችንና ሉአላዊነታችን ያለንን ቁርጠኝነት በባንዲራችን ፊት ዳግም ቃላችንን የምናድስበት እና ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው ዕለት ነው ሲልም በመግለጫው አስታውቋል፡፡

የሰንደቅ ዓላማ በዓሉ በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት መሪነት በመላው አገሪቱ በፌደራል የመንግስት ተቋማት፣ በክልሎችና በሁለቱም አስተዳደር ከተሞች ፣የመከላከያ ሰራዊት ካምፖች እንዲሁም በኢምባሲዎችና የኢትዮጵያ ሚሲዮኖች በተመሳሳይ ሰዓት ሰንደቅ ዓላማ በመስቀልና በሰንደቅ ዓላማ ፊት ቃለ መሐላ በመፈፀም ሥነ-ሥርዓት እንዲሁም በተለያዩ ዝግጅቶች በደማቅ ሁኔታ እንደሚከበርም ምክር ቤቱ ገልጿል፡፡
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com