የእለት ዜና

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአራት ዘርፎች የምርጥ ‘ስካይትራክስ’ ሽልማት አሸነፈ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በ2021 በአራት ዘርፎች የምርጥ የ’ስካይትራክስ’ የአየር መንገድ ሽልማቶች አሸናፊ ሆኗል።

አየር መንገዱ እ.አ.አ የ2021 የአፍሪካ ምርጥ አየር መንገድ ሽልማትን ጨምሮ ለ4 ተከታታይ ዓመታት ነው የተቀዳጀው።

የአፍሪካ ምርጥ የቢዝነስ ክፍል ሽልማትን ለ3 ተከታታይ ዓመታት፣ የአፍሪካ ምርጥ የምጣኔ ሃብት ክፍልም ለሶስት ተከታታይ ዓመታት አሸንፏል፡፡

በተጨማሪም የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ የ2021 ምርጥ የበረራ ሠራተኞች ሽልማት ማሸነፉ ተገልጿል።

አየር መንገዱ በዓለም አቀፍ የአየር መንገድ ደንበኞች ምርጫ እ.አ.አ በ2021 ሰባት ደረጃዎችን በማሻሻል ከምርጥ 100 የዓለም አየር መንገዶች 37ኛ ደረጃ መያዙም ተነግሯል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ተወልደ ገብረማሪያም፤ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከተከሰተ ወዲህ አየር መንገዱን በስኬት ማስቀጠል ፈታኝ ሥራ እንደነበር ገልጸዋል።

ሆኖም “እኛ ኢትዮጵያዊያን ተስፋ አልቆረጥንም፣ ለደንበኞቻችን ያለንን ታማኝነት ጠብቀን በረራችንን በመቀጠላችን ስኬት አስመዝግበናል” ብለዋል።

ሽልማቶቹ በዓለም ዙሪያ ያለማቋረጥ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል የጥራት ማረጋገጫ መሆኑን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

አየር መንገዱ የተጓዦችን ድምጽ በማግኘት የ’ስካይትራክስ’ ሽልማት አሸናፊ መሆኑ ስኬቱን ያጠናክረዋል ነው ያሉት ተወልደ።

የስካይትራክስ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኤድዋርድ ፕሌስቴድ በበኩላቸው “የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሽልማቱን ለአራት ተከታታይ ዓመታት በማሸነፍ ምርጥ የአፍሪካ አየር መንገድ መሆኑን አስመስክሯል” ብለዋል።

ዓለም አቀፉ የአየር መንገድ ሽልማት እ.አ.አ በ1999 የተጀመረ ሲሆን ገለልተኛ፣ ነፃ እና እውነተኛ የደንበኞችን የእርካታ ድምጽ መሰረት አድርጎ ይሰጣል።
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com